“እስቲልሞከረው” ፖለቲካ!

Date:

መታሰቢያ መልአከ ሕይወት

ወደ ዝርዝር ጉዳይ ከመግባቴ በፊት ርዕሱን ለማብራራት ልሞክር፡፡ “እስቲ ልሞክረው” የሚለው ቃል ለማንም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ሲኾን በጥቂቱ ለማብራራት ያህል ከፖለቲከኛ ጋር ያለውን ዝምድና ለማየት እንሞክር፡፡ ብዙ የዓለም ሐገራት መሪዎች እርግጠኛ ያልኾኑትን ነገር “እስቲ ልሞክረው” ብለው ጦርነት አስነስተው ከፍተኛ ሰዋዊ እና የንብረት ኪሣራ ደርሶባቸው ወድቀትን አስተናግደዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን እነሱ “እስቲ ልሞክረው“ ብለው በጀመሩት ጦርነት በሺ ወይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ፖለቲካ የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ መንግሥት ብቻ ሊሠራው የሚችለው ሥራ ወይም “የመንግሥት ሥራ” ማለት ነው፡፡

የብዙ ሀገር መሪዎች የያዙት ሐገር አይበቃንም ግዛታችን ማስፋፋት አለብን ብለው ጦርነት ለኩሰው የተሳካለቸው አሉ፡፡ ያሰቡትን ሳያሳኩ ሕዝባቸውን አስጨርሰው ለውድቀት የበቁም በርካታ ናቸው፡፡ በአንደኛው እና ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀርመኖች ያለበቂ የወታደር አቅም ዓለምን እንወራለን ብለው ሁለቴ ተሸንፈው አሁን ተሰብስበው ሐገራቸው ተቀምጠዋል፡፡ እዚህ ላይ የግድ ማወቅ ያለብን ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ሕግ ባልነበረበት ወቅት፤ በዓለም ላይ የትኛውም መንግሥት የበላይ እንደኾነ ባልታወቀበት ዘመን የበላይ ለመኾን ሙከራ መደረጉ ብዙም የማይደንቀው መንግሥታት ከቀደምት ታሪክ ተምረው ሊሳካ እንደማይችል ሊያውቁ የሚችሉበት መንገድ ባለመኖሩ ነው፡፡

በአሁኑ በሰለጠነ ዘመን መረጃ እንደ ልብ በሚገኝበት ዘመን የዛሬ 80 እና 100 ዓመት የተሠራን ስሕተት መድገም ግን አሳዛኝነቱን ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ በቅርቡ በሀገራችን ሰሜኑ ክፍል ተነስቶ ለብዙ ወገኖቻችን ዕልቂት ምክንያት የኾነው ጦርነት “እስቲ ልሞከረው” ተብሎ የተደረገ ጦርነት እንጂ ሊሳካ እንደማይችል እንኳን ወታደራዊ ሳይንስ የተማረ ቡድን ማንም ተራ ሰው ሊገነዘበው የሚችለው ጉዳይ ነበር፡፡ በእነ ዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በስድስት ወታደራዊ አደረጃጀት ተከቦ ይህንን ጦርነት መቀስቀሱ በእጅጉን አሣፋሪ ተግባር ነው፡፡ ትግራይን የከበቡት ስድት አደረጃጀቶች አንደኛ መከላከያ፣ ሁለተኛ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሦስተኛ የአማራ ሚሊሺያ፣ አራተኛ ፋኖ፣ አምስተኛ የአፋር ልዩ ኃይል፣ ስድስተኛ የኤርትራ ጦር ሲኾኑ የህወሓት አዛዦች ከዚህ ሁሉ ሠራዊት ተዋግተን አዲስ አበባ እንገባለን ብለው ጦርነት መክፈታቸው ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በእጅጉን እንቆቅልሽ የኾነ ጉዳይ ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ወታደራዊ አደረጃጀቶች ይህንን ውጤት ያስመዘገቡት አዲስ አበባ ከከተመው መንግሥት ጋር ከፍተኛ ፍቅር ኖሯቸው ሳይኾን ህወሓትን መመከት የሀገር እና የሕልውና ጉዳይ መኾኑን በመገንዘባቸው ነው፡፡ አንድ ሰው አንድ ድርጊት ሲፈፅም በሌሎች ላይ ምንም ጉዳት የማያስከትል ከኾነ እስቲ ልሞክረው ብሎ ቢሞክር ብዙም ችግር ላይፈጥር ይችላል፡፡ በሰዎች ሕይወት እና በሀገር ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ተግባር ግን “እስቲ ልሞክረው” ብሎ መጀመር በ21ኛው ክፍለ ዘመን በእጅጉ አሳፋሪ ነው፡፡ በቅርቡ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የወደመው ንብረት በገንዘብ ተሰልቶ የቀረበ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ ሐገራችን ካለባት የውጪ ዕዳ ጋር ተቀራራቢ እንደኾነ እንረዳለን፡፡ በሰሜኑ የሐገራችን ክፍል ይህንን ሁሉ መከራ አስተናግደን ሌላ ደግሞ “እስቲ ልሞክረው” የሚል አጀንዳ እየተዘጋጀልን ነው፡፡ ይህ አጀንዳ አዲስ የኦሮሞ መንግሥት የማዋለድ ተግባር ሲኾን ይህን ፕሮጀከት እውን ለማድረግ ሥራው የተጀመረው ከቤተመንግሥት ግንባታ ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሕዝቦች በማንነታቸው ተሰብስበው የራሳቸውን ሀገር ቢመስርቱ ዴሞራሲያዊ መብት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ነገር ግን አንድ ሀገር ሲመሰረት የግድ ሊኖረው የሚገባ ነገር ድንበር ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በታሪኩ አንድ ቦታ ብቻ ሰፍሮ፣ የራሱን ንጉሥ ወይም ንጉሠ ነገሥት መስርቶ፣ የእምነት ተቋማትን ገንብቶ፣ ግብር የመሠብሰብ ሥርዓት ዘርግቶ የኖረበት አጋጣሚ የለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የነፍጠኛው ሥርዓት መስፋፋት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ በነፃነት በመላው ምስራቅ አፍሪካ እየተዘዋወረ የኖረ ሕዝብ ነው፡፡ ታድያ በምን ሁኔታ ነው ለኦሮሞ ሕዝብ ሳጥን ተሠርቶለት እዚህኛው ሳጥን ውስጥ መንግሥት እንመስርት የሚባለው? የኦሮሞ መንግሥት የመመስረት ሙከራ ሲደረግ የቱ ጋር ነው ድንበር የሚመሰረተው?

ሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የተፈጠሩት በቅኝ ገዢዎች ነው፡፡ ቅኝ ገዢዎች ድንበር አስምረው የአፍሪካ ሕዝቦች ስለአስተዳደሩ ያ ድንበር እንዲፀና ተደርጎ የአፍሪካ ሕዝቦች በሰላም እየኖሩ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቅኝ ገዢዎች ገብተው ድንበር እንዲያሳምሩ ነፍጠኞች ዕድል አልሰጧቸውም፡፡ ስለዚህ አሁን ሥልጣን የያዙ ኃይሎች በየትኛውም የታሪክ መነሻ ላይ ተነስተው ነው የብሔር ድንበር የሚያሰምሩት? የትግራይ ኤሊቶች “እስቲ ልሞክረው” ብለው በጫሩት ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃንና በትሪሊዮን የሚቆጠር ንብረት አጣን፡፡ የኦሮሞ ኤሌቶች ደግሞ የኦሮሞ መንግሥት እንመሰርታለን ብለው በሚለኩሱት ጦርነት የስንት ዜጎችን ሕይወትና ንብረት ሊወድም ይኾን?

ዶ/ር ደብረጽዮን የሰሜኑን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት እጅግ በርካታ ታዋቂ ሰዎች “እባክህ ይቅርብህ” ብለውት ነበር፤ ነገር ግን በመጨረሻ ይህ ሁሉ ውድመት ደርሶ ጉዳዩ በድርድር ተቋጨ፡፡ አሁንም የኦሮሞ መንግሥት ለመመሥረት እየሠሩ ያሉት ኃይሎችም ብዙ ተለምነዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም በእብሪት “እስቲ ልሞክረው” ብለው ብዙ ሰው ለማስጨረስ እየሠሩ ነው፡፡ ደብረጽዮን በሰሜን ዕዝ ላይ ጦርነት ሲያውጅ የጦርነቱ የመጨረሻ ውጤት ደብረጽዮን ካሰበው የተገላቢጦሽ ነው የኾነው፡፡ የሚገርመው ይህንን ጦርነት “እስቲ ልሞክረው” ብሎ ሦስት ጊዜ ማካሄዱ ነው፡፡ አንድ ሕንፃ የሚገነባ ኢንጅነር ሕንፃውን ሲገነባ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ማን ምን ማድረግ እንዳለበት በትክክል አውቆ ነው፡፡ ከተጠናቀቀ በኋላ ሕንፃው ያለችግር ለመኖሪያ ቤት ወይም ለቢሮ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ይህ ኢንጂነር ባለሙያ ስለኾነ አንድም ነገር እስቲ ልሞክረው ብሎ የሚሠራው ነገር የለም፡፡

ፖለቲከኞች ግን የመጨረሻው ውጤት ምን እንደኾነ የማያውቁትን ነገር የብዙ ዜጎች ሕይወት የሚቀጥፍ ነገር ወይም ጦርነት ይቆሰቁሱና መጨረሻ ላይ እንደራደር ይላሉ፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ዓይነት ሠዎች ቤተ መንግሥት እንዳይገቡ ከልባችን መሥራት አለብን፡፡ ይህ ችግር የኛ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ የትግራይ ኤሊቶች እና የኦሮሞ ኤሌቶች ይህንን ሁሉ ሥርዓት የሠሩት ያለበቂ ዕውቀት ሥልጣን እና ከፍተኛ ገንዘብ እጃቸው ላይ ስለገባ ነው፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ እነሱ አሁን እየሠሩ ያለውን ስሕተት ሌሎች መሪዎች ከመቶ ዓመታት በፊት የሠሩት ስሕተት መኾኑ ነው፡፡

አሁንም ከዚህ በፊትም ደጋግሜ እንዳልኩት የኦሮሞ ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ ኖሮ ከሌሎቹ ሕዝቦች ጋር ተዋሕዶ የቀጠለ ሕዝብ እንጂ እራሱን ከሌሎች አግልሎ ዘር እየቆጠረ ቤተሰብ እየመሠረተ የኖረ ሕዝብ አደለም፡፡ የትግራይ ኤሊቶች ሥልጣን ከእጃቸው ስለወጣ ሦስት ጊዜ ስለተሸነፉ አሁን ሰከን ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ኤሊቶች ግን አሁንም ሥልጣን እና ገንዘብ በእጃቸው ስላለ በተከታታይ ስሕተት እየሠሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያሰቃዩ ነው፡፡ በኦሮሞ ኤሊቶች ስሕተት ከምንም በላይ ገፈት ቀማሹ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡ ዛሬ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ እንኳን ኢንቨስት ሊያደርግ ይቅርና ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ ሻይ እና ቡና የመጠጣት ፍላጎቱ እየጠፋ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ኢኮኖሚን ክፉኛ ይጎዳል፡፡ በአጠቃላይ “እስቲ ልሞክረው” እያሉ በ120 ሚሊዮን ሕዝብ መቀለድ ቢቆም ጥሩ ነው፡፡  

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...