ዘመኑ የቀና ፤ ሀገሩም የጸና ይኾንልን ዘንድ…!

Date:

ወርሃ ጥቅምት 2017፣ እንኾ ግዮን ከውድ አንባቢዎቿ ጋር ዳግም ተገናኘች፡፡ መጽሔታችን ለንባብ በቆየችባቸው ባለፉት ከስድስት ከፍ እያሉ ላሉ ዓመታት በርካታ አዲስ ዘመናትን ከወድ አንባቢዎቿ ጋር አሳልፋለች፡፡ ሀገራችን እና ሕዝባችን ያለፉባቸውን መልከ ብዙ ኹኔታዎች ከግምት በማስገባትም ለወገን ይበጃሉ ያለቻቸውን መልዕክቶች በዚህ የርዕሰ አንቀጽ ዓምዷ አስተላልፋለች ፤ ጠቃሚ ምክረ ሐሳቦችንም አሻግራለች፡፡ ዘንድሮም በጎ ዐዋጇን ለውድ አንባቢዎቿ ‹‹እንካችሁ›› ከማለት አትቦዝንም፡፡

በዘንድሮ የአዲስ ዓመት ዋዜማ ከተሰሙ ዜናዎች መካከል፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ውጤት ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ከኾነ በዘንድሮው ዓመት ለፈተና ከተቀመጡት ተማሪዎች መካከል 5 በመቶ የሚኾኑት ብቻ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ መቶኛው ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የሁለት በመቶ ብልጫ እንዳለው የተገለጸ ሲኾን፣ ይኽም እንደ ‹‹ለውጥ›› ሲሞካሽ ተደምጧል፡፡ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ባሉባት ኢትዮጵያ በዚህ መጠን ዝቅ ያለ ቁጥር ያለው ተማሪ የማለፉ ዜና በምንም መመዘኛ ‹‹ለውጥ›› ተደርጎ ሊወሰድ የሚችልበት ዐውድ ሊኖር ግን አይችልም፡፡

ጥያቄው ታዲያ 95 በመቶ ተፈታኞች ወዳቂ በኾኑባት የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትውልዱ ዕጣ ፈንታ ምን ይኾናል የሚለው ነው፡፡ መንግሥት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተመሣሣይ መልኩ ከወደቁ ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹን ‹‹ሪሚዲያል›› በተባለው መርኃ ግብሩ ወደ ተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ልኮ ካስተማረ በኋላ ሌላ ፈተና በመሥጠት ዩኒቨርሲቲ ገብተው የሚማሩበትን ዕድል መፍጠሩ አይዘነጋም፡፡ እስካሁን የተለየ አካሔድ ለመከተል እንዳሰበ ያሳወቀው ነገር ባለመኖሩም፣ ዘንድሮም የወደቁትን ተማሪዎች አስመልክቶ ተመሣሣይ አካሔድ ሊከተል ስለመቻሉ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ጥያቄው ግን ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ መልክ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ልኮ አስተምሮ ዳግም ከመፈተን ይልቅ ሌላ መንገድ ቢከተል አይሻልም ወይ የሚል ነው፡፡

በዚህ ረገድ የተለያዩ የትምህርት ባለሙያዎች አንድ ወሣኝ አማራጭ ሲያቀርቡ በመደመጥ ላይ ናቸው፡፡ ይኸውም መንግሥት እነኚህን የብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ማለፍ የተሣናቸውን ተማሪዎች መልሶ ወደየዩኒቨርሲቲዎቹ ለ‹‹ሪሚዲያል›› ትምህርት በመላክ ተጨማሪ ባጀት እና ወጪ ከማብዛት ይልቅ ተማሪዎቹ ዓመቱን እንደ 12ኛ ክፍል ተማሪ አጥንተው ዳግም ለፈተና እንዲቀመጡ ለምን አያደርግም የሚል ነው፡፡ በርግጥም በብዙ መልኩ ከታየ ይኽ አማራጭ የተሻለ ሊኾን ይችላል የሚል ዕምነት ‹‹ግዮን›› አላት፡፡

መንግሥት በተደጋጋሚ የትምህርት ጥራትን ከሥረ መሠረቱ ለማረጋገጥ ዕቅድ እንዳለው ሲገልጽ ተደምጧል፡፡ በዚህም ምክንያት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ተጨማሪ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመገንባት ፍላጎትም ዕቅድም እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ይኽን ተከትሎም እስካሁን የተገነቡት ዩኒቨርሲቲዎች ዕጣ ፈንታ ጥቂት ተማሪዎች እና ብዙ የመማርያ ሕንጻዎች ከመታቀፍ የሚዘል አለመኾኑ ግልጽ ኾኗል፡፡ እንዲህ ያለው የመንግሥት ውሣኔ ‹‹ድንገቴ›› ከመኾኑ ጋር ተያይዞ በሽግግሩ ውስጥ ለብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና የሚቀመጡ ተማሪዎች ላይ የራሱ ተጽዕኖ ሊኖረው መቻሉ ባያስጠረጥርም፣ በዘላቂነት ከታየ ግን የራሱ በጎ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል፡፡

ኾኖም ቀደም ብለን ለመጥቀስ እንደሞከርነው፣ እነኚህ በነባሩ ፖሊሲ ተምረው ለፈተና የተቀመጡ በሽግግሩ መሃል ያሉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም የተጠና መልስ እንደሚያሻው ባለፉት ዓመታት ከታየው ሁኔታ በመነሳት መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይም የዘንድሮዎቹን ወደ ዩኒቨርሲቲ ማለፍ የተሣናቸው ተማሪዎች ከፍ ብለን ባስቀመጥነው መልኩ፣ ፈተናውን ደግመው እንዲወስዱ ቢደረግ የተሻለ ኾኖ ሊገኝ ይችላል የሚለው ሐሳብ ግዘፍ ይነሣል፡፡ በአጠቃላይ ዘመኑም የጸና ሀገሩም የቀና ይኾንልን ዘንድ መንግሥት ይኽን ጉዳይ ያስብበት በማለት መልዕክታችንን እናሻግራለን፡፡

———-

ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 216 ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...