ግዙፉ መንግስታዊዉ የቴሌኮም አቅራቢ የሆነዉ ኢትዮ ቴሌኮም በትላንትናው ዕለት ሚያዚያ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. “ዘመን ገበያ” የተሰኘ ሀገር አቀፍ የዲጂታል የገበያ ቦታን በይፋ ካስጀመረ በኋላ፣ ከዚህ ፕላትፎርም ጋር ለመተባበር ፍላጎት ላላቸው የንግድ ድርጅቶች እና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጭዎች ጥሪ አቅርቧል ።
ኩባንያው ከዘመን ገበያ ጋር ለመስራት ባቀረበው ጥሪ መሰረት፣ ከ42 በላይ የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች እና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ሰጭዎች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ።
“ዘመን ገበያ” የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠን፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ ዲጂታል አካታችነትን በማስፋፋትና የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
ተቋሙ እንዳስታወቀው በቀጣይም የኢትዮጵያን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከሚፈልጉ አካላት ጋር ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።
ይህ የዲጂታል መድረክ ለአምራቾችና ለአገልግሎት አቅራቢዎች ሰፊ የገበያ ተደራሽነትን እንደሚያረጋግጥ፣ የሥራ ማስኬጃ ወጪን እንደሚቀንስ፣ ከደንበኞች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለመገንባት እንደሚያግዝ እንዲሁም የዲጂታል ክፍያ መፍትሄዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅሞችን ይሰጣል ተብሏል።
ለሸማቾች በበኩሉ ሰፋ ያሉ የምርትና የአገልግሎት አማራጮችን፣ ምቹና ተደራሽ ግብይትን እንዲሁም ተወዳዳሪ ዋጋዎችን ያቀርባል። ለሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ደግሞ ሰፊ ገበያ እንዲያገኙና በአገልግሎት አፈጻጸማቸው ላይ መሻሻል እንዲያመጡ ያግዛል ሲል ኢትዮቴሌኮም ገልጿል።
