አለመማርና ስቃይ

Date:

ሠሎሞን ለማ ገመቹ.

‹‹ያጤ ዮሐንስ ነገር እጅግ ያሳዝናል፡፡ እጅግ ያስለቅሳል፡፡ … ለዘውድ ሳስተው ሠራዊት ለማብዛት፣ ጦር ለማጠንከር ብለው፤ የሚአበሉት እህል፣ የሚሰጡት ገንዘብ፣ የሚሸልሙት መሣሪያ፣ የሚጋለብ ፈረስ፣ የሚጫን በቅሎ ለሠራዊታቸው ቢያጡ፤ ደሀ በደሉ፡፡ ተሰሪ አገቡ፡፡… አገር ዘረፉ፡፡ አገር አጠፉ፡፡ ደሀ አስለቀሱ፡፡ ተትግሬ በቀር ሠራዊታቸው ድፍን በጌምድርን (ጎንደርን) መደመዱን አጠፋ፡፡ የትግሬ ወታደር በሐምሌ ዝርዝር አሳጨደ፡፡ በበጌምድር (በጎንደር) ደሀ ግፍ ሠራበት፡፡ የትግሬ ወታደር ‹በዚያ ጉሮሮ በሚፍቅ ቋንቋው ኩሪ ኩሪ› እያለ እርጉዝ አስወረዳት፡፡ ዕመጫት ጡቷ ደረቀባት፡፡ ቄሱ ተቤክሲያን፣ ገበሬው ተዱሩ፣ ነጋዴው ተመደብሩ ተሸሽጎ በትግሬ ወታደር (በድርጊቱ) አለቀሰ፡፡ ተማለለ፡፡ የጎጃም ደሀ ሦስት ወር ሙሉ በትግሬ ሰው ሲያለቅስ ኑሮ፤ ‹አጤ ዮሐንስ ከደርቡሽ ጋር ሊዋጉ መተማ ወረዱ› በተባለ ጊዜ እንዲህ ብሎ የርግማን ቃል ተናገረ፡-

‹ዘንድሮ ንጉሡ ደህና ቢመለሱ፤

ምንኛ ጎልድፏል ጎጃሜ ምላሱ›

ይሄን ሁሉ አፄ ዮሐንስ አወቁት? ያውቁት ነበር? ዛሬ እንዲህ እርሳቸው ተረሱ፡፡ ያደረጉት ነገር ግን እስተመቸውም አይረሳም፡፡…›› /1901 ዓ.ም ዳግማዊ አጤ ምኒልክ – በአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዘብሔረ ዘጌ. ከገጽ 54-55./

ከፍ ሲል በጥቅስ የተቀመጠው ዛሬ በይፋ የተደገመ፣ የክብር፣ የደም፣ የአጥንት፣ የሕይወት፣ የንብረት… ከባድና መራር ዋጋ የከፈልንበት ታሪክ ቀዳሚ ነፀብራቅ ነው፡፡ እኛ ግን… እንደዚህ ከተሰነደም ይሁን በአፈ-ታሪክ ከዘመን ወደ ዘመን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከተሸጋገረ ዕውነት በአግባቡ የመማር አቅማችን ኮስማና ይመስለኛል፡፡ አንዳንዴም የነበረ በጎነታችንን እንደ ጥንጣን እና ነቀዝ ሲበሉና ሲያነቅዙ… ከኖሩት፤ እንደ ንጉሡ የማጎንበስ፣ እንደ አታሞው የማርገድ፣ ወዲህም ለጥ-  ወዲያም ለጥ ብሎ የመኖር ልማድና ወደ ባሕልነት ማደግ ከቻሉት እነዚሁኑ መሰል ባሕሪያት መድኃኒት አለማግኘት የተነሳ፤ አሁን ካለንበት ማኅበረሰባዊም ይሁን ብሔራዊ የስጋትና የሰቀቀን ደረጃ ላይ በመድረሳችን… ከታሪክ ክፉ ደግ ያለመማር ድንዛዜን ገንዘብ ያደረግን ሆኖ ይሰማኛል፡፡

ዕውነተኛው የተሰነደ፣ የተኖረ፣ በአንደበት ቅብብሎሽ፣ በሰሚ ስሞሽ… ከዚህኛው ዘመን ላይ ከደረሰው ታሪክ የሰው ልጅ ሊያተርፍ የሚገባው፤ የጎበጠውን ለማቅናት፣ ሥህተቱን ለማረም፣ የደፈረሰውን ለማጥራት፤ ስቃይና ሰቆቃውን፣ ግፍና በደሉን፣ የትዕቢትና የዕብሪት ተግባሩን፣ የበቀልና የወር-ተረኝነት ጅራፍ ግርፊያን፤ ዝርፊያን፣ ቅሚያን፣ የማንአለብኝነትን ኢ-ግብረ-ገባዊ ድርጊቶች ማስቆም፣ ፈፅሞ እንዳይደጋገሙ የሚደረግበትን እና ከዚህም ሰናይ የሐሣብ መንደርደሪያ በመነሳት ብዙኃኑን ጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉ ትልሞችን መተለም የሚችልበትን ዕውቀት ነበር፡፡

እንደ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ሁሉ፤ በቀረበው ትላንት ‹‹በግፈኛ ዐመሉ የተነሳ ከማዕከል ተገፍቷል›› በተባለው ‹‹የሕወሓት ጥቁር ጣሊያን›› አገዛዝ ዘመን ተጽፎ አደባባይ በዋለው የአንዳርጌ መስፍን ሽፈራው ‹‹ዓርበኛና ባንዳ›› መፅሐፍም ይሁን፤ ከዚያም ቀደም ብሎ ግደይ ባሕሪ ሹም ‹‹አሞራ›› በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃው መፅሐፍና በሌሎችም ጠቀሜታቸው ጉልህ በሚሆን ድርሳናት፣ የፖለቲካና የታሪክ፣የኢትዮጵያዊውን ማኅበረሰብ ማንነትና ምንነት… በሚዳስሱ የጥናትና የምርምር ሥራዎች ወዘተ. የኋላ ወይም የነበረና የኖረ ስሙና ግብሩ በሙሉ፤ እጅግ ያደፈና የቆሸሸ ስለሆነው የሕወሓት ፀረ-ኢትዮጵያውያን እና ፀረ-ኢትዮጵያ ዓላማና ተግባር፣ በማንኛውም ጥሩ ሊባል የማይችል ድርጊት ሚዛን ሲመዘን ‹‹ዝቅ ሲል ከርስ፤ ከፍ ሲል ፈርስ!›› ስለመሆኑ፤ ምን ያልተነገረ፣ ምን ያልተፃፈ፤ ሊመጣ ያለውንና የመጣውን ሰይጣናዊ ድርጊት በተመለከተ ምንስ ያልቀረበ ማሳሰቢያ ነበር?

በጭካኔና በአረመኔያዊ ተግባራቸው እጅግ የከፉትና የጣሊያንን ፋሽስት ሠራዊት ድርጊት ከእጥፍ በላይ በግልጽ በአደባባይ ከራያ እስከ ደብረ-ሲና፣ ከተከዜ ወልቃይት እስከ ደቡብ ጎንደር ጋሳይ፣ በመላው የወሎና በአብዛኛው የአፋር ምድር ‹‹የእኛው›› የሚባሉት ጥቁር ጣሊያኖች፤ የሰማነውን፣ ያየነውንና ቃላቶች ሊገልጹት የማይቻላቸውን ድርጊቶች በሙሉ ዛሬ ሊፈፅሙ የቻሉት፤ ታሪክ ሊያስተምረን ከሚችለው ትምህርት እኛ ኢትዮጵያውያን ልንማር የምንችልበትን ዕድል ለራሳችን በመንፈጋችን ጭምር መሆኑን ለመካድ የምንደፍር አይመስለኝም፡፡

በርግጥ ከታሪክ መጥፎ ገጽታዎች መማር፤ የአስተዋይና የአብሮነትን ገንቢ፣ አናጭና አበልጻጊ ግብረ-ገባዊ እሴቶችን ያለመተውና የማዳበር ጽኑ ፍላጎት ያለውና ለተግባራዊነታቸውም የማይዋልል አቋም ሊኖረው የሚችል ማኅበረሰብ ጸጋ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያዊ ዜጋ የዚህ ጸጋ ባለቤት አይደለም ወይ?›› የሚለው ጥያቄ መከተሉ አይቀርም፡፡ የጥያቄው መልስ ‹‹የጸጋው ባለቤት ነው›› የሚል ከሆነ ደግሞ ‹‹ይህን የመሰለውን ጸጋ እንዴት ሳይጠቀምበት ወይም ፍሬ እንዲያፈራ ለማድረግ ጥረት ሳያደርግ ቀረ? ጥረት አድርጎስ ከሆነ በምን ምክንያት ነው ፍሬ ሳያፈራ የቀረው?…›› የሚሉትና ሌሎችም መሰል ጥያቄዎች መዥጎድጎዳቸው የሚታመን ይሆናል፡፡ ተጨባጩ ዕውነት ግን አይደለም ከታሪክ ጸዓዳና ፀሊም ገጽታዎች ለመማር የመፈለጉ ተነሳሽነት ዕንጭጭ ከመሆኑም ባሻገር፤ ሚዛናዊ ዕይታ ያላቸውንም ይሁን ወደፊት ብሔራዊ ይዘት ሊኖራቸው የሚገባቸውን ታሪካዊ ሠነዶች ከማዘጋጀት አኳያ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ንዑሳን ታሪኮችን በትዕግስት የመመልከት  ፈቃድ ‹‹ይበል!›› በሚያሰኝ ደረጃ አለመስተዋሉ ይመስለኛል፡፡  

ያም ሆነ አልሆነ… ታሪክ ከሚነግረን፣ የታሪክ ገጾች ከሚያስነብቡን፣ ታሪክ ሊያስገነዝበንና በይበልጥ ሊያተጋን ከሚችለው ዘርፈ-ብዙ ሐቅ፣ ያለፉ ነገሮች… ልንማር ወይ ልናተርፍ ባለመቻላችን፤ ሲዖልንና ገሃነምን የሚመኙ ባንዶችና ጡት-ነካሾች… ቢያንስ በዘመነ-ዮሐንስና በዘመነ-ጣሊያን ‹‹ሆኖ ነበር…›› የተባለውንና የሰው ልጅ ሊከተለው ይገባል ከሚባለው የግብረ-ገብነት ሥርዓት ፍፁም ያፈነገጠ፣ ‹‹ሰይጣንም ቢሆን ሊሠራውና ሊያስበው አይችልም›› የተባለለትን ሰቅጣጭና አስነዋሪ ተግባር በሙሉ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ በሙሉ ይኸው ፈፅመውታል፡፡ የፈፀሙትም ድርጊት በሙሉ በአድራጊዎቹ ጉዶች በኩል ‹‹ኧረ ከናካቴው ሊታሰብ አይችልም!…›› ተብሎ ማስተባበያ የተሰነዘረበት አልነበረም፡፡ ይልቁንም የሆነው ሁሉ ሊሆን እንደሚችል አንድ ጊዜ አይደለም በጥቂት አስተዋይ የኢትዮጵያ ልጆች አንደበት ባለፉት አርባ ምናምን ዓመታት ተደጋግሞ ሲነገር፣ በደማቅ ብዕሮቻቸውም ሲፃፍ የነበረ ነው፡፡ ‹‹ከታሪክ የማይማሩ፤ መጥፎን ነገር ሊደግሙት ይገደዳሉ›› የሚለው አስተማሪ አባባል ተግባራዊ ፍቺስ ጡት-ነካሾቹና የታሪክ አተላዎቹ ዘረኛ ባንዳ ወያኔዎች ከፈፀሙብን የአረመኔያዊ ተግባሮች ሁሉ ድምር ወጤት የተለየ ምንስ ትርጉም ይኖረዋል?   

 ታዋቂው የፍልስፍና መምህርና የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር ጠና ደዎ ‹‹ሰው፣ ግብረ-ገብና ሥነ-ምግባር የዘመናችን ቁልፍ ጉዳዮች›› በተሰኘው ዳጎስ ያለ መፅሐፋቸው /አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬስ፤ 2008 ዓ.ም ዕትም/ በገጽ 49. ከሥነ-ምግባርና ከግብረ-ገብ መርሆዎች አንዱ ‹‹የስቃይ ወይም የማሰቃየት ድርጊትን በሰው ላይ ከመፈፀም መታቀብ›› ነው ይሉናል፡፡ ይህንንም አባባላቸውን ሲያብራሩ፡- ‹‹በዓለም ላይ በአንድ በኩል የሚያስደስቱና በሌላ በኩል የሚያሰቃዩ ነገሮች አሉ፡፡ ጤናማ የሆነ ማንኛውም ሰው የሚያስደስተውን እንጂ ለስቃይ የሚዳርገውን ነገር አይፈልግም፡፡ ሰውን ለስቃይ የሚዳርጉ በርካታ የሰው ልጅ ድርጊቶች ግን አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ውሸት፣ ስርቆት፣ ቅናት፣ ምቀኝነት፣ ሐሜት፣ ስም ማጥፋት፣ ፍትሕን መንፈግ፣ መብትን መጋፋት፣ ማታለል ወይም ማጭበርበር፣ ዕምነት ማጉደል፣ ክህደት መፈፀም፣ ቃል-ኪዳን ማፍረስ ዋንኞቹ ናቸው፡፡ ሰው ምንጊዜም ስቃይን ምርጫው አያደርግም፡፡ ምክንያቱም ስቃይ የአካልና የመንፈስ ጉዳት ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ከስቃይ ነፃ ለመሆን ያለው ፍላጎትና ምርጫ ሊከበርለት እንጂ መሰቃየት የማይፈልግ ሰው በሌላ ሰው ላይ ስቃይ ማድረስ የለበትም›› ይላሉ፡፡ ነገር ግን በታሪክ የባሕሪ ስጦታው፣ በዓመታት ውስጥ በተጨባጭ የተስተዋለ ግብሩ የሰውን ልጅ ማሰቃየትና ከዚሁም ዓይነቱ ዕኩይ ድርጊት ማትረፍ መሆኑ የተመሰከረለት ጡት-ነካሹ ሕወሓት… ወረራ በፈፀመባቸው የኢትዮጵያ መሬቶች ሁሉ፤ ከፍ ሲል በጥቅስ የተገለጹትንና እያንዳንዶቹን የስቃይ ተግባሮች በሙሉ አንዳች ሳያጓድል… ‹‹ለመንግሥትነት በቅቷል›› ከተባለበትም ይሁን በደደቢት በረሃ ከነ አጥፊ መርዙ ከተፈለፈለበት ሰዓት ጀምሮ ይኸው ወደ መረጠው ሲዖልና ገሃነም… በሃገር አቀፍ የተባበረ ክንድ እየተሸኘ በሚገኝበት ጊዜ ፈፅሟል፡፡ ወደፊትም ስሙ ዕንኳን ዳግመኛ እንዳይነሳ ተደርጎ… ወደማይመለስበት ከርሰ-መቃብር እስካልወረደና የኢትዮጵያ አኩራፊና ሻምላ አምላኪ… ፖለቲከኞች ከነጭፍሮቻቸው ከመሰል ዕኩይ የዘረኝነትና ፀረ-ግብረ-ገባዊነት የጥፋት ጎዳና መመለስ እስካልቻሉ፣ ኢትዮጵያውያንም ከታሪክ እስካልተማሩ ድረስ፤ የሆነውም ይሁን ሊሆን የሚችለው፤ ከሆነው የተለየና አዲስ ነገር ነው ሊባል አይችልም፡፡…

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...