በፓሲፊክ ውቅያኖስ ላይ እየተከሰተ ያለው የኤል ኒኖ ክስተት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት ሁሉ የበለጠ ጠንካራ ሊሆን እንደሚችል የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የአየር ሁኔታ እና የአየር ንብረት አገልግሎት (ሜት ኦፊስ) አስጠንቅቋል።
ይህ ሃይለኛ የተፈጥሮ የአየር ንብረት ክስተት የአለም አቀፍ የሙቀት መጠንን የሚጨምር ሲሆን፤ለከባድ የአየር ንብረት መዛባቶች ያለውን ስጋትም ከፍ ያደርገዋል።
ሜት ኦፊስ እንደገለጸው፤ ይህ ተፈጥሯዊ ክስተት ከሰው ሰራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በመደራረብ 2027ን በአለም አቀፍ ደረጃ በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ የበለጠ ‹‹ሞቃታማ ›› ዓመት የመሆን እድሉን ይጨምረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም የሚታዩ የአየር ንብረት ሁኔታዎች በክስተቱ መጎዳታቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዩ ይገኛሉ፤ በሕንድ ዝቅተኛ የዝናብ መጠን መመዝገቡ እና በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል የሃሪኬን አውሎ ንፋስ እንቅስቃሴ መቀነሱ ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።
በተጨማሪም ኤል ኒኖ በዩናይትድ ኪንግደም በኩል ለዝናባማ እና አውሎ ንፋሳማ የበጋ ወቅት መንስኤ ሊሆን እንደሚችልና በረጅም ጊዜ ትንበያዎች ላይ ያልተረጋጋ የአየር ጠባይ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸውን ዘገባው ያመላክታል።
በእንግሊዝ ሜት ኦፊስ የረጅም ጊዜ ትንበያ ክፍለ ኃላፊ ፕሮፌሰር አዳም ስካይፍ ‹‹ይህ ክስተት አስቀድሞ ታይቶ የማይታወቅ ሁነቶች ስብስብ መሆኑን በግልጽ ልንገነዘብ ይገባል››ብለዋል።
አክለውም ‹‹በትንበያዎቻችን ውስጥ እንደዚህ ያለ ከፍተኛ የኤል ኒኖ ስጋት ምልክት አይቼ አላውቅም›› ብለዋል።
ምንም እንኳ የአየር ንብረት ለውጥ የኤል ኒኖ ክስተቶችን ያባብሳል ለማለት የሚያስችል ግልጽ ማስረጃ ባይኖርም፤እየሞቀች በመጣችው ዓለም ውስጥ ግን የክስተቱ ተፅዕኖዎች የበለጠ ከባድ እና አደገኛ እየሆኑ መጥተዋል።
