
ከአለባቸው ደሳለኝ አበሻ (ለንደን)
በምኒልክ አደባባይ የታላቁ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ሀውልት ቆሞ ይገኛል። ሀውልቱ የአዲስ አበባ ከተማ ጉልላትና መለያ፣ የመላ አፍሪካውያን ኩራት መገለጫ የአድዋ ችቦዎች ዘመን ተሻጋሪ ምስክር በመሆኑ መዘክረ ዓድዋ ነው።
ይህ ሐውልት ከመዳብ ብቻ የተሰራ ሳይሆን በዓድዋ ዘማቾች ደምና አጥንት የቆመ እስኪመስል ድረስ የሐውልቱ ውክልና ግዝፈቱ በመላ ኢትዮጵያዊያን ዘንድም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያን ልብ ተቀርፆ በታላቅ ከበሬታ የነፃነት ምልክት ተምሳሌት ሆኗል።
የእምዬ ምንይልክ ሐውልት የዓድዋውን ዘመቻ የሚመሰክር ውብ የታሪክ መጽሐፍ ሲኾን ማንበብ ለማይችሉ ብዙም ጥቅም የለውም፡፡ ሰው ሰው ለሚሸቱ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዓለም ገና አንብባ ካልጨረሰቻቸው ድንቅ የታሪክ መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ምንይልክ መሆናቸውን የሚያረጋግጥበት ሰነድ ነው። ይህን የማየት እድል ካጋጠማቸው ትውልዶች መካከል አንዱ በመሆኔ የኢትዮጵያዊነት ኩራቴ አይሎ አፍሪካዊነቴ እና ጥቁርነቴም ክቡር መሆኑን የሚያትም የዓድዋ መንፈስ ይሞቀኛል።
የዓድዋን ታሪክ እየሰማሁ አድጌያለሁ። በባርነት ጭነት ቅስማቸው ባልተሰበሩ፤ በጭቆና ቀንበር አንገታቸውን ባልደፉ ጥቁር ሕዝቦች መካከል በመፈጠሬ ኢትዮጵያዊነት በነፃነትና በአንድነት ጥላ ላይ የተነጣጠረ ህያው ቃል መሆኑን እመሰክራለሁ። በዚህ ምክንያት አንድም ቀን የበታችነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም። አንገቴን ቀና አድርጌ ደረቴን ነፍቼ፤ ስራመድ ሕይወቴ በሚሊዮኖች የታጀበ እስኪመስለኝ ድረስ ኩራት ይሰማኛል።
በሐውልቱ አጠገብ ሳልፍ ዓለም የምደነቅበትን የታሪክ መፀሐፍ ገልጭ አንብቤ የጨረስኩ ይመስለኛል። ሰማያት ተከፍተው አምላክ የገለጠልኝን ምስጢር የማይና የምሰማ እስኪመስለኝ ድረስ እደነቃለሁ። በዚያ የነፃነት አደባባይ ስደርስ የጀግኖች መዓዛ ያውደኛል። የፈረሶቹ ኮቴ ፉርፉርታ ከዳን ሲሰማ ድንጉላ ፈረሶቹ ሲያሽካኩ እንደሚጎርፍ ውኃ ድምፅ ሲያጉረመርም እምዬ ምንይልክ በፀሐይ፣ በጨረቃና በሰማያት ሠራዊት ታጅበው የመጡ ይመስለኛል።
ሽለላና ፉከራው .. ቀራርቶና እልታው፣ የጅጂ ሽባባው ዓድዋ .. የጥላሁን ገሠሠ አጥንቴም ይከስከስ .. የመሐሙድ አሕመድ ባባቶቻችን ደም .. የዓለማየሁ እሸቴ ያ ጥቁር ግስላ … አጅበውኝ የዓድዋ ተራሮችን በአይነ ሕሊናዬ ስቃኝ ምድሪቱ በሙሉ የምትንቀጠቀጥ ይመስለኛል።
የጀግኖች መንፈስ ከወደቁባቸው ተራራዎች፣ ካሸለቡባቸው ሸለቆዎች፣ መንፈሳቸው ሳይሞት አሁንም ለሀገሬ ነፃነት ይሟገታል ፤ አፅሜ በማለት ጃሎ ይላሉ …። ዋ..ለካስ ዓድዋ መንፈስ ነው።
አፈር የማያበላሽውን የጀግኖች አባቶቻችን ድንቅ ስራ እያሰብኩ 127 ዓመት ወደኋላ ተመልሼ ከታሪክ ጋር የተጨባበጥኩ ይመስለኛል። በዚህን ጊዜ ህይወቴ መረጋጋት ይጀምራል። ኢትዮጵያዊ በመሆኔም እድሜ ልክ የሚቆይ ነፃነት እንዳለኝ ያህል የመንፈስ ኩራት ይሰማኛል። ገና በዚያ አደባባይ ስደርስ ሰውነቴ መሞቅ የሚጀምረው ደም ስሮቼ በፍጥነት የሚረጩት፣ ጡንቻዎቼን የሚነዝረኝ የአንበሳ ጎፈሩ፣ የጎራዴው ስለት የጋሻ አመካከታቸው፣ የጦር አወራወራቸው.. ውል ይልበኛል።
ገበየሁ ጎራ፣ በሻህ አቦዬ፣ ትንታጉ ታፈሰ፣ ጣይቱ ብጡል፣ ተክለ ሀይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ ሚካኤል፣ ራስ መንገሻ፣ ሐብቴ አባመላ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ንጉስ ተከለሀይማኖት፣ ራስ ወሌ ብጡል፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኮነን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ቀኝ አዝማች ባንቲ፣ መንገሻ አቲከም፣ ራስ ወልደ ጊዮርጊስ… ኧረ ስንቱን ላንሳው፡፡
የሀውልቱም ሚስጥር ይህው ነው።
“ከትልቅ ወይም ከትንሽም ቢሆን መወለድ ሙያ አይደለም፤ ራስን ለታላቅ ሙያ መውለድ ግን ሙያ ነው”
የማያድፈው የማይቆሽሽው ከእምዬ ምንይልክ ሐዉልት ሥር የተፃፈው ህያው ቃል ነው። አዲሱ ትውልድም ሞቴን ከሐውልቱ ስር ያድርገው እያለ እሚጮህበት ምክንያት ለዚህ ነው። እናም አድዋ ማለት ከፍታ ነው፣ አድዋ ማለት እኩልነት! አድዋ መብለጥ፣ ማሸነፍና እንቢተኝነት ነው። አድዋ ማለት ለትውልድ መዳን፣ ለትውልድ አንገት መቃናት የፈሰሰ ደም፣… የወደቀ የጀግና አፅም፣ በባሩድ የነደደ ስጋ ነው! አዎን እደግመዋለሁ፡፡ አድዋ ማለት ከፍታ ነው፥ አድዋ ማለት እኩልነት!! አድዋ መብለጥ፣ ማሸነፍና እንቢተኝነት ነው።
ለዚህ ነው ፈሪዎች የሚፈሩት፡፡ ለዚህ ነው ትርክት ብቻ የሚሆኑት፡፡ ዱሮስ ለራሱ ክብር የለለው ሰው የክብር ትርጉምን መች ያውቀዋል?
ውርደት የለመደ ሰው የሚያከብረው ጀግና የለውም። ከሰው ክብር እራሳቸውን ያሳነሱ ፈሪዎች የቆመ የጀግና ሐውልት ሲመለከቱ ብርክ ይይዛቸዋል። የነገዋን ኢትዮጵያ የሚረከቡ ወጣቶች ግን በሐውልቱ ዙሪያ ያስገመግማሉ፤ ድምፃቸው ከፍ አድርገው እንዲህ እያሉ ይዘምራሉ፡-
“የጀግኖች.. ደም ጥሪ ..ቃሉ ቀሰቀሰኝ
ለታሪክ አደራ ..ለድል ታጠቅ አለኝ!!
ታሪክን የኋሊት ሠፍሮ አደባባዩን በትዝታ የሚያውደው ሐገር ተረካቢ ድምፅ ነው። በደመና ውስጥ እንደሚታይ ቀስተ ደመና ግርማ ሞገስ ለብሰው፣ እንቢልታና መለኮት ይነፉታል፣ ከበሮው ይጎስሙታል፣ የአርበኞቹ ሽለላና ቀራርቶ የወይዛዝርቶቹ እልታና ጉሮ ወሸባዬ ያቀልጡታል አዲስ አበባም ለ127 ዓመታት ሕያው ምስክር ሆና እልልታውን አብራ አቅልጣዋለች!! በዚህ የድል ሀውልት አደባባይ ስደርስ የሚሰማኝ ነፃነት ይኸው ነው፡፡
የተናቁ የታሪክ እጆችን በማስመሰል የእውነተኛውን ታሪክ መታሰቢያ ለማጥፋት ይሞክራሉ ነገር ግን የእምዬ ምንይልክ ታሪክ ረዥም ጎራዴ ነው።
በሰማይ ላይ የፈሰን በክዋክብት የተሞላውን ደማቁን ሰማይ ቀና ብሎ አለማየት ንፉግነት ነው። ምንይልክ ማለት እንደዚህ ነው። ይህ የጥቁር ንጉሥ ኮኮብ ድምቀትና ውበቱ የትውልድ ስብዕና ስላገኘ ነው ሚስጥሩ፡፡ በዓለም ላይ የበለፀገ የግቢ አበባ የሚመስለውን ነፃነት ካወጁ፣ ከከበሩ ሐውልቶችን ውስጥ የእምዬ ምንይልክን ሐውልት የሚስተካከል የለም። የዓድዋው የጦር መሪ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የምንይልክ ሐውልት የአፍሪካውያን ፍልስፍና እና ቅኔ ነው። የሐውልቱ ሚስጥር ይኸው ነው!
አባቶቻችን ለኛ ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ባርነትን ላለመሸከም የከፈሉት መራር እውነት ነው፡፡ የብርሀን ፀዳሉ ሲለካም ከእንጦጦ ቤተመንግሥት እስከ ዓድዋ ተራሮች ድረስ .. ያበራል!! የሐውልቱ ሚስጥር ይኸው ነው፡፡
እኛም እስከ አለም ዳርቻ ድረስ ስለ አባቶቻችን ገድል እንዘምራለን።
ምንይልክ … ጥቁር ሰው …!!
ገና አፍሪካም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ከኛ ጋር ወረኢሉ ላይ፣ ውጫሌ ላይ፣ ዓድዋ ላይ፣ በእነዚህ ታሪካዊ ቦታዎች ላይ አብረውን ይዘምራሉ፡፡ ምንይልክ..ጥቁር ሰው። የሐውልቱ ሚስጥር ይህው ነው።
የጠቅላላ የጥቁር አፍሪካዉያን ታሪክ ማሰሪው ምንይልክ መሆናቸውን ገና አለም ትመሰክራለች። “በሰው ፊት የሚመሰከሩልኝ ሁሉ እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ቤት ፊት እመሰክርለታለሁ። በሰው ፊት የሚከዳኝን ግን እኔም በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እከዳዋለሁ” ተብሏንና እኛም በሁላችንም ልብ ውስጥ ዘልቆ የሚውለበለበው የዓድዋ ህያው ታሪክ የነፃነት ድ-ም-ፅ ነውና በሀውልቱ ስር እየመሰከርን ዘመናትን እያቋረጥን በትውልድ ቅብብሎሽ ገና እንዘምራለን። ምንይልክ…ጥቁር ሰው…! የሀውልቱ ሚስጥር ይህው ነው። የአፍሪካውያን ፍልስፍና እና ቅኔ ነው።
ቸር እንሰንብት!