በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ የተዘረፈ እና የአጼ ቴዎድሮስ ሊሆን እንደሚችል የሚገመት መጽሐፍ ቅዱስ በአቡ ዳቢ በ250000 ዩሮ ለሽያጭ ሊቀርብ ነው።
ከትላንት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ለሽያጭ የሚቀርበው በግዕዝ ቋንቋ በብራና ላይ የተጻፈው መጽሐፍ የሉቃስ ወንጌልን ሙሉ በሙሉ፤ እንዲሁም ከዮሐንስ ወንጌል ደግሞ ከመጨረሻዎቹ 16 ጥቅሶች በስተቀር ሙሉውን የያዘ ነው።
መጽሐፉ እ.ኤ.አ. ከ1730-1740 ጎንደር ውስጥ እንደተጻፈ የተገመተ ሲሆን፣ ተአምራትንና የክርስቶስን ትንሣኤ የሚያሳዩ 235 ሥዕሎችን አካቷል።
ዋና መቀመጫው ኦስትሪያ የሆነው “ኢንሊብሪስ” የተባለ በተለይ ጥንታዊ መጻሕፍትን የሚሰበስብና የሚሸጥ ተቋም አማካኝነት በአቡ ዳቢ ለሽያጭ የቀረበው ከኢትዮጵያ የተወሰደው መጽሐፍ ቅዱስ 250000 ዩሮ የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለታል።
መረጃውን የነገሩን የታሪክ ተመራማሪውና በኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ የሚያጠኑት፣ የተዘረፉትም እንዲመለሱ በማድረግ የሚታወቁት ዶ/ር አሉላ ፓንክኸርስት “ከነገ ጀምሮ ለሽያጭ የሚቀርበው መጽሐፍ ቅዱስ የአፄ ቴዎድሮስ የራሳቸው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማግኘት ቢያስቸግርም፣ መጽሐፉ ለየት ያለና ውብ በመሆኑ የእሳቸው የመሆኑ ዕድሉ አያጠራጥርም” ብለውናል።
መጽሐፉ በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ጦር አዛዥ ናፒር መወሰዱን፣ ከዚያም ለሕንድ የእንግሊዝ ግዛት ዋና አዛዥ በስጦታ መበርከቱን፣ ከዚያም ከአንዱ ሙዚየም ወደ ሌላኛው፣ ከአንድ ግለሰብ ወደ ሌላ ግለሰብ በሽያጭ ሲተላለፍ 158 ዓመታት ማስቆጠሩን ዶ/ር አሉላ አስረድተዋል።
በ19ኛው ክፍለ ዘመን ለተዘረፉ ቅርሶች ዩኔስኮ ከለላ እንደማይሰጥ የነገሩን የታሪክና የቅርስ ተመራማሪው ዶ/ር አሉላ፣ በሕግ በኩል ኢንሊብሪስ መጽሐፉን የመሸጥ መብት ስላለው ምንም ማድረግ አይቻልም ብለዋል።
ሆኖም የተዘረፈ ቅርስ በአሁኑ ወቅት ለሽያጭ መቅረብ የለበትም የሚል የሞራል መከራከሪያ እንዳለና በዚህም አማካኝነት ቅርሱ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ መሥራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
መጽሐፉ ከኢትዮጵያ መዘረፉና ለሽያጭ መቅረቡ በየሚዲያውና በዲፕሎማሲው በኩል ጫና ከተደረገ ግለሰቦችም ሆኑ ሙዚየሞች ለመግዛት እንደማይደፍሩ ተመራማሪው ነግረውናል።
በዲፕሎማሲው መንገድ መጽሐፉን ለሽያጭ ያቀረበው ተቋም ኦስትሪያ የሚገኝ በመሆኑና ሽያጩ የሚካሄደው ደግሞ በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬትስ አቡ ዳቢ በመሆኑ ከሁለቱ ሀገራት ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።
“ዘመኑ ተለውጧል፣ ስለ ቅርሶች መመለስ ያለው እይታም ተቀይሯል። ስለዚህ ኢንሊብሪስ ሽያጩን በማቆም፣ ይህ ድንቅ የብራና ጽሑፍ በሌላ የግል ስብስብ ውስጥ ገብቶ ከሕዝብ ዕይታ ከመሰወሩ በፊት፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለዕይታ እንዲበቃ ጥረት መደረግ አለበት” ሲሉም አክለዋል።
መጽሐፉን ከመሸጥ ለማዳን ያለው ጊዜ አንድ ሳምንት ብቻ፣ዋጋውም ውድ መሆኑን ያስገነዘቡት ዶ/ር አሉላ፣ በዚህም ቢቻል በነፃ ካልተቻለም ለጨረታ ከቀረበበት ዝቅተኛ ዋጋ ተገዝቶ ቅርሱ ለሀገሩ እንዲበቃ ሁሉም ጥረት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ሸገር 102.1
