የኬንያና የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምንና ሳፋሪኮምን በጋራ ለመደገፍ መስማማታቸውን ለአንድ ቀን ይፋዊ ሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታ እንዲሻሻል ኬንያና ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጹት ፕሬዚዳንት ሩቶ፤ “ለጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ትስስር፣ ዲጂታል ዕድገትና የጋራ ብልጽግና ባለን የጋራ ርዕይ ላይ ተመስርተን ለቀጣናው መረጋጋት፣ ለንግግርና ለአፍሪካዊ መፍትሔዎች ያለንን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠናል” ብለዋል።
በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቆሙት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ ሁለቱ መሪዎች ከተነጋገሩባቸው ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንደኛው ኢትዮ ቴሌኮምንና ሳፋሪኮምን በጋራ ለመደገፍ መስማማታቸው መሆኑንም አመልክተዋል።
ሁለቱ ተቋማት በቀጠናዊ ገበያው ውስጥ ያሉትን ስትራቴጀካዊ የጋራ ኢንቨስትመንት ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንት ሩቶ፤ ኢትዮ ቴሌኮምና ሳፋሪኮም ከኬንያና ከኢትዮጵያ መንግስታት ሙሉ ድጋፍ በሚያገኙባቸው ጉዳዮች ላይ መስማማታቸውን በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
