‹‹ከባለሙያዎች በርካታ የማበረታቻ አስተያየቶች ደርሰውናል›› ቤተልሔም ተስፉ

Date:

ከግንቦት 2 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም 17ኛው የአዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል ተካሒዷል፡፡ በፌስቲቫሉ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ የተለያዩ ፊልሞች ለእይታ በቅተዋል፡፡ በመክፈቻ እና በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱም አቶ ክቡር ገና፣ በኢትዮጵያ የኢጣሊያ አምባሰደርን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ታድመዋል፡፡ አጠቃላይ የፌስቲቫሉ ቆይታ ምን ይመስል ነበር ስንል ከፌስቲቫሉ አስተባባሪ ቤተልሔም ተስፉ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡

ራስሽን እና በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ያለሽን ኃላፊነት ብትገልጪልን?

ቤተልሔም፡- ቤተልሔም ተስፉ እባላለሁ፡፡ በፊልም ፌስቲቫሉ ላይ ያለኝ ኃላፊነት ፌስቲቫል ኮርድኔተር ነኝ፡፡

ፌስቲቫሉ ለስንት ቀናት ተካሄደ? የአሁኑስ ስንተኛው ነው?

ቤተልሔም፡- ፌስቲቫሉ ‹‹አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል›› ይባላል፡፡ አሁን የተካሄደው ለ17ተኛ ጊዜ ነው፡፡ ላለፉት 16 ዓመታት በተከታታይ ተካሂዷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝም አላስቆመውም፡፡ ይህ 17ኛ ፌስቲቫልም ከግንቦት 2 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ነው የተካሄደው፡፡

ካለፉት ዓመታት ፌስቲቫሎች የዘንድሮው በምን ይለያል?

ቤተልሔም፡- የዘንድሮው ፌስቲቫል ከሌሎቹ ጊዜያት የሚለየው አዳዲስ ድርጅቶች ከእኛ ጋር በመሥራታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ እንደጥላ ኮስሞቲክስ፣ የኢትዮጵያ እናቶችና ሕፃናት ማኅበር፣ የተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎች፣ አዋሽ ባንክ፣ ኩሪፍቱ ሪዞርት፣ የኢትዮጵያ ሰርቪስ ማኅበር፣ ግዮን መጽሔት፣ ካፒታል ጋዜጣ እና ሌሎችም አጋሮቻችን ኾነው የሠሩበት ነው፡፡  ከዚህ በተጨማሪ በፌስቲቫሉ በርካታ የአፍሪካ ዶክመንተሪ ፊልሞች ታይተዋል፡፡ ወደ አራት የሚጠጉ የኢትዮጵያ ዶክመንተሪ ፊልሞችም እንዲሁ ለእይታ ቀርበዋል፡፡

የፌስቲቫሉ የመክፈቻ ሥርዓት ምን ይመስል ነበር?

ቤተልሔም፡- የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ የተጀመረው በባሕላዊ ሙዚቃ ነበር፡፡ ቀጥሎ ሰርከስ ታየ፣ በመቀጠል አቶ ክቡር ገና የመክፈቻ ንግግር አደረጉ፤ በመቀጠልም የጣሊያን ኢምባሲ ወኪል እንዲሁ ንግግር አድርገዋል፡፡

የንግግሮቹ አንኳር ነጥቦች ምንድን ናቸው? ቦታውስ የት ነው?

ቤተልሔም፡- የመክፈቻ ዝግጅቱ የተካሄደው በጣሊያን ባሕል ማዕከል ነው፡፡ በመድረኩ አቶ ክቡር ገና ፌስቲቫሉ እንዲሳካ ትብብር ላደረጉ አካላት እና ለስፖንሰሮቻችን ምሥጋናቸውን የገለጹ ሲኾን፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ባሕል እና ምናብ ወለድ የፈጠራ ሥራዎች እንዲስፋፉ ላደረጉት ቁርጠኝነት ለተሞላው ተግባርም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ የፊልሙ መክፈቻ የ30 ደቂቃ ዶክመተሪ ነው፡፡ ታሪኩ ሁለት ኢትዮጵያዊ ወንድማማቾች ጣሊያን ሀገር ሄደው ያጋጠማቸውን ነገር የሚያሳይ ነው፡፡ የጣሊያን አምባሳደሩም በዚህ ዙሪያ የሚያጠነጥን የኢትዮጵያና የጣሊያን ግንኙነት በተመለከተ እንዲሁም በፌስቲቫሉ ላይ የነበረውን ሁኔታ አስመልክተው ነበር ንግግር ያደረጉት፡፡

የ30 ደቂቃው የመክፈቻ ዶክመተሪ ፊልም አስተማሪነቱ ምንድነው? እንዴትስ ተመረጠ?

ቤተልሔም፡- ሊመረጥ የቻለበት ምክንያት ታሪኩ ለብዙዎች የስኬት መሰላል በመኾን ያስተምራል ተብሎ ስለታሰበበት ነው፡፡ ፊልሙ ላይ ሁለቱ ወንድማማቾች የማያውቁት ሀገር ሄደው ምን ያህል ስኬታማ ኾነው ሀገራቸውን ማስጠራት እንደቻሉ፤ የገጠማቸውን ፈተና እንዴት በስኬት እንደተወጡት የሚያሳይ በመኾኑ የተሻለ መልዕክት ለታዳሚው ማተላለፍ ይችላል የሚል ግምት ስላለው ነው የተመረጠው፡፡

ፊልም ፌስቲቫሉ አምስት ቀን የዘለቀ ከመኾኑ አንፃር የት የት ቦታ ታየ? የፊልሞቹስ ይዘት እንዴት ነበር?

ቤተልሔም፡- ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የመክፈቻ ፕሮግራሙ በጣሊያን ባሕል ማዕከል ነበር፡፡  ሌሎቹ ቀናት ደግሞ ፌስቲቫሉ የተካሄደው ሀገር ፍቅር ቲያትር እንዲሁም ጎታ ኢንስቲቲዩት ነው፡፡ የመዝግያ መርሐግብሩ ደግሞ በተከፈተበት የጣሊያን ባሕል ማዕከል ነው የተካሄደው፡፡  ለምሳሌ መክፈቻው ላይ ‹‹አሜሪካን ፋሚሊ›› የሚባል ድራማ ነበር፡፡ የሚናገረውም ሜክሲኳውያን የኾኑ ቤተሰቦች አሜሪካ ሄደው ሰነድ አልባ በመኾናቸው እናትየው ታስራ፤ አንዱ ልጅ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ማንነቱን ሲያጠና ግማሽ አፍሪካዊ መኾኑን ይደርስበታል፡፡  አሜሪካ ያሉት ልጆች ደግሞ አንዷ ታማሚ ሌላው ጠበቃ ናቸው፡፡ ጠበቃው ልጅ እናቱን በማስፈታት እንዲሁም እህቱን ለማስታመም የሚያደርግበትን ሂደት የሚያሳይ ነው፡፡ ይህን ዓይነት ችግር ሜክሲኳውያን ብቻ ሳይኾን በርካታ ኢትዮጵያውያንንም ያጋጠመ ነው፡፡ በርካታ አፍሪካውያን ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ስደተኞች የዚህ ገጠመኝ ተካፋይ መኾናቸውን ድራማው ያሳያል፡፡

በፊልሞቹ ተደራሽ መደረግ የተፈለገው ይዘት ምንድነው?

ቤተልሔም፡- አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል የሚመርጣቸው ዶክመንተሪዎች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ይህን የምናደርገው እንዲሁ ከሚሰማ ይልቅ በዶክመንተሪ ፊልም ሲኾን ሰዎች እየተዝናኑ የሚማሩበት ይኾናል በማለት ነው፡፡ ችግሩ የአንድ ሀገር ብቻ ሳይኾን በሁሉም ቦታ ያለ መኾኑንም ለመገንዘብ ይረዳል፡፡ በዚህ ደግሞ እኔ እራሴም ብዙ የማላውቃቸውን ነገሮች ተምሬያለሁ፡፡ ፌስቲቫሉን ስናዘጋጅ በዘርፉ እየሰሩም ይሁን እየተማሩ ያሉ ሰዎች ፕላት ፎርሙን በመጠቀምና ዶክመንተሪ በመሥራት ምን ያህል መሄድ እንደሚቻል ለማሳየትም ነው፡፡ አሁን እየተካሄዱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሶችን ለሰዎች ድምፅ በመኾን በፊልሙ ዘርፍ ምን ያህል ማስተማር እንደሚቻልም ያሳያል፡፡

በአምስቱ ቀናት ውስጥ ምን ያህል ፊልሞች ለእይታ በቁ?

ቤተልሔም፡- በአምስት ቀን ውስጥ 29 የዶክመንተሪ ፊልሞች ታይተዋል፡፡ ፊልሞቹ ሁሉንም ሀገሮች ያጠቃለሉ ናቸው፡፡ ከአሜሪካም፣ ከአውሮፓም፣ ከአፍሪካም በደንብ ተዋቅሮ ነው የተዘጋጀው፡፡ ብዙ ቋንቋዎችን፣ ብዙ ባሕሎችን የነካና የሰውን ፍላጎት ያማከለ ለመምረጥም ያስቸገረን ነው፡፡ ሰውም የፈለገውን መርጦ አይቷል፡፡  

ፊልሞቹ ከታዩ በኋላ የተሠጡ አስተያየቶች አሉ?

ቤተልሔም፡- አዎ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከባለሙያዎች በርካታ የማበረታቻ አስተያየቶች ደርሰውናል፡፡ “በጣም ጥሩ መንገድ ነው፤ በተለይ ወጣቱ እየተዝናና ይማርበታል፡፡ በዘርፉ ካሉ ሰዎች ጋር ለመገኛኘትም አመቺ ነው” የሚሉ አስተያየቶች ሰምተናል፡፡ እኛም በዘርፉ ያሉ ሰዎች እንዲገናኙ እንፈልጋለን፡፡ በሌላ በኩል ከተመልካቹ በኩልም እንዲሁ በርካታ አስተያየቶች መጥተዋል፡፡ በተለይ ፊልሙ የሚታይበት ቦታ አንድ ቦታ ብቻ ቢኾን ደስተኛ እንደኾኑ ገልፀውልናል፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ ያሳያችኋቸው ፊልሞች ዳይሬክተሮች ተገኝተው ነበር? የተገኙ ካሉ?

ቤተልሔም፡- ሁለት ዳይሬክተሮች በመርሐ ግብሩ ተገኝተው ነበር፡፡ አንደኛዋ የአሜሪካን ፋሚሊ ፊልም ዳይሪክተር ስትኾን በፊልሙ ላይም ተዋናይ ኾናም ተሳትፋለች፡፡ ከእርሷ ጋር ጥያቄና መልስ ተደርጎ ነበር፡፡ ሁለተኛው የተገኘው ዳይሬክተር ኢያን ቮሊፕ ዲማሞ ያንቩረፕ የሚባለው ነው፡፡ ሲንሃሊንኮ የሚባል አጭር ዶክመንተሪ አዘጋጅ ነው፡፡ ታሪኩ በድሮ ጊዜ ሲኒማ በሜክሲኮ ውስጥ እንዴት እንደቀጠለ እና የሜክሲኮን ታሪክ በፊልሙ ውስጥ እንዴት እንደነበር የሚያሳይ ነው፡፡  ብዙ ሽልማቶችን ያሸነፈ ነው፡፡ ከእርሱም ጋር ጥያቄና መልስ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የፊልም ባለሙያዎች በዚህ ፕግራም ላይ ተገኝተው ነበር? ከሁለቱ ዳይሬክተሮችስ ጋር ተገናኝተው ነበር?

ቤተልሔም፡- ቅዳሜ ግንቦት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በጎታ ኢንስቲዩቲሽን ሌክቸር ነበር፡፡ እነዚህን ዳይሬክተሮች በማምጣት አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ካሉ የፊልም ተማሪዎችን፣ የቶም ፊልም ማሰልጠኛ ተማሪዎችን አነጋግረን በማምጣት እንዲገናኙ አድርገናል፡፡ በዚህም ሥራቸውን እንዴት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ማውጣት እንደሚቻል፤ ሰብዓዊ መብት ላይ በራሳቸው የሚሠሩ ከኾኑ ምን ማድረግ እንዳለባቸው፤ ሥራዎችን ሲያገኙ የት የት እንደሚያመለክቱ፤ ወ.ዘ.ተ ያለውን ነገር እንዲሁም ዳይሬክተር ሲኾኑ የሚያጋጥማቸውን ነገር እንዴት ማለፍ እንዳለባቸው ተወያይተዋል፡፡  ዳይሬክተሮቹም ያጋጠማቸውን አጋርተዋል፡፡  

ከተሳታፊዎቹ በኩል የተነሳ ነገር አለ?

ቤተልሔም፡- ከታዳሚው የተወሰደው አስተያየት ሰዓቱ አጠረ፤ የሳምንት ጊዜ ይኑረው ወዘተ የሚሉ ናቸው፡፡

አዲስ ኢንተርናሽናል የፊልም ፌስቲቫል መዘጋጀት እንደሀገር ያለው ጥቅም ምንድነው?

ቤተልሔም፡- በርካታ ጥቅም አለው፡፡ የመጀመሪያው ጥቅም ማኅበረሰቡ ስለ ሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለእኛ ለማስተማር ቀላል ያደርግልናል፡፡ ስናስተምር እያዝናናን እንዲኾን ያስችለናል፡፡ በተጨማሪም በዘርፉ ላሉ ሙያተኞች ከፍተኛ ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የመሥራት ፍላጎት ካላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ግንዛቤ ይሠጣል፡፡ ከዚህ ሌላ ሰው በነፃ ይማርበታል፡፡

የፌስቲቫሉ መዝጊያ መርሐ ግብር ምን ይመስል ነበር?

ቤተልሔም፡- መዝጊያ ፕሮግራሙ ያደረግነው በአጭር ዶክመንተሪ ነው፡፡ የዶክመንተሪው ርዝመት 26 ደቂቃ ነው፡፡ “ቃተኛ ሜሽን” የሚባል ፊልም ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ወጣቶችን የሚሸጡ ሰዎችን ታሪክ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህ ዶክመንተሪ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የጣሊያን ባሕል ተቋም የተማሩ ተማሪዎች ያዘጋጁትን የ4 ደቂቃ ዶክመንተሪ አሳየን፡፡ በመቀጠል የደቡብ ሱዳን ቅርጫት ኳስ ፌደሬሽን “ሌላ ሀገር ሄደን የቅርጫት ኳስ ልምዳቸው ምን ይመስላል?” የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ፊልም አሳየን፤ በመቀጠል የአንድ ጣሊያናዊ እግር ኳስ ተጫዋች ታሪክ የሚያሳይ ዶክመንተሪ አሳይተን ፕሮግራማችንን አጠቃለልን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...