በክቡር ገና
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በገደል አፋፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ጉዳዩን ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከማህበራዊ ሕይወት አንጻር ብናየው በሁለም ዘርፍ ሀገሪቱ በቋፍ ላይ ነው ያለችው፡፡ ሀገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ሁለንተናዊ ኪሳራ፣ ረሀብ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ እዳ፣ 31.4 በመቶ የደረሰ የዋጋ ግሽበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የመንግሥትና የግል መዋዕለ ንዋይ መመናመን ተጋርጦባታል፡፡
ይህ ሁሉ አበሳ የደረሰው ግን በድንገት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ መከራ የብሔርተኛ ልሂቃን የሌት ተቀን ትጋት ውጤት ነው፡፡ የብሔር ልሂቃንና የነሱን ፈለግ የተከተሉ የብሔር ፖለቲከኞች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሁሉንም ነገር በጠባብ የብሔር መነጽር ስለሚያዩት የሀገሪቱ ችግር ከድጡ ወደ ማጡ እየተሸጋገረ ነው፡፡
ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ጂቡቲ ሄጄ ከአንድ ጂቡቲያዊ የቀድሞ ወዳጄ ጋር ተገናኘን፡፡ ከዚህ በፊት ከዚህ የንግድ ሰው ጋር የምንጨዋወተው ስለንግድና ኢንቨስትመንት ነበር፡፡ አሁን ግን ጨዋታችን ተቀይሮ ‹‹እናንተ ኢትዮጵያውያን ሓላፊነት የሚሰማችሁ ሰዎች አይደላችሁም፡፡ ኢትዮጵያውያን ምን እየሆናችሁ ነው? ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት አደረጋችሁ፡፡ አሁን ደግሞ በአማራ አካባቢ ከመጀመሪያ የባሰ ግዙፍ ቀውስ እየፈጠራችሁ ነው፡፡ እኮ ለምን?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
አዎን ‹‹ለምን?›› ሁላችንም ምላሽ ልናፈላልግት የሚገባን የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡
በእኔ አመለካከት ኢትዮጵያን ሊበታትኗት የሚችሉ አራት አደጋዎች ተጋርጠውባታል ባይ ነኝ፡፡ ለነዚህ አራት የሕልውና አደጋዎች መፍትሔ ማፈላለግ ከሁሉም ዜጎችና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ሁሉ ይጠበቃል፡፡
- ሥልጣን በአንድ ወገን ተጠቃሎ መያዙ
የኢትዮጵያን ፖለቲካ በወፍ በረር ለሚከታተል ሰው እንኳ ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት ተንሰራፍቶና ሥር ሰዶ የኖረው በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባሕልና በታሪክ ተከፋፍሎ የዘለቀው አገዛዝ አሁንም ተጠናክሮና ተባብሶ መቀጠሉን ልብ ይላል፡፡ በመርኅ ደረጃ በራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ብቻ የሚመሩት የብልጽግና ፓርቲ ልሂቃን በተለያዩ ብሔረሰቦች መካከል ፍርሀትና አለመተማመን በማስረጽ የጋራ የኾነውን ኢትዮጵያዊ ማንነትን በመሸርሸር ረገድ ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ በአንድ ላይ ጸንታ የምትኖረው በኃይልና ጉልበት ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ ከታሪክ አንጻር ትክክል ያልሆነ፣ ከፖለቲካም አኳያ ሓላፊነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው፡፡ እንዲያው አይበለውና የኢትዮጵያ ጉዳይ ከማይጠገንበት ደረጃ ደርሶ ኢትዮጵያ የምትበታተን ከሆነ በዋነኝነት ለዚህ ተጠያቂው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥና የፖለቲካ ሥልጣን ቀድሞ ከነበረበት ከትግራይ ሊሂቃን ወጥቶ በአብዛኛው በኦሮሞ ልሂቃን እጅ መግባቱ ነው፡፡ አብዛኛው የፖለቲካ ሥልጣን በኦሮሞ ልሂቃን እጅ ተጠቅልሎ መግባቱ የአማራ ብሔርተኝነትን በእጅጉ ያቀጣጠለው ሲሆን የአማራ ብሔርተኝነት በዚህ ፍጥነት መቀጣጠሉ ደግሞ ምን ሊያመጣ እንደሚችል ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አስተዳደር በአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ መድረሻውን ሳያውቅ ያለእቅድና ዓላማ በደመነፍስ ከሚሔድ ባቡር ጋር ይመሳሰላል፡፡ ይህ መንግሥት ልብ ገዝቶ፣ ጆሮውን ለሕዝብ ሠጥቶና ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ድጋፍ አግኝቶ በጊዜ ቆራጥ እርምጃ ካልወሰደ በራሱ ብቻ ተግባራዊ የሚያደርገው ምንም ዐይነት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሀገሪቱን ከመንኮታኮት አያድናትም፡፡
ቀድሞውኑ ሀገሪቱ አሁን ከገባችበት የመከራ አረንቋ እንዴት ልትወድቅ ቻለች ብለን የጠየቅን እንደሆነ በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው ጦርነት፣ በኦሮሚያ በተነሳው ግጭት፣ እንደ ቋያ እሳት በተዛመተውና በተንሰራፋው ሌብነት፣ በነዚህ ገፊ ምክንያቶች በተከሰተውና መቆጣጠር ባልተቻለው የኑሮ ወድነት እንዲሁም በቅርቡ በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭትና ያለመረጋጋት ምክንያት እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ የዜጎች አበሳና መከራ የተፈጠረው አራት ኪሎ በሚገኘው የወቅቱ መንግሥት በመኾኑ ጉዳዩ ከብልጽግና ፓርቲ አመራር ራስ አይወርድም፡፡
- ተጠያቂነት ያለመኖርና መላቅጥ የሌለው የብሔር ፌዴራሊዝም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሀገሪቱ ለውጥ እንደሚኖር፣ ዴሞክራሲ እንደሚሰፍን፣ ፍቅር እንደሚያብብ፣ ፓርኮች እንደሚገነቡና ብልጽግና እንደሚረጋገጥ ቃል ገብተውልን ነበር፡፡ ቃል ከገቡልን ውስጥ የማንክደው የፓርኮች መገንባትን ብቻ ነው፡፡ ሲጀምሩ እራሳቸውን እንደ አዘማኝ፣ እንደ ለውጥ መሪ፣ አልፎ ተርፎም እንደ ፈላስፋም ተመስለው ቀረቡልን፡፡ መሪውን የሚያምነውም የዋሁ ሕዝባችንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ሊያወጡ ከእግዜር የተላኩ መሪ ናቸው እስከ ማለት ደረሰ፡፡
የኾነው ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ የተጠያቂነት ጉዳይ ብናነሳ እንኳ ዶ/ር ዐቢይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን የሚያዩት ፍጹም ተጠያቂነት የሌለበት የማይከሰስ የማይወቀስ ተቋም አድርገው ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከናወኑና የፓርክ ግንባታዎች፣ የወንዝ ዳር ፕሮጀክቶች፣ የቤተመንግሥት እድሳቶችና ‹‹ገበታ ለሀገር›› የተሰኙት ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደላቸው ናቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤትና በብልጽግና ፓርቲ ተግባራዊ የሚደረጉ ውሳኔዎች በቂ ጥናትና ምክክር ተደርጎባቸው ሥራ ላይ የሚውሉ አይደለም፡፡ ይህ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጓደል ደግሞ ከላይ እስከ ታች ባሉ የአስተዳደር እርከኖችና በመንግሥት ተቋማት የሚስተዋል ነው፡፡
ወደ ብሔር ፌዴራሊዝም ሥርዓታችን ስንመጣ ደግሞ የሥርዓቱ መሠረት የኾነው ሕገ-መንግሥት ለብሔር ብሔረሰቦች እንጂ ለግለሰቦችና ለዜጎች እውቅና አይሰጥም፡፡ ለይስሙላ የግለሰቦችና የዜጎች መብት ይከበራል ቢልም በገሐዱ ዓለም የሚታይ አይደለም፡፡ ትኩረቱ ሁሉ ቡድን መብት ላይ ነው፡፡ ስለዚህም ሰዎች ወደውም ሆነው ተገደው ‹‹ዘመድ ከዘመዱ…›› እንደሚባለው በጎጥ እንዲሰባሰቡ ሆኗል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የብሔር ጉዳይ የሁሉ ነገር አልፋና ኦሜጋ ሆኗል፡፡ ስለዚህም ማንኛውንም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር ለመፍታት በብሔር መነጽር መመልከትና በብሔር ሚዛን መዳኘት ግዴታ ኾኗል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ያለችን በርካታ ብሔረሰቦችን ያቀፈች ሀገር መምራትና ማስተዳደር ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ፡፡ ለአንዱ እናት ለሌላው የእንጀራ እናት መኾን ግን አብሮነታችንን ክፉኛ እንደሚጎዳ ልብ ይሏል፡፡ አሁን የሚታየው በፌዴራልና በክልሎች መካከል ያለው የጌታና የሎሌ ግንኙነት፣ በባለሥልጣናትና በሕዝቡ መካከል ያለው ያለመተማመን በመንግሥትና በተለያዩ የአስተዳደር እንከኖች እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝቡ መካከል የትብብር መንፈስ ሳይሆን የመራራቅና የባተዋርነት መንፈስ እንዲሰፍን አድርጓል፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የመግባባትና የትብብር መንፈስ ከሌሌ መንግሥት የለየለት አምባገነን እንደሚሆንና ሕዝብን በኃይል ወደ መግዛት እንደሚሸጋገር የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡
- የተንሰራፋውና ሥር የሰደደው ሌብነት
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸረ ሙስና አጀንዳ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ይህ ሙስና በሚል ገራገር አገላለጽ የሚነገረውን ሌብነት አንታገሰውም ሲሉ በሌላ ወቅት ደግሞ ‹‹የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ ይሁን›› በሚል መንፈስ ነገሩን ውሃ ይቸልሱበታል፡፡ እናም ጠቅላዩ ሌብነትን ለመታገል እስካሁን ያደረጉት ጥረት ምንም ፍሬ ያላፈራና እዚህ ግባ የሚባልም አይደለም፡፡
ስለዚህም ሌብነት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ውስጥ የሚገባ ማጣፈጫ ከመሆኑም በላይ ሌብነት ያልገባበት የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት የለም፡፡ የተንሰራፋውና ሥር የሰደደው ሌብነት በሀገሪቱ ረሀብን፣ ሥራ አጥነትን ብሎም ድህነትን አስከትሏል፡፡ በሁሉም ዘርፍ የገነነው ሌብነት ዜጎች ሰርቶ የመለወጥ ጥረታቸውን በማቀጨጭ፣ የኢኮኖሚ እድገትና ልማትን በማሰናከል፣ ባላቸውና በሌላቸው መካከል ያለውን ልዩነት በእጅጉ በማስፋት ዜጎችን ‹‹የድሀ ድሀ›› ወደሚል አዘቅት እያወረዳቸው ይገኛል፡፡
ሌብነት አገራችንን ያወድማል ስንል ወደፊት እንደሚከሰትና እንደ ማንቂያ ደወል የምናሳስበው ሳይሆን በአሁኑ ሰዓት አገራችንን እያወደመ ያለ ነቀርሳ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በቅርቡ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ የእርዳታ እህል ዘረፋ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ በግጭትና በተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው በሰቆቃ ከሚኖሩ ዜጎች አፍ የእርዳታ እህል ዘርፎ ወደ ውጪ ኤክስፖርት የሚያደርግ ነፍሰ በላ ባለሥልጣን ያፈራች ሀገር ኾናለች – ኢትዮጵያ፡፡ ይህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንደ ዜጋ አንገት የሚያስደፋና ከሌብነትም ባለፈ በሰው ሕይወት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ከመኾኑም በላይ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ ገጽታ የሚያጠለሽ ቅስም ሰባሪ ተግባር ነው፡፡
- የአየር ንብረት ለውጥና የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ጉዳት
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው ተጽእኖ ከዚህ መለስ የሚባል አይደለም፡፡ በሀገራችን የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው የተፈጥሮ አደጋ የመሠረተ ልማት አውታሮች፣ ግብርና፣ የመኖሪያ አካባቢዎችና የግል ንብረቶች፣ የሕዝብ ጤና እንዲሁም ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል፡፡ ከ80 አስከ 85 በመቶ የሚኾነው ሕዝብ በግብርናና በከብት እርባታ በሚተዳደርባት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለው የተፈጥሮ አደጋ አውዳሚ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ በሚከሰተው የተፈጥሮ አደጋ በተለይም የገጠሩ ነዋሪ የምግብ እጥረት፣ የጤና መታወክ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ እጥረት፣ ሥራ አጥነት፣ መፈናቀልና ስደት ይደርስበታል፡፡ አደጋው ቀድሞውኑ ድሀ የነበሩትን የድሀ ድሀ ያደርጋቸዋል፡፡ እናም የአየር ንብረት ለውጥ ብዙኃኑን የሚጎዳ ስለሆነ የሀገር ጉዳት ነውና መላ ካልተባለ ጉዳቱ ሀገር አውዳሚ ነው፡፡
ነገሩን እናጠቃለውና የተከበረው መንግሥታችን እንዲህ አፍጥጠውና አግጠው ከፊታችን ለተጋረጡት ሀገር ሀፍራሽ አደጋዎች እየወሰደ ያለው እርምጃ ምንድነው? ጦርነት ማካሄድ? አዲስ ታክስ መጣል? አዲስ ብድር ማፈላለግ? ችግኝ መትከል? የኤሌክትሪክ መኪና መንዳት? ኢትዮጵያን ለቻይና መሸጥ? ወይስ የእርዳታ ስንዴን ኤክስፖርት ማድረግ?
መንግሥት ገደል አፋፍ ላይ የቆመችው ሀገራችንን ለመታደግ እስካሁን ከገጠማት አደጋ ጋር የሚመጣጠን መፍትሔ እርምጃ እወሰደ ባለመሆኑ ዜጎች መላ ልንመታ ይገባል፡፡ እስቲ መላ ምቱ!
