አዳነ ጥላሁን ዳኜ(ወልዲያ)
ሳምንቱ የክርስቲያኖች ታላቁ በዐል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዐል የሚከበርበት ሳምንት ነውና እስቲ በመንፈሳዊነቱ ዙሪያ ከታዘብኩት ትንሽ ማለት እችል ዘንድ ነገሬን በሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳት መነሻነት ልጀምር፡-
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ ላይ በወያኔና በፌደራል መንግሥት መካከል በተካሄደው ድርድር ላይ ተካፍሎ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የሰላም ስምምነት የተፈራረመው በአምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተመራው ልዑካን ቡድን ነበር:: ይኸ ቡድን የሰላም ስምምነት መፈራረሙ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ድርጊቱን የፈፀመው ግን ያገሪቱን ህግ ጥሶ አሸባሪ ከተባለው የወያኔ ቡድን ጋር በመሆኑ በርካታ ትችት እንዲነሳበት በር ከፍቷል፡፡ የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶም ዝርዝር ማብራሪያ ጉዳዩ ለሚመለከተው የኢትዮጵያ ህዝብ መስጠት ነበረበት ፤ ይኸም አልሆነም፡፡
ዝርዝር ማብራሪያ ባለመሥጠቱም በጦርነቱ ወቅት ከመንግሥት ጎን ቆሞ ክፉና ደጉን የተካፈለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከነገሩ ባለቤትነት በመገለሉ ብሎም የስምምነቱ ፍሬ ጉዳይ በምስጢር በመያዙ ቅሬታ ከማስነሳቱም ሌላ ፕሪቶሪያም ሆነ ናይሮቢ ላይ በተደረገው ስምምነት ዙሪያ ለበርካታ መላምት የዳረገ ብሎም በአንዳንድ ቁልፍ ሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያም ጥርጣሬ አሳዳሪ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በአፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ የተመራ ሌላ የልዑካን ቡድን ታህሳስ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ መቀሌ ተጓዘና ከወያኔ አጋሚዶዎች ጋር ተቃቅፎ በመሳሳም ዝምድናውን አጠናከረ:: በዚህ ቡድን መቀሌ መጓዝ ዙሪያ ቅሬታ ያስከተሉትና አነጋጋሪ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ የመጀመሪያው አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ ከዚህ ቀደም በራሳቸው ሰብሳቢነት በፓርላማ አባላት አማካኝነት አሸባሪ አስብለው ያስወሰኑበት ቡድን የአሸባሪነት ስያሜ ሳይሻር ራሳቸው ሕጉን ጥሰው ከአሸባሪ ቡድን ጋር መገናኘታቸው አንዱ ሲሆን፣ በ2ኛ ደረጃ ቀደም ሲል ፕሪቶሪያ በተደረገው ስምምነት ወቅት እንዲፈርስ ከተወሰነበት የወያኔ ቡድን ጋር መገናኘታቸው በራሱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ለፈራሹ ቡድን ቀጣይ ሕልውና ዋስትና እንደመስጠት መቆጠሩ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ዝርዝር ትንተና ውስጥ ብገባ ከተነሳሁበት ጭብጥ ያወጣኛልና ጉዳዩን ለሕግ ባለሙያዎች ትቼ ላነሳው ወደፈለግሁት ፍሬ ነጥብ ልግባ፡-
በነክቡር ታገሰ ጫፎ ጉብኝት ዙሪያ ላነሳው የፈለግሁት ትዝብት ቡድኑ መቀሌ በገባበት ወቅት አቀባበል ካደረጉለት መካከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶና የእስልምና ቤተ እምነቶች መሪዎች በኩል ስለታየው የአቋም መንሸራተትና ተገለባባጭነት ነው፡፡
በወቅቱ የእስልምና መሪው ቡድኑ መቀሌ የገባበት ቀን ታሪካዊ ቀን መሆኗንና የኢትዮጵያን አየር መንገድ በጉጉት ይጠብቁ እንደነበር ሲገልፁ የኦርቶዶክሱ መሪ ደግሞ እንኳን ደህና መጣችሁን አስቀድመው ስለሰላሙ ዘላቂነት ምኞታቸውን ገልፀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መቀሌ በመግባቱ ደስተኛ መሆናቸውንና ሌላም ሌላም ጉዳይ ነው ያነሱት፡፡
ሁለቱም መንፈሳዊ መሪዎች ያሳዩትን መለሳለስና ፍቅር አዘል ንግግር እንደሰማሁም እውነት እነዚህ መሪዎች እየደለሉን ይሆን? ወይስ ከአንጀታው ነው ይኸን ፍቅር አዘል ንግግር ያሰሙት የሚል ጥያቄ ነው ያጨረብኝ:: ሰሚ ካለ እግዜር ያሳያችሁ የሚል አቤቱታ አቅርቤ ትዝብቴን ሰቀጥል ሁለቱም መሪዎች የሰላም ስምምነት ተፈረመ እስከተባለበት ወቅት ድረስ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ትግሬነትን፣ ከሀገራዊነት ይልቅ ነገድና ጎሳን ከፍቅር ይልቅ ጠብና ደም መፋሱስን፣ ከአንድነት ይልቅ መነጣጠልን፣ ከመንፈሳዊነት ይልቅ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቀንቃኝነትን መርጠው የሽፍታው ቡድን በኢትዮጵያ ላይ ለፈፀመው አረመኔያዊ የግፍ ተግባር ቡራኬ የሰጡና እጅግ በርካታ ንፁሀን መጨፍጨፋቸውን ከመደገፍ አልፈው የትግራይን ኦርቶዶክስና እስልምና ሃይማኖቶች አመራር ከእናት ቤተእምነቶች የገነጠሉ መሆናቸውን ያሳወቁን ከሦስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ነው፡፡
በእስልምና ሃይማኖት ዙሪያ ጆሮየን ቢቆርጡት የማልሰማ ወደል መሀይም በመሆኔ በእንግዳ ተቀባዩ የመቀሌው የእስልምና መሪ በኩል ከላይ ካቀረብኩት አስተያየት ውጭ የምለው ተጨማሪ አስተያየት የለኝም፡፡ የአቡነ ኢሳይያስ አቋም መዋዠቅና በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ተግባር ግን ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ ለት የተባለው ብሂል በእርሳቸው ተክለ ቁመና ዙሪያ ደብዝዞ መጥፋቱን ነው ያሳየኝ፡፡
እዚህ ላይ ነገሬ ይሰምር ዘንድ ከአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) በመቀጠል የወያኔ ኢሕአዴግን መራር አገዛዝ ፊት ለፊት የተጋፈጠውን አርቲስት ፋሲል ደመወዝን ማንሳት እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ ፋሲል ከወያኔና የወያኔ ታማኝ ተላላኪ አረመኔዎች ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጠው ሰው ብቻ ሳይሆን ሳር ቅጠሉ ጭምር ለዚያ አረመኔ አገዛዝ ታማኝ አገልጋይ ለመሆን በሚያሸረግድበትና በሚሯሯጥበት ወቅት ነበር፡፡
ይህ ሩጫና ማሸርገድ ጠንቶ ይታይ የነበረው ደግሞ አገር ይታደጋል ተብሎ ይታሰብ የነበረው ግን ከአገር ፍቅር ይልቅ የግል ጥቅሙ ፍቅር ጠንቶበት ከዘረኛውና ጎሳ አምላኪው ብሎም ህዝብ ረጋጩ የወያኔ ኢሕአዴግ ጉያ ተሸጉጦ በአቋም ደረጃ እንደገበታ ውሀ ሲዋልል በነበረው ተምሬአለሁ እያለ በመማሩ ይመፃደቅ በነበረው (ንዑስ ከበርቴም ይባላል) የህብረተሰብ ክፍል ነበር፡፡
ከ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ማግሥት እስከ 2007 ዓ.ም በነበሩት 10 ዓመታት የዚህ ተምሬአለሁ ባይ የሕብረተሰብ ክፍል የአብዮታዊ ዴሞከራሲ አሸርጋጅነት እጅግ ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም በጣም እጅግ በሆነ ሁኔታ ገዝፎ ለጉድ የታየበት ወቅት ነበር፡፡ በነዚህ ዓመታት በድርጅቱ የስብሰባው ቦታ ሁሉ አቦል ቡና በማሳለፍ ፋፎ ቆሎ በማቅረብና ዳቦ በማደል በበላይ የኢሕአዴግ ባለስልጣናት አካባቢ ታማኝነቱ እንዲታወቅለት ሽር ብትን ይል የነበረው ይኸው ተምሬአለሁ ባይ የሕብረተሰብ ክፍል እንደነበር የትናንት ትዝታ ነው፡፡
አንድ ወቅት ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ የእርሳቸውን ፊርማ በማስታወሻነት ለማስቀረት የነበረውን የስብሰባ ተሳታፊ ሽሚያና ግፊያ ለተመለከተ ብቻ ሳይሆን እርሳቸው በሞቱበት ወቅት መርዶውን ለሕዝብ ለመንገር በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ያለው ዜና አንባቢ (ስሙን አልጠቅስም) ከዜናው ይልቅ እናቱን የተረዳ ሀዘንተኛ በመሰለ አኳኀን ያስቀደመልን እንባውን ነበር፡፡ ያ ዜና አንባቢ የዚያን ዕለት ድርጊቱን ረስቶና ቆዳውን ገልብጦ አቶ መለስ የዘረጉትን ሀገራዊ አገዛዝ ሲያወግዝ በሰማሁት ቁጥር አየ ሰው እያልኩ እስቃለሁ፡፡ ለነገሩ በአቶ መለስ ሞት ምን ያልታዘብነው አለ? በገጠር በከተማው በየቀበሌው ድንኳን ተጥሎ ሁሉም አልቃሽና አስለቃሽ ሆኖ ማን የበለጠ እንዳዘነ እንዲታወቅለት አንገቱ የተሰበረ መሆኑን ለማሳየት የተሯሯጠበትና እጅግ ገራሚም አስተዛዛቢም ተውኔት ጭምር የተሰራበት እንደነበር አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡
ለዚህ አባባሌም ሩቅ መሄድ ሳያስፈልግ የዕለት ምግብና መጠለያ ያልነበራቸውና የሌላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይቀር የለቅሶውና የሀዘኑ ተካፋይ ሆኑ ተብሎ የቀረበውን ትዕይንት ብቻ መጥቀሱ ይበቃል፡፡ እውነት ለመናገር እነዚህ ጎዳና ተዳዳሪዎች መለስ ሞተ አልሞተ ምን ይቀርባቸዋል? የእርሱ ሞትስ በእነርሱ ኑሮ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? እነርሱ በዚያ መልክ ሀዘን እንዲገልፁ የተደረገውስ በፍላጎታቸው ወይስ በካድሬ ግፊት ገንዘብ ተከፍሏቸው? የእነርሱ ሀዘንተኛ ሆኖ በቴሌቪዥን መቅረብ ለኢሕአዴግ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ የሚያጎላው ለድርጅቱ የሚያስገኘውን ጥቅም ወይስ በፓርቲው ላይ የሚደርስበት ትችት ነው የሚያመዝነው? ወዘተ የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ቢያጭርም ይቺን መጣጥፍ ለሚያነብ ፍርዱን ትቼ ከይቅርታ ጋር ወደዋናው አጀንዳየ ልመለስ፡፡
እንግዲህ ፋሲል አስከፊውን የወያኔ ኢሕአዴግ አገዛዝ የተጋፈጠውና “አረሱት” የሚለውን ዜማ በአደባባይ ያቀነቀነው ከላይ እንደጠቀስኩት ሳር ቅጠሉ ሳይቀር እጅግ በርካታው ያዳም ዘር የኢሕአዴግ ቱባ ባለሥልጣናትን ጫማ ለመሳም በሚሽቀዳደምበትና የአድርባይነቱ ቫይረስ በመላ ኢትዮጵያ ተጠናክሮ በተስፋፋበት ዓመታት ውስጥ ነው ፋሲል ያን ሙዚቃ ያቀነቀነውም በሀገረ ኢትዮጵያ ከሚኖሩ ውሱን ኗሪዎች ውጭ በመላ ሀገሪቱ የአድርባይነቱ በሽታ ጠንቶ ሰው የሚሆን ሰው ፈልጎ በማጣቱ ነበር፡፡
በወቅቱ ፋሲል ከኛ ከኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ያገኜው ግብረመልስም ጭቆናው በቃኝ በሚል አካኪ ዘራፍ ብለን ከጎኑ መቆምን ሳይሆን በፍርሀት ቆፈን ተሸብበን ካድሬ አየኝ አላየኝ በሚል ፍርሀት የታጀበ ጭብጨባ ድጋፍን በመግለፅ ያለበለዚያም የቤትን በር ዘግቶና አልጋ ውስጥ ገብቶ አንሶላ ውስጥ ተደብቆ በሹክሹክታ ፋሲልን ማመስገንና ማድነቅን ነበር፡፡ ያኔ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በወያኔ ኢሕአዴግ የማደንዘዣ ኪኒን (የሥልጣን ወንበር፣ የትምህርት ዕድልና የተለያየ ጥቅማጥቅም/ ደንዝዘን ስለነበር) በግልፅ አደባባይ ከጎኑ ልንቆምለት ባለመቻላችን በአካልም በሥነልቦናም በገንዘብ ጭምር መክፈል ያለበትን መሥዋዕትነት ከፍሎ በዚያ ተስረቅራቂ ድምፁ ሄድኩላችሁ እንግዲህ ይስፋችሁ የሚል ሽለላ በማሰማት እኛ በሕይወት ያለነው አለመርባታችንን ስለመታዘቡ ገልፆ ዘረኛው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን እንዴት እንዳዋረዷትና እንዳጎሳቆሏት ይመለከቱለት ዘንድ ወደሙታን ሰፈር ፊቱን በማዞር ለዐፄ ቴዎድሮስ አቤቱታ አዘል ጥሪ በማቅረብ ወደአሜሪካ ኮበለለ፡፡
አሁን ላይ አስተዛዛቢ ደግሞ መቼም ዓለም ወረተኛ ናትና ነገር ዓለሙ ተገለባብጦ የወያኔ ኢሕአዴግ ክንድ ዝሎ ለውጥ መጣ ሲባል ፋሲልና ፋሲልን መሰሎች የከፈሉትን መስዋዕትነት ባላካተተ መልኩ የታሪክ ሽሚያ ውስጥ ገብቶ የለውጥ አቀንቀኝነቱን ፋና ወጊነት ማዕረግ ለመውሰድ በየአደባባዩ ጎፈሬውን የሚያበጥረው አንድም በነፋሲል ዓይነቶቹ ላይ የግፍ አርጪሜ ሲያሳርፍ የነበረው ካድሬ ሲሆን በሌላ በኩልም ትናንት ከትናንት በስቲያ በየድርጅት ስብሰባ ላይ ቆሎ ሲሰፍር የነበረው አሸርጋጅ መሆኑ ነው፡፡
በአሁኑ ያገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሀገራችንን የቁልቁለት ጉዞ እጅግ የከፋና አሳሳቢ የሚያደርገውም በአቋሙ የሚፀና አቋመ ብርቱ መጥፋቱ ብቻ ሳይሆን የመገለባበጡና የአድርባይነቱ በሽታ በኛ በዓለማውያን ብቻ ሳይገታ ወደመንፈሳዊ መሪዎቻችን በመተላለፉ ጭምር ነው፡፡
እዚህ ላይ መነሳት ያለበት አንኳር ነጥብ በተከበሩ አፈጉባዔ ታገሰ ጫፎ የተመራው ልዑካን ቡድን ዘንድ በኢትዮጵያዊነት ወዝና ለዛ ጠብ እርግፍ ያለ ፍቅር ያሳዩን አቡነ ኢሳይያስ እርሳቸው የሚመሯት የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ እምነት ሥር እንደማትተዳደር ብቻ ሳይሆን በጉርብትና ጭምር እሳት እንደማትጫጫር ብሎም ዝምድና እንደሌላት ይፋ ያደረጉት ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ መሆኑን ነው እንግዲህ ትናንት ከትናንት በስቲያ በትህትና ምትክ የታባታችሁ ዓይነት አንድምታ ባዘለ ግግግር ከመንፈሳዊ አባትነታቸው ይልቅ የትግራይ አጋሚዶዎች ፍቅር ጠንቶባቸው በፖለቲከው ውስጥ ተዘፍቀው ጠብ ጫሪነትንና መገንጠልን ሲያቀነቅኑ የነበሩ አባት ባንድ ጊዜ ተገልብጠው ስለፍቅር፣ ስለሰላምና የኢትዮጵያ ንብረት ስለሆነው ጤያራ ጭምር ውዳሴ ሲያሰሙ ስሰማ ፋሲል አፄ ቴዎድሮስን ከመቃብር እንደጠራ ሁሉ እኔ ደግሞ አቋመ ብርቱ የነበሩት አቡነ ሰላማ፣ አቡነ ጴጥሮስንና አቡነ ሚካኤልን ነው መጥራት ያማረኝ፡፡
አቡነ ሰላማ የያዙት አቋም ትክክልም ይሁን አይሁን በአቋማቸው ፀንተው ነው ቴዎድሮስን የተጋፈጡትም ሆነ በእስር ቆይተው እስር ላይ እንዳሉ የሞቱት፡፡ አቡነ ጴጥሮስም ኾኑ አቡነ ሚካኤል የፋሺሽት ኢጣሊያን ፋሽስትነት አጋልጠውና ግንባራቸው ላይ ለተደገነው የጥይት አረር ሳይበረግጉ እንዳውም ለኢጣሊያ የተገዛህ ርጉም ሁን የሚል ግዝት አሰምተው ነው አዲስ አበባ እና ጎሬ ላይ ሞትን ፊት ለፊት የተጋፈጡት፡፡ እንግዲህ የእነዚህን አቋመ ብርቱ ጳጳሳት ወንበር የተረከቡት የኛ መሪዎችን እንደገበታ ውሃ የሚዋልል አቋም አይተን ብናዝን ብንተክዝ የሚፈርድብን ያለ አይመስለኝም፡፡
አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የሃይማኖት አባቶች አቋመ ብርቱነት መሸርሸር የጀመረው በአቡነ ማቲዎስ የመጨረሻ ዕድሜ ዘመን ሲሆን የቤተ እምነቷ አጠቃላይ ገፅታ ከአምላክ ፍላጎት ይልቅ ወደሰውኛ ፍላጎት ተቀይሮ ጎልቶ የወጣውም በአቡነ ጳውሎስ የጵጵስና ዘመን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የአቡነ ማቲዎስ እንደገበታ ውሀ የዋለለ አቋም ገሀድ የወጣው ደጃዝማች ተፈሪ መኮንን በሸረቡት ሴራ መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱን ከምኒልክ ዙፋን ላይ በገለበጡበት ዕለት የልጅ ኢያሱን ከስልጣን መውረድ እንዲያፀድቁ ከንቲባ ወልደፃድቅ ሕዝብ በተሰበሰበበት ሸንጎ ላይ በጠየቋቸው ጊዜ ባሳዩት መወላወል እንደሆነ የሴራው ቀንደኛ አስተባባሪ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም “ሕይወቴ” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ላይ ዘርዝረውታል (ገፅ 296)
አፄ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን በተወገዱበት ወቅት የነበሩት አቡነ ቴዎፍሎስም ባገር ደረጃ የእልቂት ዳመና ባንዣበበበት ወቅት አቋመ ብርቱነት የከዳቸው ሌላው ጳጳስ ነበሩ፡፡ ኋላ ላይ ተይዘው መረሸናቸው ላይቀር ለአፄ ኃይለሥላሴ የገቡትን መሀላ አፍርሰው ከደርግ ጋር ለመሥራት ነበር የሞከሩት፡፡ ይኸንን የጳጳሱን መገለባበጥና ከደርግ ጋር ለመስራት ዳር ዳር ማለት የታዘቡት ደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ “ሕይወቴ” በሚለው ባለ636 ገፅ ቅፅ 1 መፅሐፋቸው ላይ ሲያብራሩት እርሳቸው ከጳጳሱ ቤት በመሄድ የንጉሡን አላግባብ መታሰር ይቃወሙ ዘንድ ሥልጣናቸውን ለሌላ ጳጳስ አስረክበው በምነና እንዲቀመጡ ሲጠይቋቸው “አየ ደጃዝማች ይቺ ነፍስኮ ታሳሳለች” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ገልፀው “ይቺ ነፍስ ታሳሳለች” ያሉት አባባል ምንነቱ እስካሁን ግልፅ እንዳልሆነላቸው ያብራራሉ (ገፅ 534)
ወያኔ ኢሕአዴግ ሥልጣን ይዞ የመለስ ዜናዊ አሸርጋጅና በአማራ ሕዝብ መጨፍጨፍ ዙሪያ ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚሆነው ታምራት ላይኔ በሰጠው ግልፅ ድጋፍ አቡነ መርቆሬዎስን በማባረር ከመንበረ ሥልጣኑ ላይ የወጡት አቡነ ጳውሎስ በበኩላቸው የሚታወቁት በመንፈሳዊነቱ ዙሪያ በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ የነፍስ ልጆች በነበራቸው አርአያነት ሳይሆን በጎጥ አምላኪነት በተዋቀረው ፖለቲካ አራማጅነታቸው ነበር፡፡ በአቡነ ጳውሎስ የጵጵስና ዘመን ባገር ደረጃ እጅግ በርካታ አማኞች ብቻ ሳይሆኑ ካህናትና ቀሳውስት ጭምር ባንድ እጃቸው መስቀል በሌላው እጃቸው ደግሞ የኢሕአዴግ ልሳን የነበረችውን አዲስ ራዕይ ይዘው የሚዞሩ መንፈሳዊነትን በሸቀጥነት ለገበያ ትርፍ ያቀረቡ አባ ለነፍሱ ሳይሆን “አባ ለከርሱና አባ ለልብሱ” የሚል የዳቦ ስም የወጣላቸው ዋሾ ሀሳዊ መሲሆች እንደአሸን የፈሉበት ዘመን ነበር፡፡
ከ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ጀምሮም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመከራ ማስታወሻ ሆኖ በሚታሰበውና ከራስ ላይ በሚደፋው የሾህ አክሊል ምሳሌ ላይ የኢሕአዴግ የምርጫ ምልክት የነበረችውን የንብ አርማ ለጥፈውና በንዋየ ቅዱሳት አልባሳት አሸብርቀው በከበሮ ታጅበው ሳይጠሩ የኢሕአዴግ የስብሰባ አዳራሽ አድማቂ ቀሳውስት በረከቱ፡፡
በዚህ ዘመን ነው በቤተ እምነቷ ዙሪያ ውሸት፣ ጉቦኝነት፣ ተቋማትን በወንዜ ልጅ መሙላትና ወዘተ ወዘተ የተስፋፋውና ቤተእምነቷ ሙሉ በሙሉ በመንፈሳዊነት ሳይሆን በፖለቲካ ጠረን መሞላቷ ጎልቶ የወጣው፡፡ በዚህ ዙሪያ ያቀረብኩት ትዝብት በመረጃ መደገፍ ስላለበት በቤተክህነት እውቀታቸው ዙሪያ አንቱ ተብለው ይከበሩ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ ከአባ ጳውሎስ ጋር ያደረጉትን እልህ አሰጨራሽ ትግል በዝርዝር የሰፈረበትን አባቴና እምነቱ የሚለውን የስምረት አያሌውን መጽሐፍና በቤተ እምነቷ አካባቢ የነበረውን የጉቦ አቀባበል ስልት የሚዘረዝረውን… “የሰው ያለህ” በሚል ርዕስ የተፃፈዉን የመምህር ብሩክ ገብረሊባኖስን መጽሐፍ በዋቢነት አቅርቤ ወደሌላው ልለፍ፡፡
በኔ እይታ አቡነ ጳውሎስን የተኩት አቡነ ማትያስም ቢሆኑ በሀገር ደረጃ የሚገኙ የነፍስ ልጆቻቸውን ሳይሆን ለጎሳና ነገዳቸው የሚያደሉ አባት ስለመሆናቸው ባለፈው ዓመት ከትግራይ ሚዲያ ሀውስ ጋር ካደረጉት ቃለምልልስ መረዳት ይቻላል፡፡ ያኔ በቃለምልልሳቸው የትግራይ ህዝብ ከምድረ ገፅ እንዲጠፋ ተፈረደበት አሉን እንጂ አማራና አፋር ላይ የእርሳቸው ወገኖች ስለጨፈጨፉት ያዳም ዘር የተነፈሱት ነገር የለም፡፡
መቸም ነገሩ ከተነሳ አይቀር ሌላው ትዝ ያለኝ አንድ አሰገራሚ ትዝብት ላንሳ፡- በአቡነ ማትያስ ሰብሳቢነት ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ በተካሄደ ጉባዔ ላይ አንድ ተሰብሳቢ መንፈሳዊ አባት በዚያ ወቅት እጅግ አስፈሪ ቅጣት ያሰጥ በነበረው የአሸባሪነት ወንጀል ተፈርጆ የነበረውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት)ን እና የማህበረ ቅዱሳንን አንድነትና አብሮነት በመግለፅ ማኅበረ ቅዱሳንን አሸባሪ ነው ብለው ለማስፈረጅ በዚያ የስብሰባ አዳራሽ የሀሰት ምስክርነት የሰጡት በቀኝ እጃቸው የያዙትን ሀጢያት ያነፃል ብለን የምናምንበትን መስቀል ሳይፈሩ ነበር፡፡ ያን ውሸት ውሸት ይናገራሉ ብየ ካልጠበቅሁት መንፈሳዊ አባት በሰማሁበት ወቅት ትዝ ያለኝም የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ቁጥር13 ላይ “ቤተመቅደሴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት” ያለው የጌታ ቃል ነው፡፡
ከላይ በዝርዝር ለማሳየት የሞከርኩት የአባቶቻችን መንፈሳዊ ድህነት ትኩረት ተሰጥቶት በጊዜ ካልታረመ ልጆቻችን ከኛ የሚወርሱት አርዓያነቱ የጎላ መንፈሳዊ ዕሴትን ሳይሆን ጥቅመኝነት የሚያይልበትና ለትርፍ ማጋበሻነት የሚያገለግል በሸቀጥነት የሚቀርብ ዕምነትን ነው፡፡ ዕምነት ከዕምነትነቱ ወጥቶ የገበያ ሸቀጥ ከሆነ ደግሞ ለአርዓያነት የሚጠቀስ ሥነምግባር ሙቶ ይቀበራል፡፡ ያኔ ሀገር የቁልቁለት ጉዞ ሽክርክሪቷ በእጥፍ ይጨምራል እንጂ የእድገት ፈር ቀዳጅነቷ በፍፁም አይጨምርም፡፡ ስለዚህ ዛሬ በአማኑ ቀን ልብ ያለው ልብ ይበል ጆሮ ያለው ይስማ ዐይን ያለውም ሥጋታችንን ይመልከት ቅን አዕምሮ ያለውም ትዝብታችንን ይጋራ የምንለው፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ይታደጋትም!
