(በእውቀቱ ስዩም)
ዘጠና የጎረመስኩበት እንጂ የተወለድኩበት ዘመን አይደለም፤ ግን የዘጠናዎቹ ሰው ነኝ ለማለት አላቅማማም ፤” የኔ ዘመን የምንለው የተወደድንበትን እንጂ የተወለድንበትን አይደለም “ ይል ነበር ምኡዝ::
ዘጠና እውነትም ገራሚ ዘመን ነበር፤ ለመጀመርያ ጊዜ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ መጣጥፍ ጽፌ ሰላሳ ብር ተከፍሎኛል፤ ስነጽሁፍን ሙያየ ብየ የያዝኩት በይሁዳ በጀት ነው ማለት ነው፤ ያኒ ገንዘቡ አላልቅ ብሎኝ፥ማስቀመጫ ሁሉ ቸግሮኝ ትከሻየ ላይ ሳይቀር ተጨማሪ ኪስ ለመሰፋት ተገድጃለሁ፤
የምር በጊዜው ገንዘቡ በረከት ነበረው፤ የሚገርመው ያኔ የመዝናኛ ጊዜ እጥረት እንጂ የብር እጥረት ስላልነበረ “ይደገም ቅዳሜ “ የሚል ዘፈን ሁሉ ተዘፍኖ ነበር፤ አሁን ቅደሜ ሲመጣ በጀታችንን ቁርሳችን ላይ ጨርሰን ቅዳሜ ራሱ ከወረፋው ቀድሞ የገባ እሁድ እየሆነብን ተቸግረናል :;
ድሮ ደመበራድ ሰው ነበርሁ፤ አሁን ኑሮው ነው መሰል ሳር ቅጠሉ ያበሳጨኛል፤ ባለፈው አንድ ወዳጄ ከወገን ተደብቄ ቁርስ ከምበላበት ምግብ ቤት ፥ በፓራሹት ይሁን በአምባሳል ማር ቆራጭ ገመድ አላወቅሁም -ዱብ አለ፤ ከዚያ ቀለል ያለ ሳምቡሳ ያዝዛል ብየ ስጠብቅ ፤ በከፍተኛ ጭካኔ፤ ሁለት ተጨማሪ እንቁላል ያለው እንቁላል ፍርፍር ፤በማዘዝ ቀልቤን ገፈፈው፤
ጭራሽ አስተናጋጁን ጠርቶ “ እንቁላሉ ግን የፈረንጅ ነው ያበሻ ?” ብሎ ሲመራመር ራሴን መቆጣጠር አልቻልኩም፤
“ አንት የሰላቢ ልጅ ! ቅርፊት እና አስኩዋል ይኑረው እንጂ እንቁላሉ የአፍጋኒስታንስ ቢሆን ምን አባህ አገባህ? አሁን አንጥሬ ሳላዳምጥህ የቀረበልህን በልተህ፥ የጀጎል ግንብ ግንባርህን እስኪመታህ ድረስ ሽሽ “ ብየ ገሰጽሁት፤ አኩርፎ ጥሎ ይሄዳል ብየ ጠብቄ ነበር፤ እሱ ግን አኩርፎ መብላቱን ቀጠለ፤
የኑሮ ውድነቱ ያልቀየረው ነገር ቢኖር የመረዳዳት ባህላችንን ነው፤ ባለፈው አንድ አንጋፋ ተዋናይ ምኒባስ አባርረው ሲሳፈሩ የሚያሳይ ቪድዮ ቲክቶክ ላይ ተለቅቅቆ ህዝቡ አዝኖላቸው የመኪና መግዣ እያዋጣላቸው ነው፤
ይህንን የተመለከተ አንድ ድህረ- አንጋፋ ተዋናይ ጉዋደኛየ፥ ከቀበና ወደ መገናኛ የሚሄደውን ሀይገር አውቶብስ አስቁሞ ሲሳፈር የሚያሳይ ቪድዮ አስቀረጸ ፤ ባለሙያ ቀጥሮ ፥ ድሮን ሳይቀር ተከራይቶ በተለያየ አንግል ተቀርጾ ቪድዮውን ወንድሙ አካውንት ላይ ጣደው ፤
አሁን የንግሊዝ ኢምባሲን መንገድ ዘግተህ የዲፐሎማሲ ጫና ፈጥረህብናል ብሎ ፖሊስ በግር በፈረስ እና በታንክ እያፈላለገው ነው፤
