ዓባይ እና የትውልዱ ግዙፍ ኃላፊነት! ሃጂ ጀማል ሳኒ ከአሸዋ ሜዳ (ቡራዩ)

Date:

ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢና አስተሳሳሪ ማንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተሻገረችባቸው የዘመን አንጓዎች ሁሉ ይኽ ማንነት የዜጎች ማስተሳሰሪያ ገመድ ኾኖ ኖሯል፡፡ በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በዐውደ ውጊያ ተጋድሎ ሁሉ ይኽ ኢትዮጵያዊ ማንነት እንደ ችቦ በርቶ አልፏል፡፡ እኛም ትውልድ ነን፡፡ የራሳችን ታሪክ፣ የራሳችን ገድል አለን፡፡ የዘመናችን የኢትዮጵያዊነት ማኅተም ደግሞ ዓባይ ውሃ ግርጌ ይገኛል፡፡ ሁላችንንም በኢትዮጵያዊ ሰንሰለት አሰናስሎ፣ የእድገታችን ምርኩዝ ይኾን ዘንድ የሕዳሴው ግድብ ግዙፍ ምልክት ኾኗል፡፡ አዎ፣ እየተገነባ ያለው የሕዳሴ ግድባችን የማንነታችን፣ የኃያልነታችን፣ ቃልን በተግባር ፈጻሚነታችን ተጨማሪ ትዕምርት ነው፡፡

አሁን ታሪክ በመዘከርና ታሪክ በመሥራት አካፋ መስመር ላይ ተሰይመናል፡፡ ዓባይ በኛነታችን ውስጥ ያለውን ትርጉም የሚረዳና ጤነኛ ሕሊና ያለው ሰው ሊቃወመው አይችልም፡፡ የውጭ ኃይሎች ዓይናቸው ቢቀላ፣ ቆሽታቸው ቢያር ይኽንን እውነት መቀየር ከቶም አይችሉም፡፡ የዛሬው ጽሑፌ ትኩረቱን የሚያደርገውም ለዘመናት ከኢትዮጵያ ጋር በታሪክ፣ በጦርነትና በዲፕሎማሲ ግንኙነት ኖሯት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን መረዳት ባልቻለችው ግብጽ ላይ ነው፡፡ ግብጽን የመረጥኩበት ምክንያት ከግድባችንና ከመልማት ጸጋችን ጋር ያላትን ቂም ለመወጣት በምታደርገው ጥረት ውስጥ የምትጠቀማቸውን የተሳሳቱ ትርክቶች ማረም አስፈላጊ ነው ብዬ ስላመንኩ ነው፡፡

በርካታ የግብፅ ፖለቲከኞችና ምሑራን እንደ አልጀዚራ ባሉ የዐረብ ሀገራት የተለያዩ ሚዲያዎች  በመቅረብ ራሳቸውን የእስልምና ጠበቃ ለማድረግ ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ከዚህ ቀደምም ኢትዮጵያን ከእስልምና የተነጠለ ማንነት ያላት ሀገር አስመስሎ ለማቅረብ ያልፈነቀለችው ድንጋይ እንደሌለ ተመልክተናል፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ግብጽ ዐረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ከመሆን የዘለለ በእስልምና ውስጥ ይኼ ነው የሚባል ታሪክ የሌላት ሀገር መኾኗ ነው፡፡ ይኽንን ሀቅ ደፈርና ረገጥ አድርጎ መናገር ተገቢ ነው፡፡ ግብጽ በምንም መመዘኛ በእስልምና ውስጥ ያላት ድርሻ ከኢትዮጵያ ጋር ሊስተካከል ቀርቶ ሊወዳዳር የሚገባ እንኳን አይደለም፡፡ ለዚህ በርካታ ማሳያዎችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በቁርኣን የተገለፀች እና በነብያት የተመሰከረ ሀቅ ያላት ሀገር እንደኾነች ሙስሊም ሀገራት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እነኝህን ታሪኮች ለናሙና እንዘርዝራቸው፡-                                                              

1ኛ) “አላሁ አክበር” የሚለውን ቃል በዓለም ደረጃ የሚታወቀውን የሶላት ጥሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰማው ኢትዮጵያዊ ቢላል ሀበሽ ነው፡፡                             

2) ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ስደተኛ ተቀብላ የነብዩን ቤተሰብ ያስተናገደች ሀገር ናት፡፡                                                             

3ኛ) ነብዩ መሐመድን ጡት አጥብታ ያሳደገቻቸው፣ ኡሙ አይመን የተባለች ኢትዮጵያዊት ነች፡፡ ስለዚህ ከነብዩ የዘር ሐረግ ያላት የኢትዮጵያ ደም ያለው ነብይ አላት፡፡                                                                                                                                                

4ኛ) “ሀበሻን አትንኳት” ብለው መልዕክት ያስተላለፉት ነብዩ ሙሐመድ ዱአ በማድረጋቸው ነው ኢትዮጵያ በየዘመኑ የሚከፈትባት ጦርነት አሸናፊ የምትሆነው፡፡                                                                                                                                

5ኛ) ነብዩ መሐመድ ከዘመዶቻቸው ጦርነት እና ፈተና በገጠማቸው ጊዜ የጦር ረዳታቸው  ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ እነኚህና ሌሎችም በርካታ ታሪኮች ያላት ሀገር መሆኗን ዐረብ ሀገራት ያውቃሉ፡፡ ግብፅ በሥመ ኢስላም እንጂ በኢስላም ታሪክ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ቦታ የሌላት ሀገር ለመኾኗም ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ ነው በመንደርደሪያዬ ግብጽ በምንም መመዘኛ እስልምናን እየጠቀሰች በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ብቃት ሊኖራት አይችልም ለማለት የተገደድኩት፡፡

አሁን ወደ ዋናው ነገሬ ልመለስ፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብን ለትውልድ ተስፋ፣ ለእድገታችንም ምንጭ ይኾን ዘንድ ወደ ተግባር ባናሻግረው የሚገጥመን ፈተና የታሪክ ተወቃሽ ከመኾን አያድነንም፡፡ ስለዚህ ለጠላት በር ሳንከፍት ከምንግዜም በበለጠ አንድነታችን እና ጀግንነታችን ማሳየት አለብን፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመብታችን እና በሀብታችን የመጠቀም መብታችንን ሊሰናክል የሚችል ማንም አይኖርም፡፡ ግብፅ ለዘመናት በኛ ሀብት ስትጠቀም  በውሃችን ስትበለፅግ የኛ ፍቃድ እና ጥያቄ ሳያስፈልጋት ኖራለች፡፡ ፍትሕ ቢገኝ ኖሮ ካሳ ሳይቀር መክፈል ይገባት የነበረች ሀገር ናት፡፡ የኛ ብልፅግና ግን ሒሳብ የማወራረድ ሳይኾን፣ ለግብፅም ሆነ ለአፍሪካ ትልቅ ብርሃን መሥጠት በመኾኑ እንዲህ ያለው ግብዝነት አይነካካንም፡፡

ጥረን ተጣጥረን ህዝባችንን ከድህነት በማውጣት ሀገራችንን ወደ ብልፅግና ማሻገር እንፈልጋለን፡፡ ሁላችንም ተባብረን ከሕፃን እስከ አዋቂ ከገጠር እስከ ከተማ ከትናንሽ ነጋዴ እስከ ትልቁ ባለሀብት ከዳር እስከ ዳር ተደጋግፈን ምሁራኖቻችን በእውቀታቸው፣ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ውጤቱ የምናይበት ጊዜ ቅርብ ይሆናል፡፡ ልዩነታችን የቤት ሥራችን በውይይትና በጠረጴዛ ዙሪያ እንፈታለን፡፡ በዓባይ ጉዳይ ያለን አንድነት ጀግንነታችን በጦርነት ወራሪ መመከት ብቻ ሳይሆን በዓባይ ግድብም እናሳያለን፡፡

ከእንግዲህ የአላህ ፍቃድ ከሆነ ድህነት ታሪክ ሆኖ ይቀራል፡፡ ለሃገራችን ብልፅግና ለህዝባችን ድስታ የሚሆንበት ዘመን ቅርብ ይሆናል፡፡ የስልጣኔና የቴክኖሎጂ የሀይል ምንጫችን  የሆነው ውሃችን ወደ ወርቅ ለውጠን ሀገራችንን ከኋላ ቀርነት ህዝባችንን ከችግር የምናወጣበት ዘመን ተቃርቧል፡፡

ኢትዮጵያ ሀገራችን በማንም ምንም ዐይነት ጫና ወይም በደል ሳናደርስ የግብፅም ሆነ የሱዳን መብት ሳንጋፋ የማንም ጥቅም በማይነካ መልኩ በተፈጥሮ በተሰጠን ስጦታ የአባይ ወንዛችን ለመጠቀም ስንፈልግ ይህን ያህል በደልና ግፍ(ጫና) የሚደርስብን ለምን ይኾን? ይኼ በግልጽ የሚነግረን አንድ እውነት አለ፡፡ ይህም ጥንት ቅኝ ግዛት ባለመገዛታችን የቆጫቸው ሀገሮች አሉ ማለት ነው፡፡ ዓለም በሰለጠነበት በአሁኑ ዘመን ግብፅም ሆነ ሱዳን ሌሎችም የማይመለከታቸው የአውሮፓ ሀገሮች የሚያደርጉብን ጫና ሊቆም ይገባል፡፡ የዓባይ ውሃችን ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ተነስቶ እኛ ጋ የሚደርስ ቢሆን ኖሮ ይደርስብን የነበረው በደል ምን ይሆን ነበር? እኛ በአሁኑ ዘመን ያለን ኢትዮጵያውያን እድለኞች ነን፡፡ ለዘመናት ታሪክ ሲዘክረን እንኖራለን፡፡ ለመጨው ትውልድ የምናስረክበው የበለፀገች ኢትዮጵያን ይሆናል፡፡ በየዘመኑ የታሪክ ቅብብሎሽ ያላት የጀግና ትውልድ መፍለቂያ መሆኗን በታሪክ ማኅደር እናስመዘግባለን፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ በጣም ውስብስብና መሰናክል የበዘበት ጊዜ ላይ ብትሆንም፣ ይህን ጊዜ እንደምታልፈው ጥርጥር የለውም፡፡ ስድሰተኛው ሀገራዊ ምርጫ በዚህ የፈተና ጊዜ ለአፍሪካ ተምሳሌት በሆነ መልኩ አሳክተናል፡፡ የተበታተነው አንድነታችን አጠናክረን ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ቆመናል፡፡ የመንግሥት ምሥረታውም በሚያስደስት ሁኔታ ከተጠበቀው በላይ ለሕዝባችን ደስታ ሆኖ ለጠላታችን አንገት በሚያሰደፋ መልኩ ተጠናቋል፡፡ ዓባይም በቅርቡ ኃል ማመንጨት ጀምሮ ለሀገር ተጨማሪ ሞገስ፣ ለሕዝብ ደግሞ ተጨማሪ የዕድገት ስንቅ እንደሚኾን አንጠራጠርም፡፡ አላህ ሀገራችንን ይጠብቅ!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...