ከአንድ ሳምንት በፊት የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሳ ቢሂ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ልዑካን እና የዲፒ ወርልድ ዳይሬክተር ሱልጣን ቢን ሱለይማን በተገኙበት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ በይፋ ሥራ መጀመሩ ተገልጾዋል። በዲፒ ወርልድ 51%፣ በሶማሊላንድ 30% እና በኢትዮጵያ 19% ድርሳ የተያዘው የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት 500 ሺህ ኮንቴነሮችን መያዝ የሚችል ተርሚናል እንደሆነና በዓመት አንድ ሚልዮን ኮንቴነሮችን ማስተናገድ የሚችል መሆኑም ታውቋል።
ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ወደቡን ከሚያስተዳድረው የዱባዩ ዲ ፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር የተጋራችው ከሦስት ዓመታት በፊት ነበር። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለገቢ እና ወጪ ንግዷ ለመጠቀም የሚያስችላትን መሰረተ ልማት እንደምታለማ ተገልጾ ነበር። በወቅቱ የኢፌዴሪ የትራንስፖርት ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴም ኢትዮጵያ ተከታታይ ድርድርን ከሶማሌላንድ እና ከዲፒ ወርልድ ግሩፕ ጋር ካካሄደች በኋላ በበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ማግኘቷን ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም። ሰሞኑን በነበረው የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ መታደማቸው ይኽንን ያረጋግጣል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ የወደብ ድርሻ መግዛቷ ግን የሞቃዲሾውን መንግሥት አላስደሰተም ነበር፤ በዚህም ሳቢያ የሶማሊያ ፓርላማ “ሉአላዊነታችን ተነክቷል” በማለት ስምምነቱን ውድቅ እስከማድረግ ደርሶ ነበር። የሶማሌላንዱ ፓርላማ ግን ወዲያውኑ ስምምነቱን አፅድቆታል። ሶማሌላንድ ከትልቋ ሶማሊያ ተነጥላ ራስ ገዝ አስተዳደር ሆና ራሷን ማስተዳደር ከጀመረች ረዥም ዓመታት ቢቆጠሩም የሀገርነት እውቅና ግን እስካሁን አልተሰጣትም፡፡ በጎሳ (ኢሳ፣ ገደቡርሲ፣…) ግጭቶች፣ አልሸባብን በመሳሰሉ የሽብር ቡድኖች ወዘተ የሚታመሠው ይህ ቀጠና ደካማ መንግሥታዊ ሥርዓትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር በማስቻሉ ሱማሌላንድ ወደቡን ለኢኮኖሚያዊ ትስስርና እድገት ስትጠቀምበት እምብዛም አይታይም፡፡
በበርበራ ወደብ ዙሪያ ጉዳዩን ከሉዓላዊነት ጋር በማያያዝ “ያዙኝ ልቀቁኝ” ስትል የነበረችው ትልቋ ሶማሊያም በሰሞኑ ሁኔታ ግን ዝምታን መርጣለች፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ወደብ ሥራ መጀመርን ተከትሎ የታሪክ ባላንጣዋ ግብፅ ውስብስብ ሴራ በአልሸባብ፣ በሱማሊያና በጅቡቲ መንግስታት በኩል ተሾርቦ በአዲስ መልክ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ግብፅ ሱማሊያና ጅቡቲ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በቀላሉ እጃቸውን ጠምዝዛ ለፍላጎቷ ማሳኪያ ማድረግ አይሳናትም፡፡ ወትሮም ቢሆን የወደቡን ስምምነት የተቃወመችው ትልቋ ሶማሊያና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷ የሚቀንሰው ጅቡቲም ለግብፅ ሴራ እጅ ለመስጠት እንደምክንያት የሚወስዱት መነሻ አላቸው፡፡
ከሁለቱ ሀገራት በተጨማሪ የቀንድ አፍሪካ የአመታት ስጋት የሆነው “አልሸባብ” የተሰኘ የሽብር ቡድንም ከግብፅ በኩል በሚያገኘው ድጋፍ አቅሙን አጎልብቶ የወደብ እንቅስቃሴው ላይ ከባድ ስጋት ሆኖ ይመጣል የሚል ስጋት አለ፡፡ በሌላ መልኩ ከሽብር ስጋትና ከጂኦፖለቲካው ውጥረት በአንፃሩ የተሻለ የሚሆነውና በህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ እ.አ.አ በ2010 ጀምሮ በኬንያ ላሙ ግዛት በመንግስት እየተገነባ ያለው “የላሙ ወደብ” ለኢትዮጵያ ከበርበራ ወደብ የተሻለ አማራጭ ይሆናል፡፡ ሆኖም ሁለቱም ወደቦች ለኢትዮጵያ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ለኢትዮጵያ የወደብ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው የራሳችን የነበረውን የአሰብ ወደብ መልሰን የምንጠቀምበት ሁኔታ ሲፈጠር ብቻና ብቻ ነው የሚለው የበርካታ ምሑራን አስተያየት ነው፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ከዚህ ቀደም አስተያየታቸውን ሰጥተው የነበሩት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ላይ የገዛችው የ19 በመቶ ድርሻ የወደብ ችግርን በመጠኑም ቢሆን ፋታ ይሰጥ ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ብለው አያምኑም። እንደ እርሳቸው ሃሳብ ከሆነ የወደብ ችግራችን ሙሉ በሙሉ ሊፈታ የሚችለው አሰብ ወደ ኢትዮጵያ እጅ ሲገባ ብቻ ነው። እንደ ዶ/ር ያዕቆብ ከሆነ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ እና ሶማሌላንድ የአረብ ሊግ አባል ሀገራት ናቸው። እነዚህ ሀገራት እርስ በእርስም ቅርበት አላቸው። እንዲሁም ጅቡቲ ከበርካታ ሀገራት ጋር ስትራቴጂካዊ ትስስርን ፈጥራለች።
“ወደቦቿን ቻይናዎች፣ እንግሊዞች፣ ፈረንሳዮች እና ግብፆች ይጠቀሙታል። ግብፅም ብትሆን ወታደራዊ ማዕከል በኤርትራ መስርታለች። ይህ ብቻ ሳይሆን ግብፅ በደቡብ ሱዳንም ወታደራዊ ማዕከል አላት” በማለት የስጋቱን ግዝፈት ለማሳየት ዶ/ር ያዕቆብ ይሞክራሉ። ግብፅ በሶማሌላንድም የወታደራዊ ማዕከል ለመመስረት ስምምነት እያደረገች ነው ሲሉ በስጋቱ ላይ ሌላ ስጋት እንዳለ ያሳያሉ። ስለዚህ ለዶ/ር ያዕቆብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኢትዮጵያ በአረብ ሀገራት ተከባለች ማለት ይቻላል። ስለዚህ እያንዳንዱ ውሳኔዋን ከጂኦፖለቲካዊ ጥቅም አንፃር መፈተሽ ተገቢ ነው።
በበርካቶችዘንድ እንደ ዘላቂ መፍትሄ ተደርጎ የሚወሰደው ታዲያ ከኤርትራ ጋር መደራደር ነው። ኤርትራ ከእናት ሀገሯ ኢትዮጵያ ጋር በ1952 በፌዴሬሽን ስትቀላቀል የተባበሩት መንግሥታት ሰነድ “የኢትዮጵያ ሕጋዊ የሆነ ወደ ባህር የመዝለቅ መብቷ እንዲጠበቅ ኤርትራ በፌዴሬሽን ተቀላቅላለች” ይላል። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በአሰብ ላይ የነበራትን መብት ያጣችው በኢህአዴግ ስህተት ስለሆነ የባህር በር የማግኘት መብቷ መረጋገጥ አለበት የሚለው የበርካቶች ሃሳብ ነው። የባህር በር ማጣት የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የህልውናም አደጋ ስላለውም ጭምር፣ ኢትዮጵያ ደህንነቷን ለማረጋገጥ ከኤርትራ ጋር ተደራድራ አሰብ ወደብን በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋታል።
በሌላ በኩል ወደቦችን በማስተዳደር የተሰማሩ የአረብ ሀገራትን ኢትዮጵያ በጥንቃቄ ልትመለከታቸው ይገባል የሚል ሃሳብም ይደመጣል። እነዚህ ድርጅቶች ከፖለቲካ የጸዳ እንቅስቃሴ ይዘው መምጣታቸው እና አለመምጣታቸው በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በዚህ አካባቢም ሆነ በአረብ ሀገራት የግብፅ ተፅእኖ ቀላል አለመኾኑ ቀዳሚ ምክንያት ነው፡፡
የበርበራ ወደብ በደቡብ እና በደቡብ ምዕራብ ለሚገኙ የኢትዮጵያ አካባቢች ስትራቴጂካዊ ጥቅም አለው። በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ አማራጭ ወደብ በመፈለጓ ምክንያት በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል የሚፈጠር አለመግባባትም፤ ልክ እንደ እስከዛሬው ሁሉ በመነጋገር የሚፈታ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። በወደብ አጠቃቀም ዙሪያ ሊከሰቱ የሚችሉ አለመግባባቶች ወቅታዊ ሁኔታን የሚከተሉ በመሆናቸው ጥርስ የሚያናክስ ላይኾኑ ይችላሉ። ኾኖም በበርበራ ወደብ ላይ ከፍተኛውን የባለቤትነት ድርሻ ያዘው የዱባዩ ኩባንያ ቢሆንም የሶማሊያ ፓርላማ አባላት የቅሬታ ትኩረት ግን በኢትዮጵያ ተሳትፎ ላይ ነው። ይህም ሠራዊቱን አሰማርቶ ከአልሸባብ ጋር እየተፋለመ ያለውን የኢትዮጵያን መንግሥት ቅር ማሰኘቱ አይቀርም። ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ የሚያስችል ስምምነትን ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው2008 ዓ.ም ላይ ነው። ሀገሪቱ 30 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግዷ በበርበራ ወደብ በኩል እንዲወጣ ብትፈልግም እስካሁን 97 በመቶ የሚሆነው የወጪ ንግዷ በጂቡቲ ወደብ በኩል ነው እየተካሄደ ያለው። ከአንድ ሳምንት በፊት የበርበራ ወደብ የመጀመሪያ ዙር ማስፋፊያ ፕሮጀክት ተመርቆ በይፋ ሥራ መጀመር ግን ይኽንን ጨምሮ ሌሎች ለውጦችን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ከምንም በላይ በጉዳዩ ድምጹዋን በይፋ ያላሰማችው ሶማሊያ በዚህ የኢትዮጵያ ውሳኔ ሳቢያ የመልክዐ ፖለቲካውን ቅርጽ ሊቀይር ወደሚችል እርምጃ ውስጥ እንዳትገባ መንግሥት ጥልቅ ክትትልና መፍትሔዎችን ማሰናዳት እንደሚኖርበት ብዙዎች ያሳስባሉ፡፡
