ከባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ የእስራኤል መንግሥት በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ግዛት ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት ለመመከት እንዲሁም፤ ሉዓላዊነቷንና ሕዝቧን በሙሉ አቅሟ ለመጠበቅ ኢራን ዝግጁ ናት ሲሉ በኢትዮጵያ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ አምባሳደር አሊ አክባር ረዛኢ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሩ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ “ኢራን ከእስራኤል ጥቃት ራሷን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቷን ትጠቀማለች” በማለት ተናግረዋል፡፡
“እሰራኤል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተርን አንቀፅ 2 (4)ን በመጣስ በሉዓላዊቷ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ላይ ጥቃት ፈፅማለች” ያሉት አምባሳድር ረዛኢ፤ “ኢራንም በመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 52 መሰረት ራሷን የመከላከል መብት አላት” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
“በዚህም እኛ ጦርነቱን አልጀመርነውም፤ ነገር ግን ሕዝባችንና ሀገራችንን ሙሉ አቅማችንን በመጠቀም ለመጠበቅ ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡
አምባሳደር ረዛኢ አክለውም፤ “የእስራኤል ፅዮናውያን አገዛዝ የኢራንን ሰላማዊ የኒውክሌር ተቋማትን የጥቃት ኢላማ አድርጓል” ያሉ ሲሆን፤ “በኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት መፈጸም በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም ለሁሉም ግልጽ ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገርም የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኃላፊ ዛሬ ባደረጉት ፍተሻ፤ እስራኤል ‘ኢራን የኒውክሌር ቦንብ ልትሰራ ነው’ ስትል ያቀረበችውን ክስ ሀሰት እንደሆነም ማረጋገጣቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር ረዛኢ በመግለጫቸው “ሆስፒታሎች፣ ብሄራዊ የሬድዮና ቴሌቪዥን ሕንጻ፣ የመኖሪያ ቤቶችና ንጹኃን በእስራኤል ጥቃቶች ኢላማ ተደርገዋል” ያሉ ሲሆን፤ ይህም የሦስት ወር ሕጻናትንና ነፍሰ ጡር ሴቶችን ጨምሮ በርካቶች ተገድለዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም “የእስራኤል አገዛዝ ጥቃት የሰነዘረው ኢራንና አሜሪካ በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ለአምስት ዙር ያክል ድርድር እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው” ሲሉ የተናገሩት አምባሳደሩ፤ “ይህም ማን ሰላም ፈላጊ ማን ጸብ አጫሪ ነው የሚለውን በግልጽ ያሳያል” ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
(አሐዱ ሬዲዮ)
