‹‹እንደ እኔ በሕይወት ለውጥ ለማምጣት ከፍታን ይቀላቀሉ››

Date:

ዲቦራ በሱፈቃድ

ዲቦራ በሱፈቃድ ትባላለች፡፡ ኑሮዋን በሀዋሳ ከተማ ያደረገች ጠንካራ የ23 ዓመት ወጣት የአካል ጉዳተኛ ናት። ዲቦራ ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ትምህርት መማር የጀመረች ቢኾንም፣ የቤተሰባቸው ዋና የገቢ ምንጭ በሆኑት አባቷ ሞት ምክንያት ግን፣ የገንዘብ እና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች ገጠሟት። በዚህም የተነሳ የዲቦራ ቤተሰቦች ራሳቸውን ለማኖር በአነስተኛ የገቢ ማግኛ ሥራዎች ላይ ተሰማሩ፡፡ ኾኖም ሕይወት እንደ ቀድሞው አልኾነም፡፡ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ አላልፍ አለ። እንዲህ ያለው የገቢ ችግር ለተጨማሪ ማኅበራዊ ቀውሶች የዳረገ ጭምር ስለነበር፣ ዲቦራ የነበራትን ጥሩ የትምህርት አፈጻጸም ለማስቀጠል ሳይቀር አስቸጋሪ አደረገባት።

ዲቦራ ያሳለፈቻቸውን ኹነቶች ስታስታውስ ‹‹ስምንተኛ ክፍል እያለሁ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የተወሳሰቡ የጤና ችግሮችን እስከማስተናገድ ደርሼ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን በአግባቡ መውሰድ አቅቶኝ ነበር›› ትላለች። እነዚህ ሁሉ መሰናክሎች ቢኖሩባትም ፣ ዲቦራ በዚያው አልቀረችም፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ግል ኮሌጅ በመግባት ለሦስት ዓመታት ትምህርቷን ተከታትላ በአካውንቲንግ ለመመረቅ በቅታለች፡፡

ኾኖም ከተመረቀች በኋላ ለረጅም ጊዜ ሥራ አጥታ መቆየቷ፣ በእሷም ኾነ በቤተሰቧ ሕይወት ላይ ሌላ የሥነ ልቦና ጭንቀት ተፈጥሮባታል። ዲቦራ በወቅቱ ከ30 በላይ ለሚኾኑ መሥሪያ ቤቶች ሥራ ለመቀጠር የሚያስፈልገውን ማመልከቻ አስገብታ እንደነበር ብትገልጽም፣ አንዳቸውም ግን ሊቀበሏት አልቻሉም።

በዚህ ጊዜ ነበር ዲቦራ በUSAID የገንዘብ ድጋፍ ‹‹ከፍታ›› የተሰኘው ፕሮጀክት፣ እርሷን ለመሠሉ ወጣቶች ስለሚሰጠው አገልግሎት የሰማችው። ዲቦራ ሳታቅማማ የከፍታ ፕሮጀክትን የወጣቶች ጥምረት ተቀላቀለች፡፡ ከዚያም በሕይወት ክህሎት፣ በተቀጣሪነት (በውጤታማ የሥራ ባሕል)፣ በጾታዊ እና የሥነ ተዋልዶ ጤና እንዲሁም በማማከር ዘርፎች ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን መውሰድ ቻለች።

‹‹ከፍታ እምቅ አቅሜን እንድመለከት ረድቶኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለሕይወቴ ጠቃሚ የኾኑ ክህሎቶችን በመሥጠት ከሥራ ፍለጋም ኾነ ከዝግጁነት ጋር በተያያዘ ያለብኝን ክፍተቶች በሚሞላ መልኩ ደግፎኛል፡፡ በእውነቱ እንዲህ ያሉትን ሥልጠናዎች ከመውሰዴ በፊት ስለጠቀስኳቸው ጉዳዮች ምንም ዐይነት ግንዛቤው አልነበረኝም›› ስትል ዲቦራ ፕሮጀክቶ ምን ያህል ሕይወቷ ላይ ለውጥ እንዳመጣ ትገልጻለች።

ዲቦራ በከፍታ ፕሮጀክት የሥልጠና አገልግሎት ከወሰደች በኋላ የግንኙነት ድሮች በማበጀት፣ በሥራ ፍለጋም ኾነ ለሥራ በሚያስፈልጋት ዝግጁነት ረገድ ያጋጠሟትን በርካታ ውስንነቶች ድል በመንሳት በአዲስ አበባ የፋይናንስና የአስተዳደር መኮንን (ኦፊሰር) በመሆን በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ እንድትጀምር ያስቻላትን ክህሎት ቀስማለች።

እርሷም ‹‹ከፍታ እና ቡድኑ በዙሪያዬ ካለው ሁኔታ ከፍ ብዬ አዳዲስ ፈተናዎችን እንድጋፈጥ እና ያጋጠሙኝ ዕድሎችንም በወጉ እንድጠቀም ትልቅ ድጋፍ እና ጥንካሬ ሰጥተውኛል›› በማለት ምሥክርነቷን ትሰጣለች።

በመጨረሻም ‹‹እንደኔ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ልጃገረዶች ፣ እኔ በትዕግስት እንዳደረግኩት በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ለማምጣት ከፍታን እንዲቀላቀሉ እና ከአገልግሎቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበረታታለሁ›› ትላለች።

በርግጥም የከፍታ ሀዋሳ የወጣቶች የአቅም ማጎልበቻ መርሃ ግብር፣ ሕይወትንና ሌሎች ክህሎትን ለማዳበር የሚያስችሉ ሥልጠናዎችን በመሥጠት፣ በርካታ ወጣቶች እምቅ አቅማቸውን እንዲፈትሹ እና ከፍታ ፕሮጀክትም ወደ ሕይወታቸው ያመጣቸውን እድሎች እንዲጠቀሙ በማበረታታት በዜጎች ሕይወት ላይ በገሐድ የሚታይ ለውጥ እያመጣ ነው።

YOUTH AND CULTURAL

DEVELOPMENT FOUNDATION

***

ይኽ ገጽ በ‹‹ዩዝ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ካልቸራል ፋውንዴሽን›› ከዩኤስኤአይዲ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እና በሌሎች አጋሮች ድጋፍ በሚተገበረው ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› በተሰኘ ፕሮጀክት በኩል ተገቢው ሥልጠና እና ድጋፍ ተደርጎላቸው ሕይወታቸው የተለወጠ ወጣቶች ምሥክርነት የሚቀርብበት ነው፡፡ ‹‹ዩዝ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ካልቸራል ፋውንዴሽን›› ባለፉት በርካታ ዓመታት ማኅበራዊ ኃላፊነቶችን የተወጣ ድርጅት ሲኾን፣ ከሠራቸው ሥራዎች መካከል የተወሰኑትን እንደሚከተለው መጥቀስ ይቻላል፡-

  • የኢትዮጵያ ወጣቶች በሥልጠና እና በባሕል ለውውጥ መርሐ ግብሮች የማኅበራዊ ተሳትፎና የዕድገት ልውውጦች እንዲያዳብሩ አድርጓል፡፡
  • ከ100 ሺህ ያላነሱ ወጣቶች በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በበጎ ፈቃደኝነት እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡
  • በርከት ያሉ ወጣቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚኾኑበት ብድር በመሥጠት እንዲሠሩ አድርጓል፡፡
  • በሥርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ በርከት ያሉ ጥናቶችንም ሰርቷል፡፡ 
  • በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ በአሁኑ ጊዜ ከ70 በላይ ቋሚ ሠራተኞች አሉት፡፡ ከኮንትራት ሠራተኞች ጋር ሲደመር ደግሞ ከ100 በላይ ሰራተኞች በሥሩ አሉ፡፡
  • በሀገሪቱ 4 ንዑሳን ከተሞች ላይ የቅርንጫፍ ቢሮዎች ከፍቷል፡፡
  • ከ10 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችና ከ13 በላይ የመምህራን ኮሌጆች ጋር በአጋርነት ሰርቷል፡፡
  • በድርጅታቱ ድጋፍ በርካታ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ኾነዋል፡፡
  • ‹‹ከፍታ ለወጣቶች›› የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርጾ ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 216 ጥቅምት 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...