
ሂሩት በቀለ መስከረም 28/1935 ከእናቷ ተናኜወርቅ መኮንን እና ከአባቷ መቶ አለቃ በቀለ ክንፌ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ሥሙ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተወለደች። እድሜዋ ለትምህርት ሲደርስም ቀበና ሚሲዩን ትምህርት ቤት በመግባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለች ሲሆን፤ በትምህርት ቤት በነበረችበት ወቅትም ለክፍል ጓደኞቿና ለሰፈሯ ልጆች አዘውትራ ስለምታንጎራጉር፤ ይህን ችሎታዋን የተመለከቱት ጓደኞቿም ወደ ሙዚቃው ዓለም እንድትገባ በተደጋጋሚ ያበረታቷትና ይገፏፏት ነበር።
በዚህ መሰረት በ1951 ከቅርብ ጓደኛዋ ጋር በመሆን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል በመሄድ በድምፃዊነት ተፈትና ለመቀጠር በቃች፡፡ ከዛም በማስከተል ብዙም ሳትቆይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተጫወተችው “የሐር ሸረሪት” በተሰኘው ዜማ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆትንና ተቀባይነትን አገኘች። በ1952 ከምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ወደ ፖሊስ ሰራዊት ኦርኬስትራ በመዛወር በቋሚነት የሙዚቃ ክፍል አባል ሆና የተቀጠረችው ሂሩት፤ በፖሊስ ሠራዊቱ ለ35 ዓመት ያህል አገልግላለች። ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር ሴት ድምፃዊያን መካከል አንዷ የሆነችው ሂሩት በቀለ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿም በሕዝብ ዘንድ እጅግ የተወደዱ እና ለበርካታ ሴት ድምፃዊያንም መነሻ የሆኑ ናቸው።
ሂሩት ከተጫወተቻቸው አያሌ ሙዚቃዎቿ መካከል እንደ ህዝብ መዝሙር በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውና ከትንሽ እስከ ትልቅ በአገር ፍቅር ስሜት እስከአሁን የሚያዜመው “ኢትዮጵያ” የተሰኘው ሙዚቃ ይገኝበታል። በ35 ዓመታት የሙዚቃ ቆይታዋ “ሕይወት እንደሸክላ” እና “ኢትዮጵያን” ጨምሮ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን ለሕዝብ ጆሮ ያደረሰችው ሂሩት በቀለ፤ ከእነዚህም መካከል ከ38 በላይ ሙዚቃዎቿ በሸክላ የታተሙ ሲሆን፤ እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ 14 ካሴቶችንም ለአድማጮች አበርክታለች።
ሂሩት በቀለ እናት አገሯ ጥሪ ባቀረበችላት ቦታ ኹሉ በመገኘት የዜግነት ግዴታዋን በብቃት ከመወጣቷም በላይ፤ ኮንጎ ለዘመተው ለኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦር ቦታው ድረስ በመሄድ ሰራዊቱን የሚያነቃቁ ተወዳጅ ሙዚቃዎቿን አቅርባለች። በደርግ ዘመንም ራሽያን ጨምሮ በተለያዮ በርካታ የሶሻሊስት አገራት በመዘዋወር የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጾ አበርክታለች።
ከዚህም ባሻገር በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ወራሪ ኃይልና በሰሜን ኢትዮጵያ ደግሞ ከሻቢያ ጋር በተደረገው ጦርነት ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ጦሩ መሀል በመገኘት ወኔ ቀስቃሽ ሙዚቃዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ ግዳጇን መወጣቷን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ህልፈተ ህይወቷን ተከትሎ ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ አስታውቋል።
ሂሩት በቀለ በሙዚቃው ዘርፍ ለእናት አገሯ ላበረከተችው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር በርካታ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክተውላታል። ሂሩት በሙዚቃ ዓለም ውስጥ በቆየችባቸው አያሌ ዓመታት ከማህሙድ አህመድ፣ ከዓለማየሁ እሸቴ፣ ከቴዎድሮስ ታደሰ፣ ከመልካሙ ተበጀ፣ ከታደለ በቀለ፣ ከመስፍን ኃይሌ፣ ከካሳሁን ገርማሞ እና ከሌሎች ስመጥር ድምፃዊያን ጋር በመሆን ስራዎቿን ለህዝብ ሲታቀርብ ቆይታለች።
ከ1987 በኋላም እራሷን ከሙዚቃ ዓለም ያገለለችው ሂሩት ከዘፈን ዓለም ወጥታ ወደ መንፈሳዊ ዓለም በመግባትና፤ የተለያዩ የመዝሙር አልበሞችን በመስራት ለአድማጮች አቅርባለች።
ሂሩት በቀለ ባደረባት ህመም ምክንያት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለረጅም ጊዜ ህክምናዋን ስትከታተል ቆይታ፤ ግንቦት 4/2015 በተወለደች በ80 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር ሴት አርቲስቶች መካከል አንዷና ተወዳጅዋ ድምፃዊት፣ የግጥም እና የዜማ ደራሲ የነበረቸው፤ እንዲሁም ከ80ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ሕይወቷ እስካለፈበት ዕለት ድረስ በዘማሪነት አገልግሎት የተለያዩ የመዝሙር አልበሞችን በመስራት የምትታወቀው የዘማሪት ሂሩት በቀለ ሥርዓተ ቀብር በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈፅሟል። የቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይም የሂሩት በቀለ ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶች፣ የሙያ አጋሮች እንዲሁም በርካታ ቁጥር ያላቸው የጥበብ አፍቃሪያን ተገኝተውበታል። ሂሩት በቀለ የ7 ልጆች እናት፣ የ10 ልጆች አያት እና የ7 ልጆች ቅድመ አያት ነበረች፡፡
ሒሩት በቀለ እንደ ዑም ኩልቱም!
ከ‹‹ጠመንጃ እና ሙዚቃ›› መጽሐፍ የተወሰደ
“ድምጿ ስትዘፍን የመልአክ ድምፅ ይመስላል፡፡ የድምጿ ስሌት በአዕምሮ ገብቶ ሰውነትን አርክቶ ወደ ወዲያኛው ዓለም ተጉዞ ሲመለስ የህሊና ዕረፍትን ይሰጣል፤ ሲሠራ የደከመን አዕምሮ ያድሳል፡፡ ሁለተኛዋ ዑም ኩልቱም ማለት ይች ናት፡፡”
የግብፁ አልጀኻሙሪያ ጋዜጣ ጸሐፊ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ መጥቶ ሒሩት በቀለን በመድረክ ላይ ከተመለከተ በኃላ በዓረበኛ ለመላው ዓለም ያሰራጨው ጽሑፍ ነው፡፡
የሒሩት ሙዚቀኛ መሆን ድንገቴ ነው:: በ1952 ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ደጃፍ የተገኘችው ጓደኛዋ ስትፈተን ለማበረታታት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በግቢ ብቻዋን ስትንጎራደድ የተመለከቷት የምድር ጦር ሰዎች አንችም ለምን ገብትሽ አትሞክሪም ብለው በቀልድ መልክ ነገሯት፡፡ ብቻ ከመቆም በሚል ወደ ፈተናው ክፍል ገባች፡፡ ተራዋ ሲደርስም በልጅነቷ በያገር ፍቅር ማኅበር እንደተመለከተቻቸው ድምፃዊያን ረጋ ብላ ማዜም ጀመረች፡፡ ውጤቱ ሲገለፅ ጓደኛዋን ለማስፈተን ምድር ጦር ኦርኬስትራ ጎራ ያለችው ሒሩት ማለፏ ተነገራት፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ዑም ኩልቱም ሰለዚህ ትዝታዋ ሌላም ታሪክ ስታወራ ተሰምታ ታውቃለች:: ሙዚቀኛ እንድሆን ሲሳይ የተባለ ጎረቤቴ ውለታ አለብኝ እያለች ነው ::የቅጥሯ ሁኔታ ይህን ቢመስልም እሷ ግን በኇለኛው ዘመኗ ሲሳይ የተባለን ሰው ስም ታነሳለች:: ቅጥሩም በእሱ ግፊት ነው ትላለች:: ምናልባት ካለፈች በኇላ ያባረታታት ሳይሆን አይቀርም ::
በአጭር ጊዜ ውስጥ ሻለቃ አሽኔ ኃይሌ ለሒሩት በቀለ “የሐር ሸረሪት” የተባለውን ዜማ ደርሶም በ1953 የዘመን መለወጫ በዓል ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ጋር መድረኩ ላይ ተሰየመች፡፡ ነገር ግን ሒሩት ከዐይናፋርነቷ ብዛት “የሐር ሸረሪት” የተባለውን የመጀመሪያ ሙዚቃዋን ለመጨረስ አቅም አጣች፡፡ ከመኸል ሙዚቃውንም አቋርጣ መሬት መሬት እያየች ወደ መድረኩ ጀርባ አመራች፡፡ ሙዚቀኞቹ አስቀድሞ ያውቁ የነበረ ይመስል በሒሩት መድረክ ጥሎ መውረድ ሳይደናገጡ በመሣሪያ ብቻ የሐር ሸረሪትን መጫወታቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አሰገደች ካሳ ወደ መድረክ ወጥታ “የሐር ሸረሪት” የተባለውን ሙዚቃ ተጫውታ ለመጨረስ በቃች፡፡
ሒሩት ከዚህ አጋጣሚ በኃላ በብዙ ምክር ዐይን አፋርነቷ ቢቀንስም ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ጋር ግን ለመዝለቅ አልቻለችም፡፡ ወደ ፖሊስ የሙዚቃ ክፍል ለማዛወር በተሠራው ሤራ በእኩለ ሌሊት ከካምፕ ተጠርታ በወንጀል እንደምትፈለግ ተነግሯት ያላሰበችው የፖሊስ ሙዚቃ ክፍል ደጃፍ ደረሰች፡፡ ከሒሩት በቀለ አስገራሚ የፖሊስ ቅጥር ጀርባ ያሉት ተስፋዬ አበበ በዚህ መንገድ ፖሊስ ኦርኬስትራ ያመጣናትን ድምፃዊት የምድር ጦር ኃላፊዎች በተገኙበት የዘመን መለወጫ መድረክ ላይ ማቆም ከባድ ነበር ይላሉ፡፡
ግን ፈርተው አልተውትም፡፡ ግራ እና ቀኝ በፖሊስ ታጅባ ወደ መድረክ በፍጥነት አመራች፡፡ በወንጀል ሠርታለች ሰበብ ከምድር ጦር ኦርኬስትራ የተዘረፈችውን ድምፃዊ ያዩት የጦር ሰራዊቱ ኦርኬስታራ አለቆች ግን ብዙም እንደተፈራው ንትርክ ውስጥ አልገቡም፡፡ ይልቁኑም እንደወደደችው ትሁን አሉ፡፡
ለስለስ ባሉት ዜማዎች የተመልካችን ቀልብ የምትገዛው ሒሩት ከምድር ጦር ኦርኬስትራ ሰዎች ጋር በዚህ ተግባሯ ብዙ ውዝግብ ውስጥ ባትገባም ያላሰበችው ጉዳይ ግን ከፍተኛ የራስ ምታት ሆኖባት ነበር፡፡ በዘመን መለወጫ በዓል በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር መገኘት የሚያዘወትረው የአዲስ አበባ ሕዝብ የሒሩትንም እናት ቀልብ ስቦ በእዚያ አዳራሽ እንዲገኙ ምክንያት ሆነ፡፡
በወቅቱ ልጃቸውን በመድረክ የተመለከቱት እናት አስቀድመው ዓይናቸውን ማመን ቢሳናቸውም ከጥቂት ደቂቃ በኃላ ግን ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው አዳራሹን በዕንባቸው እያረጠቡ ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ የሆነውን ያላወቀችው ሒሩት ማምሻውን ወደ ቤት ስትሄድ ቤተሰቡ በሙሉ እየተላቀሰ እንደነበር ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር በነበራት ቀደምት ቃለ መጠይቅ ተናግራለች፡፡ ቤተሰቡን ለማፅናናት መሞከሯም በከፊል የተሳካላት ቢመስልም ከሌላው ዱብዳ ግን አላዳናትም፡፡ አያቷ ሲያርፉ አዝማሪ የሆነችው ሒሩት ምንም ሀብታቸው ላይ እንዳትካፈል አደራ አሉ፡፡
በተስፋዬ አበበ እና ግርማ ኃይሌ ድርሰቶች ደምቃ በ1950ዎቹ አጋማሽ ከፍ ያለ ዝናን ያተረፈችው ሒሩት በቀለ የዓለማየሁ እሸቴን ፖሊስ መግባት ተከትሎ ተወዳጅ ዜማዎቿን በቅብብል እንድታቀርብ ዕድል አገኘች፡፡ “የሁለት ፍቅረኞች ውይይት” የተሰኘ ዜማቸውም በጊዜው ከፍተኛ ተወዳጅነት ለማትረፍ ቻለ፡፡ ከመስፍን ኃይሌ ጋር ያዜመቼው “ተይ እንረዳዳ” የተባለ ሙዚቃዋም ቀስ በቀስ በከተማው መነጋጋሪያ ሆነ ፡፡
በ1953 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ማግስት “ጭር አለች ጎጆዬ” የተባለውን ዜማ ያቀረበችው ሒሩት ለጄነራል መንግሥቱ ነዋይ ባለቤት ያዜመችው ነው እየተባለ መወራቱ አልቀረም ፡፡ የግጥሙ ጸሐፊ ተስፋዬ አበበ ግን ከመንፈንቅለ መንግሥቱ ጋር የተገናኘ ሥራ ነው ተብሎ በወቅቱ በስፋት ይወራ እንደነበር ቢያስታውሱም “ጭር አለች ጎጃዬ” የፖለቲካ ጉዳይ የለበትም ይላሉ፡፡
ከፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር የስኬትን ማማ የረገጠችው የለስላሳ ሙዚቃዋ ፈርጥ ጥቂት ሥራዎቿን በሸክላ ሕትመት በፊሊፕስ አሳታሚ በኩል ለአድማጭ አቅርባለች፡፡ ከእነዚህ መካከል በግርማ ኃይሌ የተደረሰው “ከሆነ ኩነኔ”፣ በተስፋዬ አበበ የግጥም ድርሰቱ የቀረበው “የትኛው ነው ደስታ” እንዲሁም ራሷ ግጥም እና ዜማ የደረሰችለት “ዝማም ነህ ወይ” ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የፖሊሲ ሙዚቃ ክፍል ባልደረባው ንጉሤ ዳኘ “አንተንስ ለትዳር”፣ “እውነተኛ ፍቅር” እና “ደስ የሚያሰኝ” በተባሉት ሙዚቃዎች ላይ ተሳትፏል፡፡
እውቁ የስፖርት ጋዜጠኛ ሰሎሞን ተሰማ “ባህላችን ይበቃል” የተባለውን ሙዚቃ ግጥም ሲደርስ ተስፋዬ ለማም ለወራት በፖሊስ ኦርኬስትራ በቆየበት ወቅት “የሞት አበቃ” የተባለ ድርሰት አበርክቶላታል፡፡ አምኃ አሳታሚም የሕትመት ጊዜያቸው ያልታወቁ አራት የሒሩት ሙዚቃዎችን ለገበያ አቅርቧል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከዓለማየሁ ጋር በቅብብል የሠሯቸው “ተመለሰ” እና “ተይ ግድየለሽም” ይጠቀሳሉ፡፡ ሒሩት በግሏም በአምኃ አሳታሚ በኩል “አልሞከርኩም ነበር” እና “እርሱ ነው መሰለኝ “የተባሉትን ዜማዎች አቅርባላች፡፡
በ1950ዎቹ አጋማሽ ይቀርብባት በነበረው ትችት ከሙዚቃ ለመራቅ አስባ የነበረችው ሒሩት በቀለ አላስችል ብሏት ለዘመናት በያዘችው መንገድ ገፍታበታለች፡፡ የኦርኬስትራዎች ጊዜ እያከተመ የባንዶች ዘመን ሲያንሰራራም ዳህላክ እና ሮሃ ባንድ ጋር በመጣመር በ1970፣1973፣1974፣በ1975፣በ1976፣ በ1977፣1978 እንዲሁም በ1980 ከፍ ያለ ተቀበያነት ያላቸውን ካሴቶች ለአድማጭ አድርሳለች፡፡ ከእነዚህ መካከል በ1976 በፖሊስ ኦርኬስትራ ዝናን ያተረፉት የዜማና ግጥም ደራሲያን ተስፋዬ አበበ፣አያሌው አበበ፣ ንጉሴ ደኜ እና ካሳሁን ግርማሞ(የቴዲ አፍሮ አባት )የተጣመሩበት “ድማም ቆንጆ”፣ “አንተ እንደምን አለህ” እና “ኧረ እንዴት ነህ” የተባሉ ሙዚቃዎችን የያዘው አልበም ዛሬም ልዩ ምልክቷ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡
* ዑም ኩልቱም በግብጽ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ እንደ ምልክት የምትታይ ታላቅ አቀንቃኝና ተዋናይ ናት፡፡ በፈረንጆቹ 1898 የተወለደችው ዑም በአገሬው ሕዝብ የግብጽ ድምጽ በሚል ትታወቃለች፡፡ ሕልፈቷም በፈረንጆቹ 1975 ነበር::