
ህዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወቅት ሲያከናውናቸው የቆዩትን የበጎ አድራጎት ተግባራት በሌሎች ወራትም መቀጠል እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ተናገሩ።
ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ 1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-ፊጥር በዓልን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፥ ለእምነቱ ተከታዮች እንኳን ለ1 ሺህ 446ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-ፊጥር በዓል አደረሳችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የረመዳን ወር በአንድነት፣ በፍቅር፣ በአብሮነት፣ በመተጋገዝና በመደጋገፍ ማለፉን ተናግረዋል።
ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ አል-ፊጥር በዓልን ሲያከብር በጾም ወቅት ሲያደርገው እንደነበረው እርስ በርስ በመደጋገፍና ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሰላም ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ እያንዳንዱ ምዕመን ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ማመልከታቸውን ተዘግቧል ።