በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አማካኝነት ከተፈጠረው የንጋት ሐይቅ 1ሺህ408 ቶን የአሳ ምርት መገኘቱን የ #ቤንሻንጉልጉሙዝ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የእንስሳት ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ብርሃኑ ኢትቻ (ዶ/ር) በሩብ ዓመቱ ከተመረተው ዓሳ 704 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት 9 ሺህ 655 ቶን ዓሳ ለማምረት መታቀዱን የገለጹት ኃላፊው፣ የክረምት ወቅት ዓሳ ለማምረት ምቹ አለመሆን የሩብ ዓመቱ የዓሳ ምርት ዝቅተኛ እንዲሆን ምክያንት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሚቀጥሉት ወራት የሚገኘውን የዓሳ ምርት ለማሳደግም 72 ማህበራት የዓሣ ማስገር ፈቃድ መውሰዳቸውን ለጋዜጣ ፕላስ ተናግረዋል። ከግድቡ የሚገኘውን ዓሳ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የአካባቢውን ማህበረሰብ እና ዓሳ የሚያወጡ ማህበራትን ግንዛቤ የማሳደግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በህዳሴ ግድቡ በተፈጠረው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ከ29 በላይ የዓሳ ዝርያዎች የሚገኙ ሲሆን አንዱ በአማካይ ከ15 ኪሎ ግራም እስከ 20 ኪሎ ግራም እንደሚመዝን ተገልጿል። በተጨማሪም 80 ኪሎ ግራም የሚመዝን ናይል ፐርች የተባለ የዓሳ ዝርያ እንደሚገኝ መገለጹ ይታወሳል።
