አያሌው አስረስ
ስብሐታውያንን(የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት መሪዎች) እንደፈለጉ በሚዘውሩት የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በልዩ ልዩ መንገድ የሚገለፁ ተቃዎሞዎች ቢኖሩም ይህን ያህል የሚያስደነግጡ አልነበሩም፡፡
አጎራባች በኦሮሚያ የሚገኙ ቀበሌዎችን አስተሳስሮ አዲስ አበባን ለማልማት የተወጠነው «የተቀናጀ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን» የቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ በተለይ በ2008 እየተባባሰ በመሄዱ በርካታ የፖለቲካ አቀንቃኞች ለእሥር ተዳርገዋል፡፡ ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ ሄዶ የአማራና የደቡብ ክልሎችን አዳረሰ፡፡ የተከፋው ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለውን ቅሬታ ለማሳየትና የኢኮኖሚ አቅምን ለማዳክም በፋብሪካዎች ላይና በመንግሥት ተቋማት ላይ እጁን አነሳ፡፡ ከ300 በላይ ፋብሪካዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የግልና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች የእሳት እራት ሆኑ፡፡ አንዳንድ የግል የንግድ ተቋማት ሆቴሎችና ቡና ቤቶችም ዳፋው አልቀረላቸውም፡፡
በዚህ አመፅ የተሳተፉ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ ወገኖች በሕይወትና በአካል መሥዋዕት ሲከፍሉ፣ ከ70ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ እንደ ጦላይ፣ ብላቴን፣ ዝዋይ፣ ሸዋሮቢት ባሉ እሥር ቤቶች እንዲታጎሩ ተደረገ፡፡ ወደ 3 ወር የሚጠጋ ጊዜ ከታሰሩ በኋላ ተሐድሶ ተሰጥቷቸው «አይለምደንም» የሚል ቲሸርት እየለበሱ ‹‹ተመርቀው›› ወደየአካባቢያቸው እንዲመለሱ ሆነ፡፡
“አይለምደንም” ማለት የነበረበት መንግሥት፣ ከክፉ ምግባሩ ሊመለስ ባለመቻሉ አመፁ አሁንም ቀጠለ፡፡ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ አስገደደ፡፡ የኢሕአዴጉ ሊቀ መንበር ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በአዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር እና ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተተኩ፡፡ ከሥልጣን መወገድ የነበረበት ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ተመልሶ ሥልጣኑን ተቆጣጠረው፡፡ ያ ሁሉ መሥዋዕትነት መጨረሻ ላይ ያመጣው ውጤት ስብሐታውያኑን (ትህነግን) ከ4 ኪሎ ወደ መቀሌ መሸኘት ብቻ ሆነ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አካባቢ፣ በቋንቋና በብሔር ሳይለያይ ሕይወቱን፣ አካሉን፣ ንብቱን የገበረበት፤ አገር ደግሞ እስከዛሬም ድረስ ማገገሚያ ላጣችበት የኢኮኖሚ ጉዳት የተዳረገችበት የሕዝባዊ አመፁ ፍሬ፣ ተመልሶ በሕዝብ ጠላቶች እጅ የወደቀው፣ በአገራችን ጠንካራ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለመኖራቸው፣ በብሔር የተከፋፈሉ በመሆናቸውና ኅብረ ብሔራዊ ነን የሚሉትም ደካሞች በመሆናቸው መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበልም ማለት ያስፈልጋል፡፡
ወደ መቀሌ የተሸኙት ስብሐታውያኑ (ሕወሓት) መቀሌን ምሽግና መደራጃ አደረጉት፡፡ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ለ27 ዓመት በቆዩበት የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣንና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ወደ ክልሉ ያጋዙትን ሃብትና ንብረት ለጦርነት መዘጋጃ አደረጉት፡፡ በየቦታው የቀበሩትን መሳሪያ እያወጡ ወለወሉ፡፡
የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት እናቶችን፣ ታዋቂ ሰዎችና የሃይማኖት አባቶችን እንዲያግባቡት ቢልክም ስብሐታውያን የሚሰማ ጆሮ አጡ፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (የአቶ ስብሓት ነጋ የእህት ልጅ መሆናቸውን ይያዝልኝ) በሐሳባቸው ይገፉበት ዘንድ የሚያበረታታቸው በዛ፡፡ ፈረስ ከነሙሉ እቃው በአደባባይም ሸልመው ግፋ በለው አሏቸው፡፡
በአንድ በኩል የፌደራል ኃይሎች፣ በሌላው በኩል ቀደም ሲል ባሠለጠኗቸውና ባስታጠቋቸው የቅማንት፣ የቤኒሻንጉል ወዘተ ታጣቂ ኃይሎች ማዕከላዊ መንግሥቱን ስብሐታውያን እረፍት ነሱት፡፡ መከላከያ ውስጥ የነበሩ የአካባቢ ተወላጆችንም «ትግራይ ትፈልጋችኋለች» ብለው መቀሌ እንዲገቡ አደረጉ፡፡ ሚሊሺና ልዩ ኃይል በማለትም መድፍ ተኳሽ፣ ታንክ ነጂ፣ ፈንጅ ቀባሪ ወዘተ አሠለጠኑ፡፡ ጎን ለጎንም እግራቸው በረገጠበት አካባቢ የሚገኘውን የመንግሥትና የግል ንብረት እየነቀለ ወደ ትግራይ የሚጭን፣ መጫን የማይቻለውን የሚሰባብርና የሚያወድም ኃይል በበቂ አዘጋጁ፡፡ በፊደራሉ መንግሥት ላይ በሚከፍቱ ጦርነት እስከ 3 ሚሊየን ሰው ሊሞትባቸው እንደሚችል፣ በመጨረሻ እነሱ አሸናፊ እንደሚሆኑ አቅደው ወደ ጦርነት ገቡ፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ላይ «መብረቃዊ ጥቃት» ስብሓታውያኑ ከፈቱ፡፡ የፌደራል መንግሥቱ 44ሺ ያህል ጦር ይዞ 250ሺ ጦር ካላቸውና አሸባሪ ካላቸው ጋር ውጊያ ገጠመ፡፡ በ17 ቀን ውስጥም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የመቀሌ ከተማንና ሌሎችን አካባቢዎችን በእጁ አስገባ፡፡ እነአቶ ስብሓት ነጋ ከተደበቁበት የተምቤን በረሃ ተይዘው እየተጎተቱ ወጡ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም የነስብሓት ቡድንን «ዱቄት» መሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ ስሜት ገለጹ፡፡ አሸናፊነቱን ያረጋገጠው የፌደራሉ መንግሥት በዶ/ር ሙሉ ነጋ የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር ትግራይ ላይ አቋቋመ፡፡
ዶ/ር ሙሉ ነጋ ለተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራሉ መንግሥት ሊያደርገው የሚገባውን ድጋፍ በበቂ አላደረገም የሚል ክስ የነበራቸው ቢሆንም፣ እሳቸው እራሳቸው ግን የስብሓታውያን አጀንዳ አስፈፃሚ መሆናቸውን የሚገልጡ ወገኖች በየጊዜው ቅሬታቸውን ከማሰማት አልቦዘኑም ነበር፡፡ በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ኃላፊነት የያዙ ሰዎች እየተገደሉ ባለበት ጊዜም፣ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እየሰሩት ያለውን ሻጥር እየጠቀሱ ለመንግሥት መረጃ የሚሰጡ ክፍሎች ቢኖሩም የፌዴራሉ መንግሥት ግን የሕዝቡን ጩኸት መስማት አልችል ብሎ ችግሩ እየተባባሰ ሄደ፡፡
የፌደራሉ መንግሥት ወደ ክልሉ ሲገባ ድጋፉን የለገሰው ተራው የትግራይ ሕዝብ እየሆነ ባለው ነገር እያዘነ ሄደ፡፡ እንዳሰበውና እንደጠበቀው ሊሆን ባለመቻሉ እየጨነቀው ፊቱን ወደ ስብሓታውያኑ አዞረ፡፡ አንዳንዱ «ድረሱልን» የሚል የሐሰት ጥሪ በማቅረብ መከላከያ ሠራዊት በስብሓታውያን ጦር እንዲጠቃ አደረገ፡፡ በዚህ የተማረረው ማዕከላዊ መንግሥት ምክንያቶቹን ደርድሮ ሠራዊቱን ከትግራይ አወጣ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በግልፅ አማርኛ መንግሥት ከጎኑ የቆመውን የትግራይን ሕዝብ ከዳው የሚያሰኝ እንደ ነበር መግለጽ ግድ ነው፡፡ ዋና ዋና ወታደራዊ ቦታዎችን ይዞ መቆየት እንደነበረበት የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው፡፡
«ዱቄት ሆነዋል» የተባሉት ስብሓታውያን እንደገና አንሰራርተው የአፋርና የአማራ አካባቢዎችን ወረሩ፡፡ ከምሥራቅ እስከ ሰሜን ጫፍ ያለውን ሀገር የጦር ሜዳ አደረጉት፡፡ በወልዲያ፣ ደሴ መስመር እስከ ደብረሲና ዘልቀው ገቡ፡፡ «የምን ድርድር ይልቅስ እጃችሁን ስጡ» የሚል መልዕክት ለሠራዊቱና ለፌደራሉ መንግሥት መሪዎች አስተላለፉ፡፡ አጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑ በገሐድ ታየ፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ጦር ግንባር የዘመቱትና የስብሓታውያኑን ጥቃት መቀልበስ የተጀመረው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊት በመልሶ ማጥቃት ወደፊት ገሰገሰ፡፡ መቀሌ በከበባ ውስጥ ገባች፡፡ ስብሓታውያኑ መቀሌ ከተማ ውስጥ ሆነው ከተማዋን መዋጊያ ሊያደርጓት እንደፈለጉ አሳዩ፡፡ መንግሥትም የከበባ ቀለበቱን እያጠበበ መሄዱን ቀጠለ፡፡ ከተማዋን ለመያዝ ግፋ ቢል ከሳምንት የበለጠ ጊዜ እንደማይወስድበት እየታመነ መጣ፡፡
በሳተላይት መረጃ በመስጠት፣ በአውሮፕላን በድብቅ የጦር መሣሪያ በማስገባት ስብሓታውያንን ሲያስታጥቁ የቆዩት ምዕራባውያን የተኩስ አቁም እንዲደረግና ድርድር እንዲጀመር መወትወት ያዙ፡፡ ጫፍ ላይ የደረሰውን ጦርነት ጨርሶ፣ በሙሉ አሸናፊነት መቆም የነበረበት መንግሥት የድርድር ጥያቄውን ተቀብሎ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተጓዘ፡፡
መንግሥት ‹‹ድርድሩ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሳይሆን ከአንድ አመፀኛ ቡድን ጋር ነው›› ብሎን እንደነበር ልብ እንበል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ሲደርስ ስብሓታውያኑን ያየበትና የያዘበት መንገድ ግን ከአንድ አቻ አካል ጋር የሚደረግ ያስመሰለ መሆኑ ታይቶአል፡፡ የስብሓታውያኑ አርማ ከኢትዮጵያ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጎን ቦታ እንዲሰጠው ማድረግ በራሱ ለኔ የተሸናፊነት ማሳያ ነው፡፡ የመንግሥት ተደራዳሪዎች ተቃውሞ አለማሰማታቸውም ሌላው መሸነፍ ነው፡፡
ስብሓታውያኑ በመሩት ጦርነት በአፋርና በአማራ ክልል ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት፣ የመሠረተ ልማትና የተቋማት ወድመት ደርሷል፡፡ ወደ 1 ሚሊየን የሚጠጋ የትግራይ ወጣት በጦር ሜዳ እንዲረግፍ ያደረጉ፣ እነሱ በቀሰቀሱት ጦርነት እስካሁን ቁጥራቸው በውል ባልታወቀ የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ በአፋርና በአማራ ሚሊሺያና ልዩ ኃይል እንዲሁም በአማራ ፋኖ ላይ ሞትና የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን፣ ይህ ብቻ ሳይሆን ስብሓታውያኑ ማይካድራ ላይ ከ1500 በላይ አማራዎችን በዘራቸው ለይተው እንዲገደሉ በማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀለኞች መሆናቸውን፣ የወንጀል ሸክማቸው የከበደ መሆኑን የመንግሥት ተደራዳሪዎች ያሰቡት፣ የተገነዘቡት፣ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ድርድር ውስጥ የገባ ጭብጥ ስለመኖሩ ሲታይ ደግሞ ይበልጥ የሚያሳዝን ይሆናል፡፡
በድርድሩ ባገር ላይ በሰሩት በደል ልክ ስብሓታውያኑ ወንጀላቸውን እንዲሸከሙ ማድረግ ባይቻልም፣ ትጥቃቸውን ሙሉ በመሉ እንዲፈቱና በክልሉ ምርጫ ተካሂዶ የክልል መንግሥቱ እስከሚቋቋም ድረስ ጊዜያዊ አስተዳደር የመመሥረት ሥልጣን ለፊደራል መንግሥት መሠጠቱ መልካም ነው – ከቀዳዳ ይሻላል ጨምዳዳ እንዲሉ፡፡
የከፋው ግን ስምምነቱ ከተደረገ ሦስት ወር ያለፈው ቢሆንም በስምምነቱ መሠረት ትጥቃቸውን መፍታት የነበረባቸው ስብሓታውያኑ አሁንም 95 በመቶ ከነበረ ትጥቃቸው ጋር መገኘታቸው፣ ታጣቂዎቻቸው መሣሪያቸውን አውርደው ወደ ሥልጠናና ወደ ተሓድሶ ጣቢያ መግባት ሲኖርባቸው እስከ አሁንም ከነትጥቃቸው መሆናቸው፣ ድርድሩ የለበጣ ነበር እንዴ? ብሎ የሚያስጠይቅ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
ጀነራል ታደሰ ወረደ የክልሉን ጊዜያዊ አስዳደር ለማቋቋም ታጥቀው መነሳታቸውን ሰሞኑን አሳውቀዋል፡፡ ለውይይት ባቀረቡት የመመሥረቻ ሰነድ ላይ 55 በመቶ የሚሆነውን የሥልጣን ቦታ የስብሓታውያኑ የፖለቲካ ድርጅትና የወታደር ኃይላቸው እንዲይዙት ተደርጓል፡፡ 15 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በክልሉ ለሚገኙ ተቃዋሚዎች የተመደበ መሆኑ ተገልጧል፡፡ የቀረው 30 ከመቶ ባለቤቱ አልተገለጠም፡፡ የርዕሰ መስተዳድሩን ቦታ ዶ/ር ደብረ ጽዮን፣ የምከትሉን ጀኔራል ታደሰ ወረደ እንዲይዙት መደረጉም ተገልጧል፡፡ ይህ ሆነውና እየሆነ ያለው ‹‹በፊዴራሉ መንግሥት እውቅና›› መሆኑንም አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል፡፡
ይህ ማለት ተሸናፊዎቹ ስብሓታውያን ተመልሰው አሸናፊ እየሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ የሀገሩን አንድነት ለማስከበር ከመንግሥት ጎን ቆሞ ሁሉንም ዐይነት መሥዋዕትነት የከፈለው ሕዝብ ድካም ገደል እንዲገባ ተደርጓል ማለት ነው፡፡ ስብሓታውያኑ እንደገና አገግመው እና ተደራጅተው ለ3ኛ ጊዜ በአማራና በአፋር ክልል ወረራ እንዲፈፅሙ ሁኔታዎች እየተመቻቹላቸው ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ድርጊት ራስ ይዞ ኡኡ የሚያሰኝ አይሆንም?
የኢትዮጵያ ሕዝብ ድካምና መከራ እንዲበዛበት የሚያደርጉት የታወቁት ጠላቶቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ማድረግ ያለባቸውን በሰዓቱና በቦታው የማያደርጉና ማድረግ የማይፈልጉ የራሱ መሪዎችም ናቸው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሃም በላይና ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች ቆም ብለው ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የፖለቲካ ተደራዳሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ወታደራዊ ድርድሩን ኬኒያ ላይ የመሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያመጣንለት ምንድን ነው ብለው እራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው፡፡
መሪዎቻችን በደቡብ አፍሪካና በኬኒያ የተደረሰውን ስምምነት ወደ መሬት ማውረድ ባልፈለጉ ቁጥር፣ በጦር ሜዳ የተሰዉ ወገኖቻችንን ደም በእነሱ እጅ እንደፈሰሰ ከመቁጠር ሕዝብን የሚያግደው ነገር ያለመኖሩን እንዲገነዘቡልን እፈልጋለሁ፡፡ ደግሜ ደጋግሜ ማሳሰብ የምፈልገው የወገኖቻችንን መሥዋዕትነት ከንቱ እንዳይሆን፣ የትግራይ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሌላ ችግር የሚጋለጥበትን መንገድ እንዳይከፈት ነው፡፡
ገጣሚ ዮናስ አድማሱ በአንድ ወቅት የጨነቀ ነገር ገጥሞት የተጠቀመበት ምሳሌ ትዝ ይለኛል፤ ‹ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ፤ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ›› የሕዝቡን ሕይወት፣ ሃብትና ንብረት መታደግ ያለበት መንግሥት ጉዳዩን እንደ ቀላል ሲያየው መመልከትን ያህል የሚያስጨንቅስ ምን ነገር አለ? ነገሮች እየተበላሹና ከመስመር እየወጡ ሲሔዱ፣ ‹‹መንግሥት ሆይ ሰነፍ እረኛ አትሁን›› ብሎ መጮህ ግድ ያልሆነ ምን ግድ ይሆናል?
ፈጣሪ ቸር ወሬ ያሰማን!!!
