ለድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን(ቴዲ አፍሮ) መልካም ምኞታችንን እየተመኘን በድርጅታችን ሰዋሰው መልቲሚዲያ እና በድምፃዊው በኩል የነበረው ውል የተቋረጠው በስምምነት መሆኑን እና ግንኙነታችን ዛሬም እጅግ ጤነኛ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከረጅም አመታት በኋላ “ኢቶሪካ” በሚል መጠሪያ ይዞት የመጣው አልበም ሊለቀቅ በተቃረበበት ወቅት በድምጻዊውና በድርጅታችን ሰዋሰው መልቲሚዲያ መካከል የነበረው ውል መቋረጡ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም ከሰሞኑ ድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ከሰዋሰው ጋር የነበረውን ውል ማፍረሱን የተመለከቱ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡ በዚህም ምክንያት በርከት ባሉ የድምጻዊ ቴዲ አፍሮ አድናቂዎችና በድርጅታችን ሰዋሰው መልቲሚዲያ ወዳጆች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ይህንን ተከትሎ ድርጅታችን ስለተፈጠረው ነገር ማብራሪያ ለመስጠት ተገዷል፡፡
ድምጻዊ ቴዲ አፍሮና ሰዋሰው መልቲሚዲያ የአብሮ መስራት ውል የተፈራረሙት ከአልበሙ የመለቀቅ ዜና በኋላ ሳይሆን ከዛሬ 3 አመት ከ8 ወር በፊት ሲሆን ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ደግሞ የአልበም ስራውን አጠናቆ ለማስረከብ የአንድ አመት ጊዜ ወስዶ ነበር።
ሆኖም ድምጻዊው በነዚህ ጊዜያት ወስጥ የአልበም ስራውን ለማጠናቀቅ የወሰደውን ተጨማሪ ጊዜ በመረዳት መልቲሚዲያችን በትዕግስት ሲጠብቀው ቆይቷል፡፡
ከዚህ ሁሉ ግዜ በኋላ ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ እና ሰዋሰው የነበራቸው ውል የተቋረጠው በሌላ የውል ማሻሻያ ሃሳብ እንጂ እንደሚባለው በነበረው የቀደመ ውል ላይ አለመግባባት ተፈጥሮ አይደለም፡፡
ከሰሞኑ ከሚናፈሱት የተሳሳቱ መረጃዎች ውስጥ አንዱ “ውሉ የፈረሰው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ሊለቀው ካዘጋጀው አልበም ውስጥ ሰዋሰው እንዳይካተቱ የሚፈልጋቸው ስራዎች አሉ” የሚለው አንዱ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ድርጅታችን ይህ ፈጽሞ የተሳሳተ መረጃ መሆኑን ለመግለፅ ይወዳል ፣ በተጨማሪም ከድምፃዊው ጋር በሙዚቃዊ ይዘት ላይ ተነጋግረን ካለማወቃችን በላይ ሰዋሰው የድምጻዊ ቴዲ አፍሮን አዲስ አልበም እስካሁን አዳምጦ እንደማያውቅ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
ለስምምነቱ መቋረጥ በምክንያትነት የተወሰደው ጉዳይ በተለምዶ ሲ አር ቢ ቲ (CRBT) ተብሎ የሚታወቀው የመጥሪያ ድምጽ ማሳመሪያ ጉዳይ “በማን ይሁን?” የሚል መከራከሪያና የሃሳብ ልዩነት መፍጠሩ አንደኛው ሲሆን፡፡
በውሉ መሰረት የ ሲ አር ቢ ቲ (CRBT) መብት የሰዋሰው የተሰጠ ሲሆን መልቲሚዲያው ከድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ጋር በተፈጠረው የሃሳብ ልዩነት ብቻ ላለመራራቅ ሌላ መፍትሄ ይዞ ቀርቦ ነበር፡፡ ይህም የድምፃዊ ቴዲ አፍሮ የቀደሙት ስራዎች በሰዋሰው መተግበሪያ ላይ ተጭነው ተጨማሪ ክፍያ ለድምፃዊው ለመክፈል የሚል ሃሳብ ቢቀርብም የአማራጭ ሃሳቡን ድምፃዊው ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
በአንጻሩ ከድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በኩል ሌላ መፍትሄ ቀርቧል መፍትሄውም” የአልበሙ ከፊል ሙዚቃዎች በድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ዩቲዩብ ቻናል፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በሰዋሰው መልቲሚዲያ ይለቀቁ” የሚል ነበር ይህን ደግሞ ሰዋሰው መልቲሚዲያ ሃሳቡን ሳይስማማበት ቀርቷል፡፡
ድምጻዊ ቴዲ አፍሮና የሰዋሰው የስራ ግንኙነት ሂደቱ እስከዚህ ደረጃ ቢሆንም ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ለሰዋሰው መልቲሚዲያ የ3 አመት ከ8 ወር ወለድን ጨምሮ ክፍያ መልሷል ፤ በዚህም ምንም አይነት ያለመግባባት እንዳልተፈጠረ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
ሰዋሰው መልቲሚዲያ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ከሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በነገው እለት ለሚለቀው ‘ኢቶሪካ’ ለተሰኘ አዲስ አልበም መልካም ምኞታችንን እየገለፅን፤እንዲሁም እስካሁን ስለነበረን መልካም የስራ ግንኙነት ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለን፡፡
ሰዋስው መልቲሚዲያ
