በውጭ ምንዛሪ ወቅታዊ አቅርቦት ላይ የተሰጠ መረጃ
አዋሽ ባንክ የደንበኞቹን ፍላጎት በሟሟላትና ብሎም በሀገራችን ኢኮኖሚ እድገት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኝ ባንክ መሆኑ ይታወቃል።
ባንካችን በሃገራችን ውስጥ የሚታየውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቀረፍና ግልጽነት እንዲፈጠር የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል።
ለአብነት ለመጥቀስ ያህል ባንኩ እ.ኤ.አ. ከ01/01/2025 እስከ 31/03/2025 ባሉ ሦስት ወራት ብቻ ቁጥሩ ከ2200 በላይ የሆኑ ደንበኞችን ያስተናገደ ሲሆን በድምሩ ከ498 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለደንበኞች እንደ ጥያቄአቸው አቅርቧል።
በተጨማሪም ባንኩ ለተለያዩ የሀገር ውስጥ ባንኮች ከ100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ዕገዛ አድርጓል።
ባንኩ ይህን የውጭ ምንዛሪ ድልድል በሚያደርግበት ጊዜ መንግስት የፍራንኮ ቫሉታ ስርዓት ያቆመ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ሀገራችን የሚገቡ ስልታዊ ሸቀጦች (Strategic Commodities) እጥረት እንዳይከሰት በማሰብ በሦስት ወራት ብቻ ለዘይት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ፣ ለነዳጅ 79 ሚሊዮን ዶላር፣ ለስኳር 20 ሚሊዮን ዶላር፣ ለሩዝ 11 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሰጠ ሲሆን የትምህርትና የህክምና የመሳሰሉት ክፍያዎችን ቅድሚያ በመስጠት የውጭ ምንዛሪ ድልድል አድርጓል።
በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየ15 ቀኑ የውጭ ምንዛሪ በጨረታ ለባንኮች እያቀረበ በመሆኑና የወጪ ንግድ እና ወደ ሀገር ውስጥ የሚላክ ሃዋላ በጣም እየተሻሻለ ከመሆኑ የተነሳ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም አዋሽ ባንክ የደንበኞቹን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማርካት የአቅርቦት ችግር የማያጋጥመው ሲሆን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ የሚያመቻች መሆኑን እንገልፃለን።
አሁንም ባንኩ በእጁ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ በሰፊው እያቀረበ የሚቀጥል መሆኑን በአክብሮት እናሳውቃለን።
አዋሽ ባንክ
