የቻይና አካል ኾና በራስ ገዝ የምትተዳደረው ሆንግ ኮንግ ከሲጋራ የፀዱ አካባቢዎችን ለመፍጠር የተለያዩ ጥብቅ እርምጃዎችን ስትወስድ ቆይታለች። ከሰሞኑ ደግሞ አጫሾችን አፍጥጦ በመመልከት ሲጋራ የሚጨስባቸውን ቦታዎች ለመቀነስ እየሞከረች ትገኛለች፡፡ የቁጥጥሩ ሂደቱም ፍሬ ያፈራ ይመስላል። በ1980ዎቹ ከሕዝቧ 23 በመቶ የሚኾነውን ሲጋራ አጫሽ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሏን ሀገሪቱ ያወጣችው መረጃ ያመላክታል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በሕግ ደረጃ ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ማጨስ የሚያስችል ሕጋዊ መብት ባይኖርም አጫሾች በሕዝብ መካከል በተለይም በየትራንስፖርት ጣቢያው በየምግብ ቤቱ ማጨስ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ያጨሳሉ፡፡ ዜጎች ሕግ የፈቀደላቸውን መብት ተጠቅመው ከሲጋራ ጭስ የመጠበቅ መብታቸውን እንዳያስከብሩ አስፈጻሚው አካል ተግባራዊ ሊያደርግላቸው አልቻለም፡፡ ይህ በመኾኑም አሁን ላይ በሀገሪቱ ከተሞች ሲጋራ በማጨስ ሰዎችን መረበሽ ከልካይ የሌለው ሕጋዊ መብት መስሏል፡፡ በየአደባባዩ በየቦታው በአጫሾች ሳቢያ ሲጋራን ያለፍላጎት መማግ የተራው ሕዝብ ሁሌያዊ ድባብ ኾኗል፡፡
በአንጻሩ ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ጠንካራ ቅጣት የሚጥል ደንብ እየተዘጋጀ መኾኑን ገልጾ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በከፊልም ቢኾን ችግሩን ለመከላከል የሚደረገው ቁጥጥር እንደቀጠለ ቢኾንም በሕዝብ መሰብሰቢያና ባልተፈቀዱ ቦታዎች ሲጋራ የሚያጨሱ ግለሰቦች መበራከታቸው የማይደበቅ ነው፡፡ ኾኖም ግን እንደብዙዎች እምነት የትንባሆ ቁጥጥር አዋጅ በአገር አቀፍ ደረጃ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ቁጥጥሩ ላይ ምን ያህል መሻሻል አሳይቷል የሚለው አጠራጣሪ ነው። በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች በነፃነት ትምባሆ የሚጨስበት መንገድ ላይ ተገቢውን ቁጥጥር ማድረግ ካልተቻለ የሚጎዳው ሕዝብ ብዙ ነው፡፡ በቅርቡ በወጣ ጥናት እንኳን በኢትዮጵያ ከትንባሆ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ምክንያት በቀን 46 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተመላክቷል። በሀገራችን በተለይ የሲጋራ ዋጋ አነስተኛ መኾኑ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል አድርጎታል። በጥቅሉ “ሲጋራ ማጨስ ለጤና ጎጂ ነው” በማለት ብቻ ችግሩን ማስቆም ስለማይቻል አሁንም የሚመለከተው አካል ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡
