የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘና ሰራተኞችን ለመቀነስ ሳይሆን አቅማቸውን ለማሳደግ ያለመ ነው

Date:

ዘንድሮ ለሁለተኛ ዙር የሚሰጠው የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘና አመራሮችና ሰራተኞችን ለመቀነስ ሳይሆን አቅምና ብቃታቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን  የከተማና መሰረተልማት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በስሩ ያሉ ተቋማት ጋር በሁለተኛ ዙር የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ተግባራዊ እንዲያደርጉ ከተመረጡ መስሪያቤቶች መካከል በመሆኑ ከሀምሌ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የከተማና መሰረተልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገልፀዋል።

ከመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የፖሊሲ አምዶች ስር ከተቀመጡ ተግባራት መካከል የመንግስት ሰራተኞች የብቃት ምዘናና ማረጋገጫ ስርዓት መገንባትና የማስፈፀም አቅምን ማሳደግ ዋነኛው መሆኑን አንስተዋል።

በአምዶች ስር ከተቀመጡ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥም ስርአተ ስልጠና ወይም ካሪኩሌም መቅረፅ ፣ የስልጠና ሞጁል ዝግጅትና አቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሁም የብቃት ምዘና ፈተናዎችን ማዘጋጀትና ሰራተኞችን መዝኖ ውጤት የማሳወቅ ስራ መሆኑን ገልፀዋል። ይህ ማለት ግን አመራሩንና ሰራተኛን የመቀነስ አላማ ሳይሆን ብቃቱን የማሳደግና ክፍተቱን በመለየት የአቅም ግንባታ ስርዓቱን በተከታታይ ለመስጠት ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

ሪፎርም ሲደረግም የሁሉንም የመንግስት ሰራተኛና የኢትዮጵያን ህዝብ ትብብር እንደሚጠይቅ ያነሱት ሚኒስትሯ “ሁላችንም ይህ አጀንዳ የጋራችን ነው ብለን መውሰድ ይጠበቅብናል ፣ አላስፈላጊ ውዥንብሮችን መፍጠር አያስፈልግም” ብለዋል።

በሚቀጥሉ አራት ወራት ውስጥ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናቀቅና በምዘናው ውጤት መሰረት ተከታታይ የአቅም ግንባታና የስልጠና መርሀግብሮች እንደሚተገበሩ ተናግረዋል። እነዚህን ተግባራትም በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ለመከወን ከውስጥ አቅም ባሻገር ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ስምምነት ካደረገባቸው የከፍተኛ የትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር እንደሚሰራበት ጠቁመዋል።

በ8 ሚኒስቴር መስሪያቤቶች ባለፈው አመት የተጀመረው የሪፎርም ስራ ሁለተኛ ዙር በዘንድሮ አመት መጀመሩን ያነሱት ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ከፍተኛ አማካሪና በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ወልደሚካኤል ናቸው።

በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ወደ 600 የሚጠጉ ሰራተኞች መኖሩን የሚያነሱት አቶ ተስፋዬ በስሩ ያሉት ተጠሪ ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ የኮንስትራክሽን ባለስልጣን እና የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እንዲሁም በእነርሱ ስር የሚገኙ ሌሎች  ተቋማት ሪፎርሙ የሚካሄድባቸው መሆናቸውን አንስተዋል።

ከእነዚህም ውስጥ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት 270፣ በኮንስትራክሽን ባለስልጣን ወደ 100 እንዲሁም በመንገዶች አስተዳደር ወደ 6ሺህ ቋሚ ሰራተኞች እና ወደ 11ሺህ የሚሆኑ ደግሞ የኮንትራት ሰራተኞች መኖራቸውን አክለዋል። ይህ የሰራተኞች ቁጥርም በፌዴራል ደረጃ ብቻ ሲሆን በክልሎችና በከተማ ደረጃ ሲጨመር ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።

እነዚህን ሰራተኞችን ጨምሮ በርካታ ተቋማት ላይ የሚተገበረው ይህ ሁለተኛው ዙር የሪፎርም ስራ፤ ሀምሌ ወር ላይ እንደተጀመረ ያነሱ ሲሆን መዋቅር ማሻሻልን ጨምሮ ከምዘና በተጨማሪ ሌሎች ማሻሻያ የሚደረግባቸው፤ በርካታ ስራዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

(አሐዱ ራድዮ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...