በ2017 በጀት ዓመት ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ በተሰራ ሥራ በ124 የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል።
ይህ እርምጃ ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ እስከ ሥራ ስንብት የሚደርስ መሆኑን ለአሐዱ የገለጹት፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አማረ ታረቀኝ ናቸው።
እነዚህ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከሐምሌ 1 ቀን 2016 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ እርምጃ የተወሰደባቸው እንደሆኑም ተናግረዋል።
የትራፊክ ሕግን በሚመለከት የተዘጋጀው ደንብ አሽከርካሪን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፤ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎችንም ጭምር ሊቀጣ የሚችሉ መመሪያዎችን የያዘ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በዚህም መሠረት ጥፋት ያጠፋ ተቆጣጣሪ ሲገኝ የእርምት እርምጃ እየተወሰደ እንደሚሄድ የገለጹት ም/ ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማንኛውንም አካል ሳይመርጥ ሕግን እኩል በማስከበር በትራፊክ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን የመቀነሱን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
