Home ምልከታ ከኢሕአዴግ እስከ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ከኢሕአዴግ እስከ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ከኢሕአዴግ እስከ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የኢትዮጵያ መሪዎች በታዛቢዎች አንደበት!

አዳነ ጥላሁን ዳኜ (ወልድያ)

ክፍል 3

የጓድ መንግሥቱ ኃ/ማርያምን መንበረ ሥልጣን የተረከበው ‹‹ኢሕአዴግ›› የሚለውን የዳቦ ስም የተሸከመው ድርጅት ይሁን እንጂ ዋናው ግን ‹‹ሕወሓት›› የተባለው የጎሣ ፍቅር የሚወዘውዘው ድርጅት ነበር፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉትም ትግራይን የመገንጠል ዓላማ አንግቦ በሽምቅ ውጊያ ላይ የቆየው ሕወሓት አጋጣሚዎች ተገጣጠሙለትና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) የሚል ሥም ይዘው በአማራ መሬት በሚንቀሳቀሱ ተረፈ ኢሕአፓ ስብሶቦች ጀርባ ታዝሎ አዲስ አበባ መግባት ቻለና ‹‹እነሆ ለ27 ዓመታት ሀገሪቱን በሁሉም ዘርፍ አንኮትኩቶ ከገደል አፋፍ ላይ አቆማት›› ይላሉ፡፡

በዚች አጭር ጽሑፍ በ27ቱ የኢሕአዴግ ዓመተ አገዛዝ የተፈፀሙ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ግፎችና ሀገራዊ ኪሣራ ዙሪያ ዝርዝር ውስጥ ለመግባት አይቃጣኝም ፤ ልግባም ብል እንዳው በቀላሉ ፈፅሞ አልቋጨውም፡፡ ስለዚህ ባልተነገሩ በመሪዎች አንዳንድ ነጥቦች ዙሪያ መሽከርከሩ ሳይሻል አይቀርም፡፡

ኢሕአዴግ ወደሥልጣን እንደመጣ ቅድሚያ በፕሬዚዳንትነት ኋላ ላይም በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለሁለት ዐሠርተ ዓመት አንቀጥቅጠው የገዙን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ዓርማ ጭምር አምርረው የሚጠሉት አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች መለስን ‹‹ለሕዝቡና ላገሩ ልዩ ፍቅር ያለው፣ ሠርቶ የማይጠግብ፣ ስለሥራ እንጂ ስለንዋይና ዝና የማይጨነቅ፣ ይቺን ሀገር መርቶ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ራሱን የሰጠ፣ ሰው አክባሪና ተናግሮ ሰው የማያስቀይም፣ ባጭሩ ከስንት ዘመን በኋላ ብቅ ከሚሉ ብሩህ ዓላማ ከነበራቸው ብርቅ ሰዎች አንዱ ነበር›› በማለት ይበልጥ አቶ መለስን እናውቃቸው ዘንድ ጋዜጠኛ ጠዓመ አብርሃ የፃፈውን ‹‹መለስ በአጃቢዎቹ አንደበት›› የሚለውን መጽሐፍ በመረጃነት ያቀርባሉ፡፡ በተቃራኒው የመለስ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚባለውም ሆነ ብሩህ ዓላማው ‹‹ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንጂ አንድነቷን ለማስጠበቅ አልነበረም፡፡ ደግሞስ ሀገርን ያለወደብ እያስቀሩ ሀገር ወዳድነት አለወይ? ብሩህ ዓላማ የሚባለው ሕዝብን በጎሣ መከፋፈል ከሆነ፣ ብሩህ ዓላማ የሚለውን ምንነት ወይ አልተረዳነውም፣ ያለበለዚያም አውቀን ሌሎችን ልናደናግርበት አስበናል›› የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡

‹‹መለስ ወደሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ስለመኖሩም ጭምር አናውቅም ነበር፤ እኛ የምናውቀው አረጋዊ በርሄን ነበር፡፡ መለስን ያወቅነው ሥልጣን ከያዘ በኋላ ነው፡፡ ያው በተንኮል ተብትቦ አረጋዊን ጥሎት ይሆናል›› የሚሉን ደግሞ  የደርጉ  መሪ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ከገነት አየለ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ነው፡፡ በእርግጥም መለስ በጦር ሜዳ ደረት የሚያስነፋ ጀግንነት አልነበረውም፡፡ እንዳውም አንድ ወቅት የዓድዋን ባንክ ለመዝረፍ በተካሄደ ውጊያ ላይ ፈርቶ ተዋጊ ጓዶቹን ጥሎ በመሸሹ በድርጅቱ ሕግ መሠረት መረሸን ሲገባው ከሞት ያዳኑት አቶ ስብሐት ነጋ ነበሩ፡፡ የሽምቅ ተዋጊዎች አዛዥ አረጋዊ ግን መለስ ለሠራው ወንጀል ተመጣጣኝ ባይሆንም አንድ ሰሞን ለምግብ ማብሰያ ውሀ እንዲያመላልስ ቀጥቶት ስለነበር፣ ‹‹በዚህ ቅጣት ቂም ቋጥሮ ከቆየ በኋላ ወቅት ሲያመቸው አረጋዊን በወታደራዊ ጀብደኝነት ወንጀል ከሰሰውና ከድርጅቱ በማባረር ቂሙን ተወጣ›› የሚሉ ታዛቢዎችም አጋጥመውኛል፡፡

‹‹የደራሲው ማስታወሻ›› የሚል መፅሐፍ ለንባብ ያበቃው ተስፋየ ገ/አብ በበኩሉ ‹‹የመለስ ትልቁ ጉልበቱ ምላሱ እንጂ የጦር ሜዳ ውሎው ወይም የጦር ሜዳ አመራሩ አይደለም›› ይልና በአንድ ወቅት በስብሰባ ላይ ባጋጣሚ ከጎኑ የተቀመጠውን የበርሄ ጎማ እግር አባባልን ሊያስቃኘን ይሞክራል፡፡ ተስፋየ እንደሚለው፣ በርሄ የሕወሓት ነባር ታጋይ ስለነበረና በእግር ጉዞ ላይ ድካም ስለማይሰማው ጓደኞቹ ‹‹ጎማ እግር›› የሚል የቅፅል ሥም እንዳወጡለት ገልፆ፣ በርሄና እርሱ በዚያ ስብሰባ ላይ ተገናኝተው ሲጫወቱ፣ በርሄ የወሬ ሰው ስለሚጠላና በእርሱ እይታ ከነዚህ የወሬ ሰዎች አንዱ አቶ መለስ ስለሆኑበት መለስን እንደማይወደው እንደነገረውና ምክንያቱን ሲጠይቀውም ‹‹መለስ ምላሱ ነፋስ የበዛበት ባንዲራ ነው፡፡ ሲናገር ብቻ ነው የምትሰማው፡፡ ጆሮ ያለው እንኳን አይመስልም፡፡ ሲናገር መትረየስ ነው፡፡ እሳት የሆነውን ሰብስቦ ውሀ ያደርገዋል፡፡ በረዶ የሆነውን ደግሞ ነበልባል ያደርገዋል፡፡ ሠራዊቱንም እንደፈለገ›› ካለ በኋላ በተጨማሪ ‹‹መለስ የወሬ ሰው በመሆኑ የተነሳ ሀገሩን በሙሉ ይኸው ወሬ በወሬ አደረገው፡፡ ደግሞምኮ ዛሬ የተናገረውን ነገ ይገለብጠዋል፡፡ ችግር ሲመጣበትም ማምለጫ አያጣም፡፡ ሀቁን ግን አይናገርም›› በማለት ነበር ተስፋየ ገ/አብ በርሄ ጎማ እግር ‹‹ነገረኝ›› የሚለው፡፡

ተስፋየ በራሱ መለስን የሳለበት የራሱ ሥዕል አለው፡፡ እርሱ ‹‹መለስ ቄጤማ ነው፣ ልክ እንደአርቲ ጉዝጓዝ ይጎዘጎዝልሀል፡፡ ጊዜ ጠብቆ ግን መልሶ ጎዝጉዞ ይረግጥሀል፡፡ ዝሆን የረገጠው ሣር ያደርግሀል፡፡ ውጊያ ላይ ጀግና አይደለም፡፡ መለስ ጭልፊት ነው፡፡ ጤፍ በሚቆላ ምላሱ የነደደውን ያበርደዋል፡፡ ያም ሆኖ መለስ ሲቪል ጀግና አይደለም፡፡ የጦር ሜዳ ጀግንነቱም አልተሳካለትም፡፡የጥሎ ማለፍና የጠልፎ መጣል ችሎታውን ግን አሳድጓል›› ካለ በኋላ መለስንና ስየ አብርሀን ቶምና ጀሪ በሚለው የህፃናት ፊልም ተዋናይ ድመትና አይጥ ሲመስላቸው ‹‹መለስ ብልጧን አይጥ፣ ስየ ደግሞ ጅሉን ድመት ይወክላሉ፡፡ አይጧ ድመቱ ከያዘ እንደሚያንገላታት ስለምታውቅ በብልጠቷ ትጫወትበታለች›› ይለናል በደራሲው ማስታወሻ መፅሐፉ ላይ፡፡

አቶ መለስ ክፋትን፣ ጭካኔንና ሴረኝነትን ብሎም ተገለባባጭነትን የተማሩት ‹‹ከአቶ ስብሐት ነጋ ነው›› የሚሉት ታዛቢዎች አቶ ስብሐት በበኩላቸው የዕኩይ ድርጊት መሪጌታነትን የወረሱት ‹‹ከእንግሊዛዊዉ ቅድመ አያታቸው ነው›› በማለት የእርሳቸው ኢ-ሞራላዊነት ከዘር እንደወረደ በመናገር የአቶ ስብሐት ቅድመ አያት ‹‹ከጀኔራል ናፒየር ጋር ዐፄ ቴዎድሮስን ሊወጋ የመጣ እንግሊዛዊ እንደነበር›› ገልፀው ‹‹እንግሊዞች ደግሞ በተንኮልና ሴራ ብሎም ክፋት አይታሙም›› ይሉናል፡፡

ባጭሩ የአቶ መለስ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ መሬት ያልፈፀመው ግፍና ደባ የለም፡፡ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ የተተኩት አቶ ኃይለማርያምም ቢሆኑ በዘመነ ሥልጣናቸው ብዙ ደም አፍስሰዋል፤ እጅግ በርካቶችንም ለእንግልት፣ ለእሥራትና ስደት ዳርገዋል፡፡ የእርሳቸው ዕኩይ ተግባር ከአቶ መለስ የሚለየው አቶ መለስ ራሳቸው አዛዥ ራሳቸው ናዛዥ እንጂ የሌላ ጋሪ ፈረስ አልነበሩም፡፡ አቶ ኃ/ማርያም ግን ለወያኔያውያን ታማኝ መሣሪያ እንጂ ራሳቸው በራሳቸው ተማምነው የፈፀሙት ሠናይም ዕኩይም ተግባር የለም፡፡ ‹‹ያ ማለት ግን በታማኝ ታዛዥነት ወንጀል አልፈፀሙም ወይም አላስፈፀሙም ማለት አይደለም›› የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡

ባጭሩ ወያኔ መራሹ ኢሕአዴግ በዚች ሀገር ላይ የፈፀመውን አረመኔያዊ ድርጊት በዚች ጽሑፍ ዘርዝሬ አልጨርሰውም፡፡ ስለዚህ በኢሕአዴግ የተፈፀመብንን የግፍ አተላ ይገልፅልኝ ዘንድ ተስፋየ ገ/አብ ወደመድረክ ባመጣው በርሄ ጎማ እግር ‹‹እምዘአረዌ ምድር ታሕተ ከናፍሬሆሙ›› (ከምላሳቸው ሥር መርዝ የቀበሩ እባቦች ናቸው) ሲል ከመዝሙረ ዳዊት ጠቅሶ ለትግል ጓዶቹ ያለበሳቸውን የክፋት ካባ አስፍሬ እኔ ደግሞ ‹‹እግዚአብሔር ዓለምን ሲቆጣ የዘመኑን በሽታ አመጣ ፤ (ኤች አይ ቪ ወይም ኮቪድ 19) ኢትዮጵያን ሲቆጣ ደግሞ ወያኔ ኢሕአዴግን አመጣ›› በሚለው ገላጭ ዐ.ነገር የኢሕአዴግን ነገር ዘግቸ ወደዘመኑ ብልፅግና ልግባ፡፡

የብልፅግና መሪ የሆኑት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደሥልጣን ሲመጡ እስከአሁን ታይቶ የማይታወቅ የሕዝብ ፍቅር ተችሯቸዋል፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ታሪክ እንደእርሳቸው ያለ የሕዝብ ፍቅር የነበረው መሪ የለም፡፡ ዛሬ ያ ፍቅር ሙሉ በሙሉ አለማለት ግን አያስኬድም ፤ በአብዛኛው ቀንሷል የሚለው ግን ያስማማናል፡፡

አሁን አሁን በዶ/ሩ ዙሪያ ወጥ አቋም የለንም፡፡ ዶ/ሩን ከመደገፍ አልፎ መወደድ፣ ከመውደድ አልፎ እስከማምለክ የሚደርሱ ደጋፊዎች እንዳሏቸው ሁሉ ዕለት በዕለት እየፈፀሙት ባለው መንግሥታዊ ተግባራት ዙሪያ ደስተኛ ባለመሆን የሚጠሏቸውና አምርረው የሚኮንኗቸውም  አሉ፡፡

አውስትራሊያ ኗሪ የሆነው ‹‹ታምራት ታረቀኝ›› የተባለው የቀድሞው የተቃዋሚው ኢ.ዴ.ፓና የቅንጂት ሥ.አ.ኮ አባል ለዶ/ር ዐቢይ ልዩ ድጋፍና ከበሬታ ከሚሰጡት አንዱ ነው፡፡ አንድ ወቅት በዶ/ሩ ዙሪያ በድረገፅ የለቀቀውን መልዕክት እነሆ፡-

ታምራት የሚጀምረው ‹‹ዶ/ር ዐቢይ የማርያም ልጅ ጥንቅቅ አድርጎ ከፈጠራቸው አንዱ ነው›› ይልና ሲቀጥል ‹‹ዶ/ር ዐቢይ በክርስትናው መጽሐፍ ቅዱስን፣ በእስልምናው ቁርዓንን የበሉ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው፣ ፈጣሪያቸውን የሚወዱ፣ ትዕዛዛቱን በማክበርና መንገዱን በመከተል ‹ጠላትህን እንደራስህ ውደደው› የሚለውን በተግባር የተረጎሙ፣ ይቅርባይና ታጋሽ፣ ዕውነትን ተከታይና ለሕሊናቸው ያደሩ፣ ችግርን በጉልበት ሳይሆን በብልሀት ብሎም በትዕግሥት መፍታትን የተካኑ፣ ወዘተ… መሪ ናቸው›› ይላቸዋል፡፡

የታምራትን ጽሑፍ ያነበበ አንድ ታዛቢም ‹‹አቶ ታምራት በዚሁ ከቀጠለ አንድ ወቅት ለዶ/ር ዐቢይ ጽላት እናስቀርፅላቸው ሳይል አይቀርም›› ካለ በኋላ ‹‹እንዴት ቢያንስ ሌላው ቢቀር ጠ/ሚ/ሩ ሰው ናቸውና ሰው በመሆናቸው ብቻ ስህተት ሊሰሩ እንደሚችሉ ሳይታየው ቀረ?›› በማለት ጠይቆ ‹‹በዚህ ዓይነት ከሄድንማ መልዐኩ ቅዱስ ሚካዔል ፈጣሪ የሰጠውን ሥልጣኑን አስለቅቀን ለዶ/ር ዐቢይ ይሰጥ ሳንል አንቀርም›› በማለት አስተያየቱን ይሰነዝራል፡፡

የታምራትን አስተያየት ያነበቡ ሌሎች ደግሞ ‹‹ዶ/ር ዐቢይ በግለሰብነት ርህሩህ፣ ቅንና ሀቀኛ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሆኖም መመዘን ያለባቸው በግለ ሰብዕናቸው ሳይሆን ሥልጣን በያዙበት የሀገር አመራር ዙሪያ ነው›› ካሉ በኋላ ‹‹በዚህም መሠረት ባገር ደረጃ ሀገር አረጋግቶና ሰላም አስፍኖ ሀገር በመምራቱ ረገድ ብቁ ናቸው የሚል ዕምነት ስለሌለን በአመራራቸው ደስተኛ አይደለንም›› ካሉ በኋላ በእርሳቸው አስተዳደር ዙሪያ ‹‹ተፈፀሙ›› የሚሏቸውን እንከኖች ሲዘረዝሩ፤

እርሳቸው ወደስልጣን ከመጡ ጀምሮ በየቀኑ መርዶ ያልተሰማበት ቀን አለመኖሩን፣ በሕገ ወጥነት ሽፋን ቤታቸው ፈርሶ ሜዳ ላይ የተጣሉ ዜጎች መኖራቸውን እያወቁ እርምጃ በመውሰድ እንዲስተካከል ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መመሪያ ከመሰጠት ይልቅ  ዝምታን መምረጣቸውን፣ጣራ ለነካው የኑሮ ውድነት የተቀመጠ መፍትሄ አለመኖሩን፣ ከተለያዩ ያገሪቱ አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጎቻችን አይዞህ ባይ ማጣታቸውን፣ የዜጎች መንገላታት፣ እሥራትና በጠራራ ፀሐይ መታገት ተጠናክሮ መቀጠሉን፣ ፍትሕ ተጥሶ ፍ/ቤት ነፃ የለቀቀውን ፖሊስ በማንአለብኝነት ማሰሩን፣ የትግራይ አማፅያንን ትጥቅ የማስፈታቱ ተግባር ተጠናክሮ አለመቀጠሉን፣ እነዚህ አማፅያን ‹‹ወልቃይትና ራያን እናስመልሳለን›› በሚል የጦርነት ቀረርቷቸው ባልተቋረጠበት ሁኔታ የአማራን ታጣቂ ኃይል ትጥቅ ለማስፈታት መሞከሩ ፍትሐዊ አሰራር አለመሆኑን፣ ሀገር አፍራሽ የነበረው ጀኔራል ፃድቃን ለሽርሽር አሜሪካ እንድሄድ ሲፈቀድለት ሀገር ለማዳን የተዋደቀውንና ለሕክምና ወደውጭ ሊወጣ የነበረውን ጀኔራል ተፈራን እንዳይወጣ ማገድ ኢ-ፍትሐዊነት መሆኑን ወዘተርፈ በመዘርዘር ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡

በሙስና ዙሪያ ቅሬታ የሚያቀርቡት ታዛቢዎች በበኩላቸው ‹‹ዛሬ ላይ ከታችኛው የሥልጣን ዕርከን ጀምሮ እጁ በዘረፋ ያልተነከረ ካለ ያ ሰው ቂሉ ማሞ መሆን አለበት›› ካሉ በኋላ የአሁኑ የባለሥልጣናት ስርቆት እጅግ አሳዛኝና አንገት አስደፊ የሚያደርገውም ስርቆቱ ከሀገሪቱ አንጡራ ሀብት አልፎ የዕርዳታ ድርጅቶች ሀብት ጋር መነካካቱ ነው፡፡ እውነት ለመናገር እነዚህ ፈረንጆች እንዳሉት የአሜሪካ ዕርዳታ ድርጅትም ሆነ የዓለም ምግብ ድርጅት ንብረት የሆነው የዕርዳታ እህል ተሰርቆ ከሆነ ጉዳይ ማሳፈር ያለበት መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሁላችን ዜጎችንም ጭምር ስለሆነ መንግሥት አጣርቶ በሌቦቹ ላይ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡

ይኸ እኮ እንደቀላል መታየት የሌለበት ላገር ገፅታ ትልቅ ጠንቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ምድረ ፈረንጅ  ‹‹ረሀብ ማለት ኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያ ማለት ረሀብ ነው›› እንዳላለን ሁሉ ዛሬ ደግሞ ‹‹ስርቆት ማለት ኢትዮጵያ ፤ ኢትዮጵያ ማለትም ሌብነት ነው የሚል የቅፅል ስም እንደሚያወጣልን አስበን በሀፍረት አንገታችንን የምንደፋበት አሳፋሪ ሁኔታ ነው የተፈጠረው›› ካሉ በኋላ ባገሪቱ ሁለንተናዊነት ዙሪያ አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ፤ ‹‹ትናንት በኢሕአዴግ ዘመን የነበረው ሀገራዊ አሳር መከራ አሁንም ተጠናክሮ ቀጠለ እንጂ አልቆመም፡፡ በኢሕአዴግ ጊዜ ከነበረው የተለወጠ አንድም ነገር የለም›› ይሉናል፡፡

በሀገሪቱ መሪዎቻችን ዙሪያ እጅግ በርካታ ነገር በአዎንታም በአሉታም ይነሳል፡፡ እኔ ምሥጋናውንም ሆነ እሮሮውን ከዚህ በላይ ሔጄ ለመጨረስ አቅም የለኝምና ለሁላችንም የሥነምግባር ብሎም የግብረገብነት ትምህርት ይሆነን ዘንድ አሁንም በድጋሜ የተስፋየ ገ/አብ ወዳጅ የነበረው ‹‹በርሄ ጎማ እግር››  ግፍና ግፈኞችን አስመልክቶ በሰነዘረው ትምህርት አዘል ንግግር ጽሑፌን ልቋጭ፡፡ በርሄ እንደሚለው ‹‹ግፍ ግፍን ይወልዳል እንጂ ስንዴ አይወልድም፡፡ጥላቻም ተተክሎ ሮማን አያፈራም፡፡ መዘዝ አለው፡፡ ጎረቤቶቻችንን ማስቀየም ተመልሶ ጉዳቱ ለኛ ነው›› ካለ በኋላ የግፈኞችን መጨረሻ ሲያስረዳ ‹‹ወከመ ሀመልማለ ሀምል ፍጡነ ይወድቁ›› (እንደለምለም ቅጠል ይወድቃሉ) ነበር ያለው፡፡

ለዛሬው አበቃሁ፤ ቸር እንሰንብት!