Home ከታሪክ ማህደር ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ

ዘውዲቱ ምኒልክ ከአባታቸው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የወረኢሉ ተወላጅ ከሆኑት እናታቸው ከወይዘሮ አብቺው በተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ፣ በሞረትና ጅሩ ወረዳ ሰገነት ከምትባል አነስተኛ መንደር ሚያዝያ 22 ቀን 1868 ዓ.ም ተወለዱ።

ንጉሠ ነገሥታት አፄ ዩሐንስ ከሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጋር በስልጣን ሽኩቻ የተነሳ የገቡበትን ጠብ ለማብረድ ፣ በመካከላቸው ያለውን ቅራኔ ለማለዘብ አስበው ገና የስድስት ዓመት ከመንፈቅ የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙትን ዘውዲቱንና በአስራ ሁለት ዓመት እድሜ ላይ ያሉትን ልጃቸውን አርአያ ሥላሴ ዩሐንስን በጋብቻ ለማስተሳሰር ፣ ልጃቸውን ለልጃቸው እንዲድሩላቸው ራስ አሉላን ፣ ራስ ገብረኪዳንን እና ቢትወደድ ገብረመስቀልን አማላጅ አድርገው ከምኒልክ ዘንድ ቢሰዱ ፣ ምኒልክም ይሁን ብለው ጋብቻውን ፈቅደው ተቀበሉ።

ቀን ተቆርጦም ጋብቻው በከፍተኛ ድምቀት ጥቅምት 13 ቀን 1875 ዓ.ም በቤተክርስቲያን ስርዓት በተክሊልና በቁርባን ተከናወነ። ቢሆንም ግን ራስ አርአያ ሥላሴ ዩሐንስ ገና በወጣትነት እድሜያቸው ላይ ሳሉ ድንገት በመሞታቸው ምክንያት በንጉሠ ነገሥቱ ሀሳብ ታቅዶ የተመሰረተው ጋብቻ ሳይሰምር በአፍላነቱ ቀረ። ከዚያም ከዓመታት ቆይታ በኋላ ዘውዲቱ ደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድን ያገቡ ቢሆንም ይህ ጋብቻም እንከን ገጥሞት በፍቺ ለመቋጨት በቃ። ዘውዲቱ በዚህ ሁኔታ በብቸኝነት አምስት ዓመታትን ያህል ከቆዩ በኋላ እንደገናም ከራስ ጉግሣ ወሌ ጋራ በትዳር ለመጣመር በቅተዋል። በዚህ ትዳራቸውም ደስተኛ ሆነው ረዥም ዓመታትን ለማሳለፍ ቻሉ። የኋላ የኋላ ግን የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥታት ሆነው ዙፋን ላይ ሲወጡ በዙሪያቸው ባሉ ወግ አጥባቂ የሸዋ መኳንንቶች ቅጥ ያጣ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተነሳ እንደገናም በትዳራቸው ለመቆየት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ልጅ እያሱ ከመኳንንቶቻቸው ጋራ ከገቡበት ከፍተኛ ቅራኔ ላይ እንዳሉ ሁሉን ቸል ብለው ለጉብኝት ከአዲስ አበባ ተነስተው ሐረር በተጓዙበት ግዜ ፣ ይህን አጋጣሚ የሚጠባበቁት እንደ ራስ ወልደጊዮርጊስ ፣ ከንቲባ ገብሩ ፣ በጅሮንድ ተክለሐዋርያት ፣ ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝና የመሳሰሉ ያሉ መኳንንቶች ከአቡኑ ጋራ ባንድነት ሆነው ልጅ እያሱ ከስልጣን መውረዳቸውን ባዋጅ አሳወቁ። ከዚያም ዘውዲቱ ምኒልክ ዙፋኑን እንዲወርሱና ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን አልጋ ወራሽ ሆነው እንዲሾሙ ተወሰነ ። ይህ ውሳኔ መስከረም 21 ቀን 1909 ዓ.ም ፀድቆም “ግርማዊት ዘውዲቱ ፣ ንግሥተ ነገሥታት ዘ ኢትዮጵያ” ተብለው ዘውዲቱ ነገሡ ። በዚያው ዓመት ላይ በጥቅምት ወር በአዲሱና በነባሩ አስተዳደር መካከል ከተደረገው የሰገሌ ጦርነት በኋላም ከአውሮፓ የመጡና በአፍሪካ በጎረቤት ሀገራት ያሉ የእንግሊዝና የፈረንሳይ ሹማምንቶች በተገኙበት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ከአውራጃ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ገዢዎችና መኳንንቶች በተሰበሰቡበት የካቲት 4 ቀን 1909 ዓ.ም በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ አንጋሽነት በደማቅ ስነስርዓት የንግሥና በዓላቸው ተከናውኗል።

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በስልጣን ዘመን ምንም እንኳ ከብዙ ፈተናዎች ጋራ ለአጭር ግዜያት ብቻ ቢቆዩም አያሌ ስራዎችን ግን አበርክተዋል ። ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ መስከረም 17 ቀን 1916 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አባል ሀገር እንድትሆን አድርገዋል። በዚህም ደጃዝማች ናደው የተባሉ መኳንንት የኢትዮጵያ መንግሥትና የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዋና መልዕክተኛ በመሆን ከፍተኛ ግልጋሎትን ሰጥተዋል።

በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ፍቃድና ፍላጎት በልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን አማካኝነት መጋቢት 16 ቀን 1916 ዓ.ም ” ስለ ባሮች አስተዳደርና ነፃነት የቆመ ደንብ ” በሚል አርዕስት ተራማጅ አስተሳሰብን የያዘ ስለ ሰው ልጆች እኩልነትና ነፃነት የሚያትት ህገ ደንብ በመፅሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ በአልጋ ወራሹ ማተሚያ ቤት ታትሞ እንዲወጣ ተደርጓል። ንግሥተ ነገሥታቱ የታላላቆቻቸው ታሪክ ለትውልድ እንዲቆይ የነበራቸው ፍላጎት ላቅ ያለ በመሆኑ ባደረጉት ጥረት በእንግሊዞች ከመቅደላ ተዘርፈው ከሄዱት ውድ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አንዱ የሆነውን የአፄ ቴዎድሮስን ዘውድ ለማስመለስ ችለዋ።

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በኢትዮጵያ ስልጣኔ እንዲስፋፋ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። የአባታቸውን የዳግማዊ አፄ ምኒልክን ፈለግ በመከተል በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት እንዲጎለብት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል ። ህፃናትና ወጣቶች የዘመናዊ ትምህርት ተቋዳሽ እንዲሆኑ በአዋጅ አስደግፈዋል። ያወጡትን አዋጅ ተላልፎ የተገኘ ወላጅ የሚጣልበትን የቅጣት የብር መጠን ተምነው ተፈፃሚነቱን እንዲከታተሉ ለቤተክህነት አባቶች ስልጣኑን ሰጥተዋል። በሆስፒታል እና በአብያተ ቤተክርስቲያን ግንባታ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎና ክትትል በማድረግ አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል።

ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ኢትዮጵያን ከ1909 ዓ.ም አንስቶ እስከ 1922 ዓ.ም ድረስ ለአስራ ሦስት ዓመታት ያህል ገዝተው መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም ህይወታቸው ያለፈች ሲሆን ቀብራቸውም አዲስ አበባ በታዕካ ነገሥታት በዓታ ቤተክርስቲያን ተፈፅሟል።

ዘውዲቱ ምኒልክ ከሁለተኛ የትዳር አጋራቸው ከደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድ ጋር በጋብቻ ተሳስረው በሚኖሩበት ግዜ ከዕለታት አንድ ቀን ደጃች ውቤ ዘውዲቱን በጥፊ ቢመቱ ፣ ዘውዲቱ የንጉሥ ልጅ ናቸውና ለምን ተነካሁ ብለው ተናደው ፈጥነው ከአባታቸው ከምኒልክ ዘንድ ሄደው ስለመመታታቸው አቤቱታ ቢያሰሙ ፣ ንጉሥ ምኒልክም ደጃች ውቤን አስጠርተው ምን ቢያደርጓቸው ልጃቸውን እንደመቷቸው ቢጠይቁ ከደጃች ውቤ ምላሽ በማጣታቸው ደጃች ውቤን አንድ ግዜ በጥፊ አልሰው ሸኝተዋቸዋል። ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ አባታቸው እምዬ ምኒልክ ለረዥም ግዜ የአልጋ ቁራኛ ሆነው መታመማቸው እንዲሁም የጀመሩትን ፣ ያሰቡትን ከዳር ሳያደርሱ ማለፋቸው እጅጉን ያንገበግባቸው ስለነበር እምዬ ካለፉ በኋላ ዘውዲቱ እንዲህ ብለው በግጥም ሀዘናቸውን ገልፀው ነበር።

ወልደውኛል እንጂ እኔ አልወለድሁዎ

አንጀቴን ተብትበው ምነው መያዝዎ።

ቀድሞ የምናየው የለመድነው ቀርቶ

እንግዳ ሞት አየሁ አባቴ ቤት ገብቶ።

እጅግ አዝኛለሁ አላቅሰኝ አገሬ

የሁሉ አባት ሞተ ተጎዳችሁ ዛሬ።

አሻግሬ ሳየው እንዲያ በሰው ላይ

መከራም እንደሰው ይለመዳል ወይ።

በቸር ያቆየን።