“እንድንደራጅ በተደረገበት መመሪያ መሰረት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እስኪሰጠን ድረስ ህጋዊ እና ሰላማዊ የሆነው ጥያቄያችን ማቅረብ እንቀጥላለን” ሲሉ በመቀለ ከተማ 70 ካሬ የመኖሪያ ቦታ ለመውሰድ የተመዘገቡ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ትላንት ሚያዚያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ፊት ለፊት ባካሄዱት ሰልፍ በቅርቡ የጸደቀው መመሪያ 9/2017 አይመለከተንም፡ ተመዝግበን እና ገንዘብ በመቆጠብ እንድንደራጅ የተደረግንበት መመሪያ 4/2011 ነው ልንዳኝ የሚገባን ሲሉ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
አዲሱ መመሪያ ወደ ኋላ ተመልሶ እኛ ላይ ተፈጻሚ ሊሆን የሚያስችል ምንም አይነት የህግ አግባብ የለም ሲሉ አስታውቀዋል።
ለትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረዳ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ጽ/ቤታቸው ፊት ለፊት የተገኙት ሰልፈኞቹ ለስድስት አመታት ተደራጅተን ገንዘብ እየቆጠብን ያለነው 70 ካሬ ቦታ ለማግኘት እንጂ ለአፓርትመንት አይደለም፤ በተደራጀንበት መመሪያ መሰረት አፋጣኝ ምላሽ ይሰጠን የሚሉ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ለአንድ አመት ያክል ወደ ከተማዋ ጎዳናዎች በመውጣት ጥያቄያቸንን ስናቀርብ ነበር ሲሉ የገለጹት ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የሆኑት አቶ ሓጋዚ ንጉስ ለችግሮቻችን መፍትሔ የሚሰጠን አካል አላገኘንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጥያቄዎቻችንን እንኳ በሰላማዊ ሰልፍ እንዳንቀርብ ገድቦን ነበር ያሉት አቶ ሓጋዚ የፖለቲካ ችግሩ አሁን ላይ ለጊዜውም ቢሆን መፍትሔ አግኝቷል ብለን እናምናለን፣ ለዚህም ነው ፕሬዝዳንቱ ጋር ጥያቄያቸንንም ለማቅረብ የተገኘነው ሲሉ አስታውቀዋል።
ዛሬ ጥያቄያቸንን ባቀረብንበት ወቅት ተወካዮቻችሁን ሚዲያ ሳታስከትሉ መግባት ትችላላችሁ ተብለን ነበር ሲሉ የጠቆሙት ሓጋዚ ጥያቄያችን ከመገናኛ ብዙሃን የተሸፈነ አይደለም የሚል ምላሽ በመስጠታችን እስካሁን ከአስተዳደሩ በኩል ምንመ አይነት ምላሽ የሚሰጠን አካል አላጋኘንም ሲሉ ገልጸዋል።
ለመኖሪያ ቤት መስሪያ 70 ካሬ ሜትር ይሰጣችኋል ተብለው ገንዘብ ሲቆጥቡ የነበሩ የመቀለ ከተማ ነዋሪዎች ከአምስት አመት ጥበቃ በኋላ የመኖሪያ ቤት አሰራር ተቀይሯል፣ የሚሰጣችሁ መሬት የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ነው መባላቸውን በመቃወም ሰልፍ መውጣታቸውን የተመለከተ ዘገባ በተያዘው አመት 2017 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ማቅረባችን ይታወሳል።
በመንግስት ድጋፍ ቤታቸውን ለመስራት ለአምስት አመታት ሲጠባበቁ የቆዩት የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች አሁንም ገና ጥያቄያቸው እንዳልትፈታና ይልቁን ሌላ አማራጭ እንዲቀበሉ እየተገደዱ መሆኑን በመጠቆም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሮጀክቱን በግለሰቦች እንዲሰራ ከታቀደ G+1 መኖሪያ ቤቶች ወደ ሰባት ፎቅ ህንጻዎች ለማሸጋገር ድንገተኛ ውሳኔ መስጠቱ ተቃውሞ ማስነሳቱ በዘገባው ተመላክቷል።
በተለምዶ “70 ካሬ” በመባል የሚታወቀው ለእያንዳንዱ ተሳታፊ 70 ካሬ ሜትር ቦታ እንደሚሰጥ በገባው ቃል የተሰየመው ይህ ውጥን ከአምስት ዓመታት በፊት በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና መቀሌ መጀመሩ ይታወሳል።
