
‹‹እህል ዘርፋችኋል ተብሎ እርዳታ መቆሙ ትልቅ ውርደት ነው››
‹‹የተማረን ወጣት ሥራ አልሰጥህም ማለት ከመንግሥት አይጠበቅም››
በሀገራችን መንግሥት በቅርቡ ይፋ ካደረገው የንብረት ታክስ ጀምሮ በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የኑሮ ውድነት የዜጎችን ኢኮኖሚ እና በልቶ የማደር አቅም በእጅጉ እየፈተነው ነው፡፡ በዛ ላይ በየቦታው የሚሰማው ግጭት እና የቤቶች ፈረሳ፣ የእርዳታ እህል ዘረፋ እና ግዙፍ የሚባሉ የኢኮኖሚ ተቋማትን ለመሸጥ በመንግሥት በኩል እየተሔደበት ያለው ሩጫ አሳሳቢ ኾኗል፡፡ በእነኚህ እና ተያያዥ በኾኑ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ታዋቂውን የምጣኔ ሐብት ባለሙያ አቶ ክቡር ገናን እንግዳ አድርገን በመጋበዝ አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጋርተውናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- በቅርቡ የተጀመረው የንብረት ታክስ በሀገሪቱ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ምንድን ነው?
ክቡር፡- የታክሱ አነሳስ የሚያስደንቅ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ታክስ የሚመደበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ነው፡፡ አሁን ግን ድንገት መወሰኑ ዱብዳ ነው የኾነው፡፡ የንብረት ታክስ ተብሎ ሲተመን ለምን 4.5 ኾነ የሚለው እራሱ በውይይትና ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ መፈጸም ነበረበት፡፡ በተለይ አሁን ጊዜው ነው ወይ የሚለው የሚያነጋግር ነው፡፡ መንግሥት ድንገት ተነስቶ ያመጣው ነገር ነው የሚመስለው፡፡ በመሠረቱ የንብረት ታክስ የሚባለው ለአካባቢ ልማት የሚውል ገንዘብ ነው፡፡ በዚያ አካባቢ ላለ መሠረተ ልማት አገልግሎት የሚውል ነው፡፡ ሕዝብ ተወያይቶ የሚያስፈልገውን አይቶ በየጊዜው በስምምነት የሚከፍለው ነው፡፡ ችግሩ ግን አነሳስና አተማመኑ ላይ ነው፡፡ አሁን የሚተመነው የቤት ኪራይ ተተምኖ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ስህተት ሊኖረው ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ተከራዩ ምንም በማያወቀው ሁኔታ የቤት ኪራይ ሊጨምር ይችላል፣ ክፍያው ከአቅም በላይ ኾኖ የቤት ባለቤቱን ቤት እስከማሳጣት ሊደርስ ይችላል፡፡
ስለዚህ ይህ ዐይነቱ አካሄድ ትክክል ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው፤ በእኔ እይታ አሁን ባለንበት ችግር ታክሱ ጠቃሚ ቢኾን እንኳ ወቅቱ ግን አይደለም፡፡ ሕዝቡንም ያላወያየ በመኾኑ ከጥቅም ይልቅ ጉዳት ያመጣል ባይ ነኝ፡፡ በእርግጥ አሁን ሰው ፍርሃት ላይ ስለኾነ ቤቴ ይወረሳል ብሎ ሊከፍል ይችላል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዐይነት ታክስ ሲጣል ሁለት ዓመትም ይሁን ሦስት ዓመት ጊዜ ተሰጥቶ ነው መጣል ያለበት፡፡ ሕዝቡ ተዘጋጅቶ ገንዘቡንና ገቢውን አስልቶ ታክስ አለብኝ ብሎ እንዲያስብ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን ግን ያላሰበው ወጭ ነው የመጣበት፡፡ ይህ አሁን ካለው ድህነት አንጻር ለሕዝቡ አስቸጋሪ ነው፡፡
ግዮን፡- የንብረት ታክስ አጀማመሩ ለኅብረተሰቡ ሰፊ ማብራሪያ ሳይሰጥበት ቁርጥ ያለ የመክፈያ ጊዜ ተቀምጦለት ቀኑን ያሳለፈ እንደሚቀጣ መነገሩስ እንዴት ይታያል?
ክቡር፡- በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ሕዝብን በዚህ መልኩ ሊያስጨንቅ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ በሚመርጥበት ጊዜ እንዲህ ዐይነት ነገሮች እንዳሉ በምርጫ ቅስቀሳው አልተነገረውም፡፡ በወቅቱ መንግሥት በምርጫ ቅስቀሳ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ሲያስተዋውቅ ይህንን ጉዳይም ይፋ ማድረግ ነበረበት፡፡ ሕዝብ የሚመርጠው ቅስቀሳውን አይቶ ነው፡፡ ድንገት በምሥጢር በሚመስል መልኩ ‹‹ይህንን ያልከፈልክ…›› ማለት አግባብ አይደለም፡፡ ምሥጢራዊ በሚመስል መንገድ መረጃን በማሰራጨት ሕዝብን ማስጨነቅ ከመንግሥት አይጠበቅም፡፡
ግዮን፡- የ2016 ዓ.ም በጀት አመዳደብና በተለይ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን በተመለከተ ይፋ የተደረገው ክፍፍል ፍትሐዊ ነው ማለት ይቻላል?
ክቡር፡- በጀት ሲመደብ መስፈርቶች መኖር ይኖርባቸዋል፡፡ ያሉትን ችግሮችና የወደፊት ገቢዎች ከግምት ባስገባ መልኩ ነው በጀት የሚመደበው፡፡ እንደተባለው የአማራ፣ የአፋርና ትግራይ ክልሎች በጦርነቱ በጣም ተጎድተዋል፡፡ በመጠኑም ቢኾንም ኦሮሚያ ክልል እነዚህ ክልሎች የደረሰባቸውን ችግር ያህል አልደረሰበትም፡፡ ስለዚህ የበጀት አመዳደቡ ትንሽ ፍትሐዊነት የጎደለው ይመስላል፡፡ መስተካከልም ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በተለይ ሦስቱ ክልሎች በጦርነት ብዙ ሀብታቸው ወድሟል፡፡ የአማራ ሕዝብም ይሁን ሌላው ፈልጎ የመጣበት ችግር አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ በግድ ተለምኖ የተሳተፈበት ጦርነት በመኾኑ በጀቱን ማስተካከል የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ የበጀት ቀመሩ ድጋሜ መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡
ግዮን፡- መንግሥት በሚቀጥለው ዓመት ምንም ዐይነት የሠራተኛ ቅጥር እንደማያደርግ አስታውቋል፤ ይህ ነገር በተለይ ከተመራቂ ተማሪዎች አንጻር እንዴት ይታያል? እንደመንግሥትስ እንዲህ ማለት ይቻላል?
ክቡር፡- መንግሥት በአጠቃላይ እንዲህ ዓይነት መልእክት ማስተላለፉ ‹‹ገንዘብ የለም›› የሚለውን ለመጠቆም ነው፡፡ በጀቱ ይህንን ስለማይፈቅድ ቅነሳ እንደሚያደርግና ጭማሪ እንደማይኖር አስታውቋል፡፡ እንደ መንግሥት ይህን እርምጃ ወሰድኩ ሲል በመሠረቱ ይህ መተካት የሚችል እቅድ ሊኖረው ይገባል፡፡ መንግሥት ሊፈቅዳቸው የሚገባ በተለይ ለሕብረተሰቡ ሁኔታዎች ተመቻችተውለት የኢንቨስተመንት አቅሙም ከፍ ብሎ የሥራ እድል ሊፈጥር የሚችልበትን መንገድ ካላስቀመጠ ተመራቂ ተማሪዎች የበለጠ ችግር አምጪዎች ይኾናሉ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህን ያደረገው የእሱን ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡ የሕዝብ ችግር ለማቃለል ድጋሚ ማሰብ ይኖበታል፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ትልቁ የሠራተኞች ቀጣሪ በመኾኑ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥት አልቀጥርም ካለ የንግድ ኅብረተሰቡ የሚቀጥርበትን ሁኔታ ካላመቻቸ የንግድ ኅብረተሰቡን እነዚህን ተመራቂ ወጣቶች ሊቀበል አይችልም፡፡ ስለዚህ እጣ ፈንታቸው ምን ሊኾን እንደሚችል መገመት ከባድ ነው፡፡ የተማረን ወጣት ሥራ አልሰጥህም ማለት ከአንድ መንግሥት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ የሌሎች ሀገራትን ሁኔታ ስንመለከት እንዲህ ዐይነት ውሳኔ ላይ ለመድረስ አይደፍሩም፡፡
ግዮን፡- ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንጻርና በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ከነበረው ቤት ፈረሳ ጋር ተያይዞ ከመጣው ቀውስ አንጻር መንግሥት ለሥራ አጥነት ያሳየው ቸልተኝት እንዴት ይታያል?
ክቡር፡- የአዲስ አበባ ዙሪያ ምንም እንኳን መንግሥት አስተዳዳሪ ቢኾንም ባለቤቱ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ መንግሥት ነው የሕዝብን ሀብት እየነጠቀ ያለው፡፡ ከተማ ሲፈርስም ኾነ ሲገነባ በእቅድ መኾን ይኖርበታል፡፡ ሲፈርስ ዓመታት ሊወስድ የሚገባው እንጂ በአንዴ ሕዝብን አፈናቅሎ ዞር በሉ በማለት የሕዝብ መንግሥት መኾን አይቻልም፡፡ ካለዚያ መንግሥት የአንድ ወገን ወይም አካል ጥቅም አስፈጻሚ ኾኗል ማለት ነው፡፡ ከተማ የሚገነባው ለሕዝብ ነው እንጂ ሕዝብ ለከተማ መፈናቀል የለበትም፡፡ ከተማ መሻሻል ያለበት ለሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ከተማ ሲሻሻልና ሲያድግ ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ ነው መስተካከል ያለበት፡፡ ዝም ብሎ ሕዝብን ያለ ፕላን 10 እና 20 ዓመት ኖረሃልና ተነስ አይባልም፡፡ ይሄ ለሕዝባዊ መንግሥት ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው፡፡
ሕዝባዊ መንግሥት ከዜጎቹ ጋር ተቀራርቦና ተወያይቶ የሚሠራ ነው፡፡ 10-15 ዓመት ግብ አስቀምጦ ነው የሚሠራው እንጅ ደስ ባለው ቀን ጠዋት ተነስቶ ቤት የሚያፈርስበት አግባብ የለም፡፡ ሰው በሀገሩ መጠለያ የማግኘት መብት አለው፡፡ አንድ ግለሰብ የመማር፣ መጠለያ የማግኘት፣ የመናገር መብት እንዳለው ሁሉ የመኖርም መብት አለው፡፡ እራሱ በሰራው መጠለያ ቤት ውስጥ የመኖር መብቱን በመንግሥት ሊገፈፍ አይገባም፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፤ ትክክል አለመኾኑን ደግሞ መንግሥት አሁን ባለበት ሁኔታ መመለስ የሚችለው አይደለም፡፡
ግዮን፡- የዩኒሴፍ እርዳታ ማቆም ኢትዮጵያ ካላት 20 ሚሊዮን የተራበ ሕዝብ አንጻር የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዴት ሊገለጽ ይችላል?
ክቡር፡- አሜሪካም ኾነች ሌላው እርዳታ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም፡፡ እርዳታ የሚሰጠው በፍላጎት ነው፡፡ ችግሩ ያለው እኛ ጋር ነው ፤ ‹‹የእርዳታ እህል ዘርፋችኋል›› ተብሎ እርዳታው መቆሙ ትልቅ ውርደት ነው፡፡ አንድ በኃላፊነት ላይ የተቀመጠ መንግሥት ለእርዳታ የመጣን እህል ፈጭቶና አሽጎ ወደ ውጭ መላክ ትልቅ ኃጢያት ነው፡፡ ምክንያቱም እርዳታው የተቀማው ከተራበ ሕዝብ ጉሮሮ ላይ ነው፡፡ የኾነው ኾኖ እርዳታው ሊቀጥል ይችላል፡፡ ይህ የሚኾነው ደግሞ ጥፋተኛው አካል ተለይቶ ተጠያቂ ሲኾንና ስለቀጣዩ ውይይት ከተካሄደ ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዐይነት ውርደት በእድሜዬ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ለእርዳታ የመጣ እህልን ከሕዝብ ነጥቆ መላክና ገንዘቡ የደረሰበት አለመታወቁ ከባድ ነው፡፡ ይህንን ሳስብ በጣም የሚያሳዝን ታሪክ ውስጥ እያለፍን መኾኑን እረዳለሁ፡፡
ግዮን፡- አንዳንድ ሰዎች መንግሥት ስንዴ መላኩን ትቶ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ያውል ይላሉ? ይህ አተያይ በእርሶ ዘንድ እንዴት ይታያል?
ክቡር፡- ስንዴን ኤክስፖርት ለማድረግ ብዙ መመቻቸት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ያዋጣል አያዋጣም የሚለው ጉዳይ ብቻ ሳይኾን ከብዙ ነገር አንጻር መታየት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የሚመረተው ምርት ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ የሚታሰብ ከኾነ ከሌሎች አምራቾች ጋር በዋጋ መጣጣሙ መታየት ይኖርበታል፡፡ የእኔ ያዋጣል ወይ ከሌሎች ጋር ይወዳደራል ወይ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ እኛ የምናመርተው ስንዴ ከዩክሬንና ራሽያ ሀገር ከሚመረተው ስንዴ በደረጃው ከፍ ያለ ነው፡፡ በዋጋ ለመሥራትም ያስቸግራል፤ ስለዚህ ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ ለሕዝቡ በእርዳታ የመጣውን ጠልፎ በመላክ እንደመንግሥት መደስኮር ተቀባይነት የለውም፡፡ ይሄ መሳለቂያ ያደርጋል፤ ይበልጥ ችግር የሚኾነው ደግሞ ለአሁን ብቻ ሳይኾን ለወደፊቱም ነው፡፡ በቀጣይ ጊዜ እንዲህ ዐይነት ችግር ቢመጣ የሚደርስ አይገኝም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ያጠፋው የኢትዮጵያን ሥም ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ በእርዳታ ብቻ መኖር የለባትም፡፡ እዚህ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ሁኔታዎችን በመመርመር ችግሮችን ቀናንሶ ከተረጂነት መውጣት ግድ ነው፡፡
ግዮን፡- አሁን ላይ እርዳታ እየጠበቀ ያለውን ሕዝብ ችግር መንግሥት በምን መልኩ ሊፈታው ይችላል?
ክቡር፡- መንግሥት ችግሩን መፍታት የሚችልበት መንገድ አለ፡፡ የመጀመሪያው ነገር የእርዳታ እህል ዘረፉ የተባሉ አካላትን በሙሉ ለቅሞ ለተጠያቂነት ማቅረብና በጥፋታቸው ልክ መቅጣት ይኖርበታል፡፡ ይህን አድርጎ ለጋስ ተቋማቱን ቢለምን ችግሩ ይቀረፋል፡፡ ከዚያ ውጭ አሜሪካን ቢነቅፍና ሕዝብ እያለቀብኝ ነው ብሎ ቢጣራ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
ግዮን፡- አሁን ያለውን የኑሮ ውድነት ሁኔታስ እንዴት ይታያል? የውድነት ደረጃውስ መቆም የሚችል ነው?
ክቡር፡- የኑሮ ውድነት በብዙ አቅጣጫ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ለገበያ የምናቀርበው ነገር በቂ አይደለም፡፡ በዚህም ከፈላጊው እያደገ መምጣት ጋር ተያይዞ ችግሩ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ አንዳንዴ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የኾነ ነገር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ለምሳሌ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ፣ እንደ ኮቪድ 19 ዐይነት ችግሮች እና የመሳሰሉት ሁኔታውን ሊያመጡትና ሊያባብሱት ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ገቢ ንግድ ምጣኔያችን ለኑሮ ውድነት ቀውስ ይዳርጋል፡፡ ለምሳሌ ከውጭ የምናመጣው ከምንልከው ከበለጠ ቀውሱን ይፈጥራል፡፡ ይሄ ማለት የዶላር ዋጋን የሚያሳጣ ነው፡፡ የብር ዋጋ እይደከመ በሄደ ቁጥር የኑሮ ግሽበት ይጨምራል፡፡ የሕዝብ ገቢ ባለበት እየረገጠ ግሽበቱ ከጨመረ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ለማስተካከል የውጪ ንግድን ማጠናከርና ምርትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ከውጭ የሚገቡ ነገሮችን መቀነስም ዋነኛው ቁልፍ ነው፡፡ መንግሥት ከአሁን በኋላ የሠራተኛ ቅጥር የለም እንዳለው ሁሉ ከአሁን በኋላ ውስኪ ከውጭ አይገባም ካለ ለውጥ ማምጣት ይችላል፡፡
ግዮን፡- አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት በምን መልኩ ሊስተካከል ይችላል?
ክቡር፡- ሊስተካከል የሚችለው የንግድ ኅብረተሰቡ ትርፍ ሊያመጣ የሚችል ሁኔታ አይቶ ገንዘቡን ማፍሰስ ሲችል ነው፡፡ አንድ ነጋዴ ድርጅት አቋቁሞ ትርፍን አልሞ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት፡፡ አሁን በሀገራችን ያለው ሁኔታ የፍርሐት ድባብ ነው፡፡ ፍርሐት ሲባል አሁን ያለው እንደሀገር አለመረጋጋት፣ ቀደም ሲል የነበረው ጦርነትና ቀጣይ ድባቡ እንዲሁም መሰል ችግሮች ኢንቨስትሩን ባለበት እንዲረግጥ አድርገውታል ማለት ነው፡፡
ግዮን፡- አሁን ያለውን ሀገራዊ አለመረጋጋትና የግጭት መበራከትስ እንዴት ማስቆም ይቻላል?
ክቡር፡- እንደሚመስለኝ መንግሥት ችግሩን የተረዳበት መንገድና እየሰጠ ያለው መፍትሔ የተሳሳተ ነው፡፡ በውይይትና በንግግር መፍታት የሚገባውን የፖለቲካ ችግር በኃይል ለመለወጥ ይሞክራል፡፡ የፖለቲካ ችግር በኃይል ሊለወጥ የሚችለው ለትንሽ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ባለፈው ጦርነት በውጤቱ ያየነው ይህን ነው፡፡ በጦርነት ማሸነፍ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ስላላደረሰ እንደገና ወደ ፖለቲካ ውስጥ ተገብቷል፡፡ ይህ ውይይት መቀጠል ካልቻለ እንደእኔ አተያይ ሩቅ ላያስኬደን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የሰላም ሂደቱን ሊመራ የሚችለው የደቡብ አፍሪካው ውይይት ብቻ ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ግን ውይይቱ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ውይይቱ እንደገና መቀጠል መሻሻልና መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ላይ መካሄድ ይኖርበታል፡፡ በአማራ ክልል እንደምናየው ለተነሱት ችግሮች ተወያይቶ መፍትሔ ከማምጣት ይልቅ በኃይል ለመፍታት ይጣራል፡፡ ይሄ አካሄድ ዘላቂ ሰላም አያመጣም፡፡ ዘላቂነት የሚኖረው ብዙኃኑ በሚፈልገው ደረጃ መሥራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማደግ የምትችለው ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ሀገሪቱ ያለፉትን 20 ዓመታት ትንሽ መሻሻልና ልማታዊ እድገት ማሳየት የቻለችው አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ነው፡፡
ግዮን፡- ሀገሪቱ ላይ አንድ ጠንካራ ፓርቲ አለመኖሩ ሀገሪቱን ለዚህ ዳርጓታል ይባላል፡፡ ይህ እንዴት ይታያል?
ክቡር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ፓርቲ የለም፡፡ ለሥሙ ፓርቲ አለ እየተባለ የሚኖረው አንድ ሰው ነው፡፡ እንኳን ተቃዋሚ ፓርቲ ገዢ ፓርቲም የለም፡፡ መወሰን የሚያስፈልግበት ቦታ ላይ መወሰን የሚችል የፓርቲ አቅም ያለው የለም፡፡ ነገር ግን አንድ ፓርቲ ውጤት የሚያመጣባቸው ሀገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የቻይናው ፓርቲ በሕዝብና በፓርቲው መካከል ማኅበራዊ ኮንትራት አለው፡፡ ሕዝቡን ሊያስተምር፣ ጤናውን ሊጠብቅ፣ ሥራ መስጠት፣ ኑሮውን ማሸነፍ፣ የደከመውን መርዳት፣ ወዘተ መንግሥት ኃላፊነት የወሰደባቸው ስምምነቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ዐይነት የፓርቲና የሕዝብ ስምምነት ሲኖር በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መንግሥት ይኖራል፡፡ መንግሥት በሀገሪቱ ላይ እድገት ያመጣል፡፡ ይኼ በቻይና የታየ ነው፤ ይህን በተለይ ምዕራባውያን ማውራት አይፈልጉም፡፡ እንደኛ ሀገር መድብለ ፓርቲ እያሉ ነገሮች እንዲጨማለቁ ነው የሚሹት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ፓርቲ ትክክለኛ ፓርቲ ነው ለማለት ግልጽነትና ተጠያቂነቱ እንደሀገር ለጠፋው ነገር ተጠያቂ ነው ወይ የሚለው መታየት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚነስትሩ በእሳቸው አነጋገር የፈለጉትን ልማት ማካሄድ ይችላሉ፡፡ ልማቱ ጥሩ ቢኾንም ምንም ዐይነት ተጠያቂነት ሊኖር አይገባም ባይ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ ትክክል አይደለም፡፡ ተጠያቂነት፣ ኃላፊነት፣ ግልጽነት የሌለበት ሀገር ወደፊት እድገትና ሰላም ይመጣል ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡
በሌላ በኩል እንደ ወልቃይት ያሉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ሁሉ መንግሥት የሚሰጣቸውን ማናቸውንም አገልግሎቶች ማግኘት አለባቸው፡፡ መንግሥት በጀት መስጠት አለበት፡፡ የአደራረሱ ጉዳይ አከራካሪ ቢኾንም መንግሥት እንደ መንግሥት ለሕዝብ በጀት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ አሁን ኃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም፤ በፖለቲካ ጉዳይ መወሰን አልቻለም፤ ይሄ የመንግሥትን ድክመት የሚያሳይ ነው፡፡ ለሕዝብ በጀት ተደራሽ ማድረግ ያልቻለ መንግሥት ትክክለኛ የመንግሥት አቅም አለው ማለት ከባድ ነው፡፡
ግዮን፡- በቀጣይ ይህን በጀት ማን ይልቀቅ ይላሉ? አማራ ክልል አሁን ባለበት ሁኔታ ይህን በጀት መስጠት ይችላል?
ክቡር፡- መንግሥት እንደመንግሥት አሁን ባለው አስተዳደር አልቻለም ቢባል እንኳ በሌላ ዘዴ ለሕዝቡ በጀቱን ማድረስ ይኖርበታል፡፡ የተለያየ ዘዴ ቀይሶ ለሕዝቡ በጀት መስጠት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የወልቃይት ሕዝብ በፓርላማውም ይሁን በሌላው ጉልበት ያለው ወኪል የለውም፡፡ የአማራ ክልል የኔ ክልል ነው ብሎ አምኖ ከተቀበለ በጀት ማስለቀቅ የማይችልበት አንዳች ነገር የለም፡፡ አማራ ክልል ማለት ቀላል ክልል ማለት አይደለም፤ እንደ ሐረር ወይም እንደሲዳማ አልያም እንደ ትግራይ የሚታይ ሳይኾን 40 ሚሊዮን ሰው የሚኖበት ክልል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በወልቃይት የበጀት ጉዳይ ዋናው ተጠያቂ የአማራ ክልል መንግሥት ነው፡፡ በጀቱን ማድረስ ያለበት የክልሉ መንግሥት ነው፡፡
ግዮን፡- የአቶ ግርማ ዋቄን ከአየር መንገድ ኃላፊነት መነሳት እንዴት ይታያል?
ክቡር፡ አቶ ግርማ ዋቄ ለአየር መንገዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግለሰብ ናቸው፡፡ ተቀባይነታቸውም፣ በሥራቸው ያላቸው ልህቀትም ከፍ ያለ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አልፈው ለሌላ ሀገር የሚሠራ የእውቀት ልዕልና ያላቸው ናቸው፡፡ ከኃላፊነት አነሳሳቸው ዝም ብለን ስናየው ማስጠንቀቂያ ያልተሰጠበትና ዘፈቀዳዊ ይመስላል፡፡ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ስም ያላቸው ግለሰብን ማንሳት አየር መንገዱን ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ከአየር መንገዱ ጋር አብረው የሚሠሩ አጋር የውጭ አካላት በአቶ ግርማ ዋቄ መኖር ውስጥ የሚያገኙት ልዕልና አለ፡፡ እንዲህ ዐይነት ግለሰብ ያለ ምክንያት ሲነሳ አብረው የሚሠሩ አካላትም በጋራ እየሠራን እንቀጥል ወይስ አንቀጥል የሚል ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ አሠራሩ ከቢዝነስ አንጻር ትክክል አይደለም፡፡ ዋናው ግን አቶ ግርማን ማንሳት ለምን አስፈለገ የሚለው ነው፡፡ አቶ ግርማ በዚህ ዙሪያ እንደሚሉት ከኾነ የሃሳብ አለመግባባት ነው፡፡ በሃሳብ ያልተግባቡበት ጉዳይ ምንድን ነው የሚለውና አሁን የተሾሙት ተተኪ አቶ ግርማ የተቃወሙትን ሃሳብ አቀንቃኝ ከኾኑ አየር መንገዱን ወዴት ይወስዱታል የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ አየር መንገዱን እየቆራረጡ ሊሸጡት ነው፡፡ አንዴ ካርጎውን ይሸጡታል፤ በመቀጠል ትምህርት ቤቱን፤ እያለ እያለ ወደ ግል ይዞራል፡፡
ዞሮ ዞሮ ይሄ ትዕዛዝ የሚመጣው ከምዕራባውያን የፋይናንስ ተቋማት ነው፡፡ “ሸጣችሁ እዳችሁን ከፍላችሁ ልማታችሁን አምጡ” የሚለው ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘው በብልጽግና መንግሥት ነው፡፡ እኔ የሚያሳዝነኝ እንዲህ ዐይነት ትርፍ ያለው ሥራ እያከናወነ ያለን ተቋም ምን ጎደለው ተብሎ እንደሚሸጥ ብቻ ነው፡፡ ስንት ሰው ሌት ተቀን ለዓመታት የለፋበትን አንስቶ ለሌላ መሥጠት ለምን አስፈለገ? የአይዲዮሎጂ ጉዳይ አድርገው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን የትኛው አይዲዮሎጂ ነው ትርፍ እያመጣ ያለ ተቋምን ወደ ግል ይዙር የሚለው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ ግን በዚህ ሽያጭ ኮሚሽን የሚያገኙ የተወሰኑ ሰዎች አሉ፡፡ እንዲህ ዐይነት ምክር የሚሰጡ የውጭ አማካሪዎች አሉ፡፡ እራሱ መንግሥትም ተቋሙን እንደተረከበው ሁሉ ማሳለፍ አለበት፡፡ ይሄ መንግሥት ተቋሙን ተረክቦ ነው ያገኘው እንጅ አቋቁሞት ወይም መሥርቶት አይደለም፡፡ የሕዝብን ሀብት ማሳደግ ነው እንጅ አሳልፎ ለሌላ መስጠት አሳፋሪ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንደሚያዝኑ አያጠራጥርም፡፡ እየተደረገ ያለውን ሥራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቀበለዋል ብዬ ማመን ይቸግረኛል፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ክቡር፡- በመጀመሪያ የፖለቲካ ችግሮችን ለመቅረፍ ከጦርነትና ግጭት ወጥቶ በውይይት መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ግጭትና ጦርነት መጥፋት ይኖርብታል፡፡ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ እልባት መስጠት ለሀገሪቱም ለሕዝቧም ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡ መለወጥ ያለባቸው ነገሮች ከሕገ መንግሥት ጀምሮ መቀየር ይኖባቸዋል፡፡ ለሕዝብ የቆመ መንግሥት ሕዝብ የሚፈልገውን ያደርጋል፡፡ ወደ ንግዱ ሕብረተሰብና ኢንቨስትመንቱ ስንመጣ ደግሞ መጀመሪያ ሰላም መስፈን አለበት፡፡ ሌላው ድንገት ተነስቶ ሕዝብ ባልተወያየበት ሁኔታ ሲወሰን እድገት አያመጣም፡፡ ስለዚህ የመንግሥታት ፖሊሲ አወጣጥ ግልጽነት ያለበትና በውይይት የተደገፈ መኾን ይኖርበታል፡፡
ሌላው ከማክሮ ኢኮኖሚ አንጻር ነገሮችን ስንመለከት ወደሀገር ውስጥ የሚገባውና የሚወጣው ወይም የሚላከው ለዓመታት መጣጣም ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ወጪና ገቢ የተጣጣመበት ወቅት በጣም አጭር ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ይህ የወጪ ገቢ ንግድ መጣጣም የሚያስፈልገው የምንዛሬውን ደረጃ ተመጣጣኝ ለማድረግ ነው፡፡ ዕቃ ልከን የምናመጣው ዶላር ለምናስገባው እቃ መግዣ ካልበቃን የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ አይቀሬ ነው፡፡ ዶላር ለማግኘት ብድር ይኬዳል፡፡ ብድር ሲከፈል ደግሞ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡ አሁን በሀገራችን ያለው ችግርም ከዕዳ ክፍያ ምግብና ማዳበሪያ ከማቅረብ አኳያ ያለ ነው፡፡ የእዳው መጠን ትልቅነት ሳይኾን የመክፈል አቅማችን ዝቅተኛ መኾኑ የቀውስ ደረጃችንን ያብሰዋል፡፡ ያለንን ንብረት ሸጠን ወደባርነት የምንሄድበትን መንገድ እራሳችንን እያመቻቸን ነው፡፡
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሠግናለን፡፡