ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያዎች መካከል

Date:

ፕሪቶሪያን በተመለከተ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ÷ ለሰላም ባለን ከፍተኛ ጉጉት ያሸነፍነውን ጦርነት አቁመን ለሰላም ድርድር ተቀምጠናል ሲሉ አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ እያሸነፈ ለድርድር የተቀመጠ መንግስት እንደሌለም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ለብዙዎች ልምድ የሚሰጥ ታሪካዊ ስምምነት መሆኑን አውስተው÷ መንግስት በጦርነቱ የዜጎችን ሞት ለማስቀረት ስምምነቱን መፈረሙን አስረድተዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምንም ውጊያ አለመደረጉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ያጣቸውን አገልግሎቶች እንዲያገኙ አስችሏል ብሏል፡፡
ነገር ግን በስምምነቱ የሚጠበቁና በበቂ ሁኔታ ተግባራዊ ያልተደረጉ ጉዳዮች እንዳሉ ገልጸው÷ለአብነትም የቀድሞ ተዋጊዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በተሟላ መንገድ አለመፈጸሙን አንስተዋል፡፡
ይህ አለመሆኑ በዋናነት የሚጎዳው የትግራይን ሕዝብ ነው፤ሀገር ማልማት የሚችሉ ወጣቶች በወታደር ስም ተቀምጠው ለክልሉ የሚላከውን በጀት ለቀለብ የሚያውሉት ከሆነ ልማት ሊመጣ አይችልም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ለእነዚህ ታጣቂዎች የሚውለውን በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ለልማት እንዲውል ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ በተሟላ ሁኔታ ሊተገበር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ተፈናቃዮችን በሚመለከት በራያ እና ጸለምት አካባቢዎች ጥሩ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተው÷ ይሁን እንጂ በወልቃይት አካባቢ የተጀመሩ ሥራዎች በተፈለገው ደረጃ አልሄዱም ብለዋል፡፡
ሰብዓዊነትንና ፖለቲካን የመቀላቀል አካሄድ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ እንዳይቻል እክል መፍጠሩን ያብረራት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ይህን አካሄድ ማረም ከተቻለ የፌደራል መንግስት ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ባለፉት ሁለት ዓመታት ተጨማሪ ጦርነት እንዳይፈጠርና ጥያቄዎች በንግግር እንዲመለሱ ላደረጉት ከፍተኛ ጥረት አመስግነዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሁለት ዓመት የሥራ ዘመን ማብቃቱን ተከትሎ እስካሁን የነበሩ አፈጻጸሞች ተገምግመው የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሚያከብር መንገድ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በሃላፊነት መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የፌደራል መንግስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ከህወሓትና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የጊዜያዊ አስተዳደሩን የስልጣን ዘመን ለማራዘም የሚያስችል ውይይት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡
በዚህ መሰረት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ለቀጣይ አንድ ዓመት ይቀጥላል የሚል እምነት መኖሩንና፤ በእነዚህ ጊዜያት አስተዳደሩ ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ለቀጣይ ምርጫ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅበት ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ኤርትራን በተመለከተ

ኢትዮጵያ ለቀይ ባህር ስትል ኤርትራን የመውረር ፍላጎት እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፍላጎት እንነጋገር፣ ሰጥቶ በመቀበል መርህ፣ ህዝቦች በሚጠቀሙበት መርህ እንወያይ የሚል ነው ብለዋል።
የኤርትራ ህዝብ የሚያስፈልገው ልማት ነው፣ ተባብረን መልማትና መስራት እንጂ አንዱ አንዱን መውጋት የእኛ እቅድ አይደለም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ላይ ማንም ሀገር ወረራ ሊፈጽም እና ከጀመርነው ህልም ሊያስቆመን ይችላል የሚል ስጋት የለብንም ብለዋል፡፡
በቂ ዝግጅት ስላለን ማንም አያስቆመንም፣ ዝግጅት የምናደርገውም ጦርነትን ለማስቆም ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
የባህር በር ጥያቄን ማንሳት ነውርነቱ አቁሟል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አቋምም በዓለም ላይ ትልቅ ሀገር ሆኖ የባህር በር የሌለው የለም ስለሆነም በሰጥቶ መቀበል መርህ ሊሆን ይገባል የሚል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ አጀንዳ ለመስጠት የመጣ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት ትኩረት የተሰጠው እና በመደመር መጽሐፍ ላይ የተካተተም ነው ብለዋል፡፡

ግድቡን በተመለከተ

በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሪቫን እንቆርጣለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
በምላሻቸውም የሕዳሴ ግድብ በሁሉም ኢትዮያውያን ትብብር ያለምንም ብድር እየተከናወነ የሚገኝ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሪቫን እንቆርጣለን ብለዋል፡፡
ከግብጽ ወንድሞቻችን ጋር በውይይት ይበልጥ መደጋገፍ እንዳለብን እናምናለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በትብብር አብረን ብንሰራ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ትስስር ማጠናከር ይቻላል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ከግብጽ ጋር አሁንም ለውይይት፣ ለድርድር እና የሕዳሴ ግድብ ያለበትን ሁኔታ ለማሳየት ዝግጁ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡
ሕዳሴ የአፍሪካ ኩራት ነው፤ ለመላው አፍሪካ መቻል ያሳየንበት ነው፤ ስህተትን ያረምንበት ነው፤ 74 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ የያዝንበትም ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጭምር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመው÷ ግድቡ በመሞላቱ ምክንያት አስዋን ግድብ ላይ የጎደለ ውሃ የለም፤ እኛም ቃል የገባነው ይህ እንዲፈጸም ነበር፤ ይህም በተግባር ተሳክቷል ነው ያሉት።

ግጭትን በተመለከተ


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግጭት ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር እኩል የተፈጠረ ነው ብለዋል።
መንግሥት ሰላምን ያስቀደመ፣ ሰላምን በይፋ የሚናገርና የሚተጋ መሆን እንዳለበት ጠቁመው÷ መንግስት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም ሥልጣን ያለው አካል መሆኑንም አንስተዋል።
መንግስት የሚዋጋው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ለዘላቂ ሰላም ሊጋጭ እንደሚችልም አስገንዝበዋል።
በህዝብ የተመረጠውን መንግስት በኃይል ለማፍረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተራ ልምምድ ሆኗል በማለት ገልጸው÷ በኃይል ሥልጣን መያዝን አቅልሎ የማየት ችግር በስፋት እንዳለም ጠቁመዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት ከአንድም ጎረቤት ጋር ያልተዋጋነው የሚያጋጩ ነገሮች ስለሌሉ ሳይሆን ግጭት ጉዳት አምጪ እንደሆነ ስለምናውቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በየመድረኩ ሰላም ሰለም የምንለው ሰላምን ስለምንፈልግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ከማንኛውም አካል ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን አመልክተዋል።
በሰላምና በድርድር ግጭቶችን ለመፍታት መንግስት ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...