የሕዝብ እና መንግሥት አያዎ የት ያደርሳል?

Date:

የኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ እውነታ ዕለት ዕለት ወደ ቁልቁለት እየተምዘገዘገ ነው፡፡ ይኽ ለመኾኑ ታሪካዊ እና ነባራዊ ምክንያቶች ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ዳሩ ግን የብልጽግና መንግሥት ያደሩ ፖለቲካዊ ቅራኔዎችን ለመፍታት የተከተላቸው መንገዶችም ኾኑ እንደ አዲስ ያዋለዳቸው ችግሮች፣ ነገሩን በብዙ መልኩ እንዳወሳሰቡት ከመረዳት ቸል አያስብልም፡፡ ትልቁ ችግር ግን ይኼ አይደለም፡፡ ዓቢይ ኾኖ የሚታየው ችግር፣ በመንግሥትነት የተሰየመው አካል ይኽንን በየዕለቱ ከአቅሙ በላይ እየከበደ የመጣውን ችግር አሳታፊ በኾነ መልኩ ለመፍታት ብሔራዊ ጥሪ ከማድረግ ይልቅ ‹‹እውነትም መንገድም እኔ ነኝ›› ብሎ ክችች ማለቱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከአምስት ዓመታት በፊት ይነሱ የነበሩት ችግሮች አድገው እና ደድረው የኢትዮጵያውያንን አብሮ የመኖር ሕላዌም ኾነ፣ የሃገረ መንግሥቱን ቀጣይነት አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ሲያስገቡት እየታዘብን ነው፡፡

እንዲህ ወዳለው ድምዳሜ የሚያስገባን በዚህ ሳምንት የተመለከትናቸው ሁለት ኹነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እነርሱም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ፊት ያደረጉት ንግግር እና ገዢው ብልጽግና ‹‹የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ የሚካሄዱ መድረኮች የማወያያ ሰነድ›› በሚል ርዕስ [ፈልጎም ይኹን ሳይፈልግ] በማኅበራዊ ሚዲያ የበተነው ጽሑፍ ነው፡፡ እነኚህ ሁለት አስረጂዎች መንግሥት ከስህተቱ ለመማር ያልፈቀደ፣ እንዲያውም ነገሮችን በጥፋት እያባባሰ በሥልጣን መሰንበትን መለዮ (modus operandi) አድርጎ ለመጓዝ መምረጡን እንድናምን ምክንያት የሚኾኑን ነጥቦች ናቸው፡፡ ዘርዘር አድርገን እንመልከታቸው፡-

እንደሚታወቀው አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የዐማራ ክልልን ለአምስት ዓመታት በርዕሰ መስተዳድርነት ከመምራት ጀምሮ፣ ‹‹ለውጥ›› የሚባለው የ2010ሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ክስተት እንዲፈጠር አብሪ ከሚባሉት ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ገዱ ሲመሩት የቆዩትም ኾነ፣ አሁን በም/ቤት የወከሉት ሕዝብ ሲያነሳቸው እና ሲታገልላቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ለመረዳት ከማንም የቀረቡ ሰው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት መሠረታዊ የአገዛዝ ለውጥ መምጣት ለጥያቄዎቹ ምላሽ የማግኛ ወሣኝ መንገድ መኾኑን አምነው ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ስለመታገላቸው በስፋት ሲነገር ቆይቷል፡፡

አቶ ገዱ ‹‹እህ›› ብለው ያዋለዱት ለውጥ አሁን ላይ የደረሰበትን ቁመና ያስቀመጡት ግን ‹‹ፖለቲካዊ ችግርን ፈጥሮ ወታደራዊ መልስ የሚሰጥ›› በማለት ነው፡፡ በክልሉ በአሁኑ ወቅት ያለውን ችግር ለመፍታት መፍትሔውም ‹‹የፖለቲካ ውይይት›› መሆኑን አጽንኦት በመሥጠት በግልጽ ‹‹ይህን ችግር በቅንነት ለመፍታት ከተፈለገ፤ እስካሁን በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ሲሞከር ከርሞ ሀገርን ወደ ከፋ ጥፋት ያመራው ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ሳይሆን፤ የፖለቲካ ውይይት ነው የሚል እምነት አለኝ›› ብለዋል፡፡

ይኽ የአቶ ገዱ ንግግር የምክር ቤቱን ምክትል አፈጉባዔ ጨምሮ በአባላቱ ዘንድ የፈጠረው ተቃውሞ፣ ለዚህም ያሳዩት ምላሽ፣ በኋላም በ‹‹አብላጫ›› ድምጽ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መጽደቅ፣ መንግሥት ስለሚከተለው ዕምነት ፍንትው አድርጎ የሚናገር ነው፡፡ አቶ ገዱ መርተው ያመጡት ሥርዓት በዚህ መልክ ‹‹ፖለቲካዊ ችግርን ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ይንቀሳቀሳል›› ከሚል ትችት አንስቶ፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ እና የብልጽግና ፓርቲ ግንኙነት በማይጠገንበት ደረጀ ስለተበጠሰ፤ በአስቸኳይ ሁሉንም የአማራ ኃይሎች ያቀፈ ጊዜያዊ አስተዳደር ይቋቋም›› እስከሚለው ጠንካራ ምክረ ሐሳባቸው ድረስ መንግሥት ከ40 እስከ 60 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርበታል የሚባለውን ክልል ችግር ብቻውን የመፍታት አንዳች አቅም እንደሌለው በግላጭ የሚያሳይ ነው፡፡ ይኽ በፖለቲካው ዓለም እውነታ እንደ ቀላል የማይታይ ትልቅ እማኝነትም ነው፡፡ እንደ አቶ ገዱ ካለ ባለፉት አምስት ዓመታት ከክልል ርዕሰ መስተዳድርነት እስከ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት፣ ከጠ/ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪነት እስከ ትልቁ የሀገሪቱ ም/ቤት አባልነት በብዙ አመራርነት ውስጥ ያለፈ ሰው ዋቢነትም አገዛዙ የገባበትን አዘቅጥ በልኩ ለመረዳት ትልቅ ማስረጃ ነው፡፡

ሌላው እና ሁለተኛው ጉዳይ የብልጽግናው መንግሥት ‹‹የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ የሚካሄዱ መድረኮች የማወያያ ሰነድ›› በሚል ርዕስ በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ባለ 36 ገጽ ጽሑፍ ነው፡፡ የጽሑፉ ሰነድ ዓቢይ ትኳሬውን ‹‹በክልሉ ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግር የመፍታት አስፈላጊነት›› ላይ ቢያደርግም ‹‹ለውጡና የአማራ ክልል››፣ ‹‹በለውጡ የአማራ ሚናና፣ የጥያቄዎቹ አፈታት››፣ ‹‹ክልሉ የገጠሙት ተግዳሮቶች››፣ ‹‹የሰሞኑ አመፅ መነሻ ምክንያቶች እና የደረሰው ጉዳት››፣ ‹‹የመልዕከት ስራ አቅጣጫዎች›› እና ሌሎችም ጉዳዮች የተካተተበት ነው፡፡

ሰነዱ በቅርቡ በዐማራ ክልል የተፈጠረውን ግጭት ምክንያት የሚገልጸው ‹‹የጽንፈኛ ቡድኑ ዋና ፍላጎት በሕዝብ የተመረጠውን የክልሉን መንግሥት በመፈንቀልና የክልሉን ስልጣን መቆጣጠር፤ በሂደት ደግሞ እራስን በማጠናከር 4 ኪሎ መግባት ነው፡፡›› (ገጽ 30) በሚል ዓረፍተ ነገር ነው፡፡ ‹‹ይህ ፍላጎቱ እንዲሳካም ለመንግሥት ድጋፍ ያስገኛል ብሎ የሚያስባቸውን ጥረቶች የማደናቀፍ አቅጣጫ ተከትሏል›› በማለት በብዙዎች የታመነውን እና ለጉዳዩ የተሰጠውን መሠረታዊ ምክንያቶች ይክዳል፡፡ አልፎ ተርፎም ‹‹እየተዋጋኝ ነው›› የሚለው ቡድን ‹‹ዋና የሚባል›› ምሽጉን ‹‹ባሕር ዳር ቀበሌ 14 ልደታ ቤተክርስቲያን ላይ በማድረግ›› ዓለማው ‹‹ሕዝቡ ቤተ ክርስቲያን ተቃጠለብኝ ብሎ እንዲወጣ መቀስቀስ›› እንደኾነ ያስቀምጣል፡፡

እንዲህ ያለው ከተነሣው የሕዝብ ጥያቄ በሺህ ማይሎች የራቁ ምክንያቶችን የመደረደር የመንግሥት ፍላጎት፣ ከፍ ብለን ለመግለጽ እንደሞከርነውም የጦርነቱን ሥረ ምክንያት ተረድቶ አሳታፊ የንግግር መፍትሔን ከመፈለግ ይልቅ፣ አለባብሶ መሔድን ምርጫው ስለማድረጉ ማሳያ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ‹‹የመልዕከት ስራ አቅጣጫዎች›› በሚለው የሰነዱ ክፍል መንግሥት የተፈጠረውን ችግር አስመልክቶ በቀጣይ ሊከተለው ያሰበውን መንገድ ሲያመላክት ‹‹የአማራን ሕዝብ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ራሱን ሸፍኖ ከሚወጋ ዘራፊ ሃይል ጋር የሚደረግ ትግል እንደሆነ፣›› (ገጽ 35) የሚል ኃይለ ቃል አስፍሮ እናገኘዋለን፡፡ መንግሥት በዚህ መልክ በሰፊው የክልሉ ሕዝበ ዘንድ የተነሳውን ጥያቄ ዕውቅና ከመሥጠት ይልቅ እንዲህ ባለ ተላላ ዓረፍተ ነገር ራሱን ለማሞኘት መፍቀዱ አጃኢብ ነው፡፡  

የክልሉን ሕዝብ ልኂቃንን ‹‹ማኩረፍና ራስን ማግለል››፣ ‹‹ንቀት››፣ ‹‹ድሎችንም ችግሮችንም ለሌላው መስጠት››፣ ‹‹በሌሎች አጀንዳ መጠለፍ›› እና ‹‹ከዘላቂ ዓላማ ይልቅ ለክሥተት መጋለጥ›› በሚሉ ሐረጎች የሚገልጸው ሰነዱ፣ መንግሥት የከፈተውን ጦርነት ‹‹ራሳቸዉን ከሕግና ሥርዓት በላይ ካደረጉ የታጠቁ ቡድኖች ጋር የሚደረግ እንደሆነ›› በስፋት መልዕክት ማሰራጨትን፣ አልፎም ‹‹ከሕልውና ሥጋት ታደጉኝ›› ብሎ በሰልፍ እና በመፈክር ሲጮኽ ከመቆየት አልፎ በማንነቱ ይደርሱበት የነበሩ ሕልቆ መሣፍርት ግድያ፣ መሳደዶች እና የመንቀሳቀስ እገዳዎች እንደተፈጸሙበት ሰነዱ ሳይቀር ፈራ ተባ ብሎ እያመነ፣ ዞር ብሎ ከታጣቂው ኃይል ጋር የሚደረገው ጦርነት ‹‹ከሰሜኑ ጦርነት የተጎዳዉን የአማራን ህዝብ ሳይወድ በግድ ወደ ጦርነት ጎትቶ ለማስገባት ቀን ከሌት ከሚጥሩ ዘራፊ ቡድኖች እና ከጦርነት ንግድ አትራፊ ከሆኑ ቡድኖች እጅ ለመታደግ የሚደረግ ትግል መሆኑን›› (ገጽ 34) ማድረጉ መንግሥት በርግጥ ያደሩም ኾነ እንደ አዲስ የተፈጠሩ ማኅበረ ፖለቲካዊ ቅራኔዎች እና ችግሮች በሰለጠነ አግባብ እንዲፈቱ ያለመፈለጉ ርቀት እና እውነታውን አለባብሶ በተማመነበት ነፍጥ ‹‹እልባት›› ለመሥጠት ያሶመሶመበት ጥግ ሙዳ ሥጋ ካየ አሞራ በላይ መኾኑን ለመረዳት አይገድም፡፡

በአጠቃላይ በሳምንቱ ዐበይት ኾነው መነጋገሪያ በኾኑት የአቶ ገዱ ንግግርም ኾነ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጨው የብልጽግና ሰነድ፣ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል የተቋጠረው ቅኔ እንዳይፈታ በእጅጉ መወሳሰቡን ኩልል አድርጎታል ብሎ ለመደምደም ያግዛል፡፡     

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...