አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ኢትዮጵያ ከተቋሙ ባገኘችው በ3.4 ቢሊዮን ዶላር የተራዘመ የብድር አቅርቦት (ECF) የታጀበው እና እያካሄደች ያለችው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም እንቅፋት ሊያጋጥመው ይችላል ሲል ትላንት ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት አስጠነቀቀ።
ከተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት ስታገኘው የነበረው ከፍተኛ የሆነ የውጭ እርዳታ ማሽቆልቆሉ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚስተዋለው ተቋሙ ደካማ ሲል የገለጸው የፀጥታ ሁኔታ ዋነኛ ችግሮቿ ናቸው ሲል ለማሻሻያው አለመሳካት በምክንያትነት አስቀምጧል፤ በተጨማሪም ተቋሙ በሪፖርቱ የትይዩ የውጭ ምንዛሬ (ጥቁር ገበያ) እያንሰራራ መምጣቱም ለኢኮኖሚ ማሻሻያው እንቅፋት መሆኑን ጠቅሷል።
ከአሥር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው የውጭ እርዳታ 12 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ይደርስ ነበር ያለው ሪፖርቱ አሁን ላይ ሀገሪቱ እያገኘች ያለችው የውጭ እርዳታ ወደ 4 በመቶ ዝቅ ብሏል ሲል ጠቁሟል፤ ገና እየቀነሰ ይሄዳል ሲልም አመላክቷል።
አይኤም ኤፍ በሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያው እንዲሳካ ለማድረገ የሄደበትን ርቀት አወድሷል፤ ተቋሙ አስቸጋሪ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ፈጽሟቸዋል ብሎ ካወደሳቸው እርምጃዎች መካከልም የድጎማ ቅነሳን ማካሄዱ፣ የታክስ ማዋቅሩ ላይ ማሻሻያ ማድረጉ፣ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን መከተሉ የሚሉት ይገኙበታል።
ተቋሙ በሪፖርቱ “አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ችግሮች አሁንም እየጨመሩ ነው” ሲል ገልጿል፤ ከነዚህም ውስጥ ቀጣይነት ያለው የጸጥታ ችግር፣ ወደ ግል ይዞታነት መዞር የሚገባቸው ተቋማት (የፕራይቬታይዜሽን) መዘግየት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) መዳከም እና የወጪ ንግዱ ዘርፍ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደቀጠለ መሆኑን ተጠቅሰዋል።
እንደ አይኤምኤፍ ሪፖርት ከሆነ በተያዘው የፈረንጆቹ አመት 2025 ከአምስት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የምግብ ወይም የሰብአዊ እርዳታ ያስፈልገዋል።
የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ በተያዘው አመት 2017 ዓ.ም የካቲት ወር መጀመሪያ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተግዳሮቶች የተሞላ መሆኑን አስታውቀው፣ የኢኮኖሚ ማሻያው “ፈታኝ” ሲሉ በመግለጽ “ጊዜ የሚወስድ” ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
