የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የት ላይ ቆሟል?
ይፋዊ ከኾኑ መረጃዎች እንደምንረዳው፣ በ2019 በኒያሚ በይፋ የተጀመረው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) 54 የሚኾኑ የአፍሪካ መንግሥታት ተስማምተው የተፈራረሙበት ሲኾን ከ40 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በየሀገሮቻቸው አጽድቀውታል ብዬ አምናለሁ። በተጨማሪም በኒያሚው ጉባኤ ላይ 30 የሚኾኑት አባል ሀገራት በአህጉሩ የሰዎችን በነፃ የመንቀሳቀስ እና መኖሪያን የመመሥረት መብቶች ፕሮቶኮልን ፈርመዋል።
እስካሁን በሸቀጥ ንግድ፣ በንግድ አገልግሎቶች እና በችግር አፈታት ዙርያ የመጀመሪያው ምዕራፍ ድርድር ተደርጎ ተጠናቋል። የሁለተኛ ምዕራፍ ድርድሮች ማለትም በኢንቨስትመንት፣ በፖሊሲ ውድድር፣ በአእምሯዊ ንብረት መብቶች እና በበይነመረብ ንግድ (e-commerce) ደግሞ አሁን ላይ በመካሄድ ላይ ይገኛል። የኾነው ኾኖ በጥር 1 ቀን 2021 በንግድ ፕሮቶኮል የንግድ ልውውጥ መጀመር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ ትልቅ ምዕራፍ ነው። ይኼ ግን ያለቀለት ሳይኾን ሂደት ነው፡፡ የዚህ የንግድ ስምምነት በተሳካ ሁኔታ ተግባራዊ መሆን ረጅም ጊዜን የሚወስድ፣ መንገዱም አቀበት ያለው ነው፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ለአፍሪካ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና 54 ሀገራትን፣ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ የኾነውን ሕዝባቸውን እና ከ3 ትሪሊየን ዶላር በላይ የኾውን የሀገር ውስጥ ምርት አቀናጅቶ የተነሣ ነው። ይህ ለአፍሪካ ጥሩ መነሻ ሲሆን፣ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናም አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን የተገለለ ሚና ለመቅረፍ እና የአፍሪካን ድምጽ በዋና ዋና መድረኮች ላይ በተሻለ ሁኔታ እንዲሰማ ለማድረግ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል። በአህጉራዊ ደረጃ፣ በቀጣናዊ ውሕደት ላይ የሚገጥሙትን በርካታ ተግዳሮቶች ለማሸነፍ እና በአፍሪካ ውስጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግም ይረዳል። ንግድን እንደ ዕድገት ሞተር በመጠቀም የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ን ጨምሮ ለወንዶች እና ለሴቶች የሥራ እድል በመፍጠር ለኢንዱስትሪ መብዛት ዕድሎችን ማሳደግም ይችላል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ግን በተጨባጭ እየሰራ ነው ማለት እንችላለን?
የአፍሪካ ሀገራት በአህጉራዊ የነጻ ንግድ ስምምነት እና ከቀረጥ ነጻ የሸቀጦች እና አገልግሎቶች ግብይት መሠረት ገበያቸውን የከፈቱት ጥር 1 ቀን ነው። በመኾኑም የንግድ እንቅስቃሴው በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሥር በይፋ ተከፍቷል። የሙከራ ግብይቱ አሁን እየተካሄደ ያለውም ከእያንዳንዱ ንዑስ ቀጣና በተመረጡ 7 ወይም 8 አገሮች ውስጥ ነው። አባል ሀገራቱም ላደጉ ሀገራት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ ላላደጉ ሀገራት ደግሞ በዐሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ 90 በመቶ የሚኾኑት ዕቃዎች ላይ ያለው ታሪፍ እንዲቀር ይጠበቃሉ። ሌሎች ወሳኝነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ 7 በመቶ ዕቃዎች ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ የሚያገኙ ሲኾን፣ ቀሪ 3 በመቶ ደግሞ ገለልተኛ ዝርዝር ውስጥ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። ብዙ ሀገራት እነዚህን ጉዳዮች አጠናቅቀው ለንግድ ተቋማቱ አሳውቀዋል፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ግን የታሪፍ ፕሮፖዛሉን እስካሁን አላቀረቡም።
እናም፣ ከፍ ብሎ እንደተገለጸው ሥራው ከተጀመረ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ብቻ ከመኾኑ አንጻር በተጨባጭ መሬት ላይ ገና አልወረደም፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ተግዳሮቶችን በተመለከተ የጥበቃ ዋስትና፣ የጉምሩክ እና የንግድ አሳላጭ ቢሮክራሲዎች፣ ከአንዱ ንዑስ ቀጣና ገበያ ወደ ሌላው ያለው የምንዛሪ ተመን አሠራር፣ ደካማ የሎጅስቲክስ እና የቴሌኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማትን መጥቀስ እንችላለን። ከዚህ ባሻገር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሁለት ታላላቅ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ የመጀመሪያው አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከትላልቅ እና የፋይናንስ ብልጫ ካላቸው ኩባንያዎች ጋር መወዳደር መቻል አለመቻላቸው ጉዳይ ነው። ምክንያቱም ይህ አህጉራዊ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትናንሽ የሀገር ውስጥ ባለሚናዎችን በትልልቅ ኮርፖሬሽኖች እንዳይጠፉ ለመከላከል የተቀመጡ እንቅፋቶችን ሳይቀር ይሰብራል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ስምምነቱ ታሪፎችን ማስቀረት መቻሉ፣ አነስተኛ እና ደካማ ኢኮኖሚ ያላቸውን የአፍሪካ ሀገራት ከጉምሩክ ቀረጥ የሚያገኙትን ከፍተኛ ገቢ የሚያጠፋ መኾኑ ነው። ይህ በመንግሥት ገቢ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገመት አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥታት ከሸቀጦች ሽያጭ ወደሌሎች አፍሪካ ሀገራት የሚላከው የወጪ ንግድ ገቢን በመሳብ ማቃለል ካልቻሉ ውጥንቅጥ መከሰቱ አይቀሬ ይኾናል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና እንዴት ትጠቀማለች?
ኢትዮጵያ ቢያንስ ለውጭ ገበያ የምታቀርበውን ምርት ማሳደግ ይኖርባታል፡፡ ይህ ደግሞ ዝም ብሎ ሊመጣ አይችልም። ጊዜ ይወስዳል። ለዚህ መፍትሔው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በመፈረም የምርት ችግሮችን በአንድ አፍሪካ ገበያ ለመፍታት እና የውጭ ባለሃብቶችን በአንድ የአፍሪካ ገበያ ማዕቀፍ ለመቅረፍ መሞከር ነው። ምክንያቱም ሰፊ ገበያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የሚኾነውን የንግድ ዐውድ ያሻሽላል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጣም አስፈላጊ የሆነውን ካፒታል እና ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ያደርጋል።
ብዙ ሥራ ፈጣሪዎች ስለ ስምምነቱ ጥቅሞች እና ጉዳቶች አሁንም መረዳቱ የላቸውም፡፡ እኛ እንደ ፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ወደ ሥራ መግባት በሚያስገኘው ጥቅም ላይ አህጉራዊ ዘመቻ እንጀምራለን፡፡ በዚህም የንግድ ከባቢን እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል፣ ብሎም በኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ጥሬ እቃዎችን በመጨመር እና የሥራ ዕድሎችን በመክፈት እንዴት እንደሚግዝ መረጃ እንሰጣለን። ባጭሩ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የኢትዮጵያ ወይም የአፍሪካ ኩባንያዎች ወደ አዲስ ገበያ እንዲቀላቀሉ ዕድሉን ይሰጣል። ይህ የደንበኞቻቸውን መሠረት በማስፋት ወደ አዲስ ምርቶች እና አገልግሎቶች እንዲያመሩ ያደርጋል፡፡ ይህም በፈጠራ ሥራ ላይ ኢንቨስት ማድረግን አዋጭ መስክ ያደርገዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ውሱንነቶች ምንድን ናቸው?
መልከ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በአንድ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ማስቀመጥ ከባድ ነው። ለምሳሌ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የአፍሪካ ምርት በግብፅ፣ በናይጄሪያ እና በደቡብ አፍሪካ የሚበረከት ሲሆን፣ ስድስት የሚኾኑት የአፍሪካ ደሴት ሀገራት ድርሻ ግን 1 በመቶ ብቻ ነው። በተጨማሪም፣ ትልልቅ ኢኮኖሚ ያላቸው ጠንካራ ኩባንያዎች ርካሽ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ ይችላሉ። ይህም የአገር ውስጥ አምራቾች ለውጭ አቅራቢዎች ሽያጭ እንዲያጡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ምክንያቱም በስምምነቱ መሠረት ከውጭ በሚገቡ ዕቃዎች ላይ የተጣለው ታሪፍ ስለሚቀንስ የምርታቸውን ዋጋ ሊቀንስ ይችላልና ነው። ለማንኛውም ይኽ ነጻ የንግድ ቀጣና ደካማውን የአፍሪካን ኢኮኖሚ የማይደግፈው የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ለመፍጠር ነው። ስለዚህ ማንኛውም ኢኮኖሚ ወደ ኋላ እንዳይቀር ተሳታፊ ሀገራት በሁሉም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የስምምነት ምዕራፎች ላይ አንድነት መኖሩን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም በስምምነቱ ሥር ያሉ ሀገራት የሰራተኛ ማኅበራትን ሥጋት የሚፈቱ እና የሀገር ውስጥ የንግድ ድርጅቶችን ሳያጠፉ ጤናማ ውድድርን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎችን ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል።
የአፍሪካ የግሉ ዘርፍ ማኅበራት የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለማስፋፋት በጋራ እየሰሩ ነው?
እኛ እንደ ፓን አፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት፣ ከሀገር ውስጥ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ማህበራት ምክር ቤቶች ጋር በቅርበት እንደመሥራታችን፣ በአህጉሪቱ የአፍሪካን የንግድ ድርጅቶች የሚያገለግል ትልቁ የንግድ ድርጅት ነን እንላለን። በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉ አባሎቻችን አማካኝነት የግል ሴክተሩን በማንቀሳቀስ ወደዚያ መድረሳችንን ማረጋገጥ እንችላለን። ነገር ግን በመሬት ላይ ያሉ አባሎቻችን በአቅም ረገድ የተለያዩ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ንግድ ምክር ቤቶች ለአባላቶቻቸው የሚሰጡትን አገልግሎት ለማስተካከል እና ውጤታማ የንግዱ ዘርፍ ደጀን ሆነው እንዲቀጥሉ “ቻምበር አፍሪካ ኮኔክሽን” የተሰኘ አዲስ መርሃ ግብር የጀመርነው። “ቻምበር አፍሪካ ኮኔክሽን” በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የተፋጠነውን የዲጂታል አሠራር በማስቀጠል በቀጣይ በየንግድ ምክር ቤቶች አማካኝነት የንግድ ድርጅቶች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙና ይኽም ደግሞ እንዴት እንደሚረዳቸው የሚዳስስ ነው። ይህ ደግሞ ለአባሎቻችን እንዲሁም ለአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አዳዲስ የንግድ መሥፈርቶችን ለማዘመን እና ውጤታማነታቸውንም ለማሳደግ ጥሩ ማዕቀፍ ይኾናል።
