(ታሪካዊው የኢትዮጵያውያን ገዳም እና ኮሌጅ)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ከመንበረ ፓትርያርክ፣ ከልዩ ጽ/ቤትና ከውጭ ግንኙነት ከተወከሉ ልኡካን ጋር ኃሙስ የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ/ም ማታ ከአዲስ አበባ ተነስተው ዐርብ ጠዋት የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ/ም ሮም ከተማ ፉሚችኖ ሊዎናርዶ ዳቪንቺ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ ደርሰው ታሪካዊ እና ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በሊዮናርዶ ዳቪንቺ አየር ማረፊያ በተለየ የእንግዳ መቀበየ ቦታ በቫቲካን ከተማ የብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ፋራንሲስ ተወካይ የሮም ጳጳስ ብፁዕ ፋረል፣ የቫቲካን የውጭ ግንኙነትና በብፁዕ ወቅዱስ ሐዋርያዊ ጉባኤ የክርስቲያኖች ኅብረት ጽ/ቤት ዋና ጸሓፊ ማንሲኞር ፋዘር ገብርኤል ኩዊኬ ሲገኙ በተጨማሪም በሮም፣ በፈረንሳይና በቫቲካን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት አምባሳደሮች አምባሳደር ነጋና አምባሳደር ሙሉጌታ ከቆንሲላ ጽ/ቤት ሠራተኞቻቸው ጋር ተገኝተው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የክብር አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብና ምሥራቅ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ፣ በጣሊያን ከሚገኙ የልዩ ልዩ ክፍለ ሀገራት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት አለቆች፣ በጣሊያን ሮም ከተማ የሚገኙት የሁለቱ አጥቢያዎች የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያምና የደብረ ከነዓን ቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት ልብሰ ተክህኖ የለበሱ አገልጋይ ካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ደማቅ መንፈሳዊ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
በፉሚችኖ ሊዮናርዶ ዳቪንቺ አየር ማረፊያ የተደረገው አቀባበል እንደተጠናቀቀ በተዘጋጀላቸው ልዩ መኪና ወደ ቫቲካን ከተማ ሳንታ ማርታ የዓለም ዐቀፍ ከፍተኛ ልኡካንና እንግዶች ማረፊያ አምርተዋል፡፡ በዚያም መጠነኛ ዕረፍት በማድረግ በዕለቱ በተዘጋጀው መርሐ ግብር መሠረት ሐዋርያዊ ጎብኝታቸውን ጀምረዋል፡፡
በዚሁ ዕለት ማለትም ዐርብ የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ/ም ከሰዓት በኋላ ከሐዋርያት አንዱ የሆነውና ታላቁ ሰማዕት ሊቀ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራልና የቅዱስ ጴጥሮስን መካነ መቃብር ጐብኝተዋል፣ ጸሎተ ኪዳንም ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አድርሰዋል፡፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል “Papal Basilica of St. Pe-ter” በመባል ይታወቃል፡፡ ይኽ ካቴድራል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በዓለም ትልቁ ካቴድራል ነበር፡፡ ቦታው ቅድመ ክርስትና የሮም ነገሥታት መዝናኛ እንደነበር ይነገራል። ቄሳር ኔሮ በክርስቲያኖች ላይ አስከፊውን የጭፍጨፋ አዋጅ ሲያውጅ ይኽ ቦታ የኔሮ ሰርከስ መጫወቻ ነበረ። በዚሁ አደባባይ በ64 ዓ/ም ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ሲያርፍ ደሙ የፈሰሰበትና የተቀበረው በዚሁ ቦታ ነበር።
የቅዱስ ጴጥሮስን መቃብርም ክርስያኖች በመከራም ውስጥ ሁነው ይጎበኙትና ይሳለሙት ነበር፡፡ በ324 ዓ/ም ታላቁ ቈስጠንጥንዮስ የቅዱስ ጴጥሮስን መቃብር ማእከል አድርጎ አንድ ካቴድራል ሠራ፡፡ ቤተ መቅደሱ በጊዜ ብዛት እያረጀ በመምጣቱ በዐሥራ አምስተኛውና ዐሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ከፍተኛ ግንባታ ተከናውኖበታል፡፡ የአሁኑ ካቴድራል በሚያዚያ ወር 1506 ዓ/ም ተጀምሮ በኅዳር ወር 1626 ዓ/ም ተጠናቋል፡፡ ካቴድራሉ በአንድ ጊዜ 20,000 (ሃያ ሺሕ) ሰው ይይዛል። የቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር አሁን ካለው ትልቁ መንበር ሥር ይገኛል፡፡ የሮሙ ፖፕ በዚህ መንበር ላይ ጸሎተ ቅዳሴ ሲያደርሱ በውስጥ እና በውጭ ሁነው ከ15-80 ሺሕ ሕዝብ ይሳተፋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በቫቲካን በሚደገፉ ታላላቅ አርኪዎሎጅስቶች ከዚህ ካቴድራል ሥር ባደረጉት ቍፋሮ በርካታ ጥንታውያን የቅድመ ክርስትናና የክርስትና ዘመን ቅርሶች አግኝተዋል፣ አብዛኛዎቹም ባሉበት በዚሁ ካቴድራል ሥር እንዳሉ ሁነው ይጐበኛሉ፡፡
ቱሪስቶች በሚጐበኙበት ጊዜ የካቴድራሉ አስጎብኝዎችና ካህናት ሰፊ ገለጻ ሲያደርጉላቸው የካቴድራሉን ሥርዐት ጠብቀው ይጐበኛሉ፤ ማለትም አጭር ቀሚስ፣ ቊምጣ ሱሪ እና ደረትን ገልጦ የሚያሳይ አልባሳት መልበስ አይፈቀድም። ካቴድራሉን ለመጐብኝት ለሚሰጠው አገልግሎት እንደ ጒብኝቱ ስፋትና የአገልግሎት መጠን በጒብኝት ወቅት ከ15 እስከ 64 ዩሮ ድረስ ይከፍላሉ፡፡ አገልግሎቶቹም ለምሳሌ በዐሥር ቋንቋ በጣሊያንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በስቴንኛ፣ በፖርቱጋልኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በራሽኛ፣ በፖላንድኛ፣ በጃፓንኛና እና ቻይንና ቋንቋዎች የሚያስተርጒሙ ወይም ገለጻ የሚያደርጉ አስጎብኝዎች፣ የሕንጻውን ክፍሎች ፎቶ ለማንሳት፣ ለመሳሰሉት ይውላል፤ ይኽም በቀጥታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሚውል ገቢ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያውያን ቤተ መቅደስ መጐብኘታቸው፤
ቀደም ባሉት ጊዜያት በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያን የሆኑ ወደ ሮም ሂደው የቅዱስ ጴጥሮስንና የቅዱስ ጳውሎስን መቃብራት፣ ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ሰማዕነት የተቀበለባቸውን አደባባዮች ከኢየሩሳሌም ቀጥለው ይጎበኙ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከእነዚህ ጐብኚዎች መካከል ኢትዮጵያዊው አባ ተስፋ ጽዮን በሰፊው ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ መልኩ ወደ ሮም ይሄዱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ቊጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ አንድ ቦታ ተስጥቷቸው እንደነበር በታሪክ ተጠቅሷል፡፡ ይኽም ቦታ በአሁኑ ጊዜ “ቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያ ኮሌጅ” በመባል ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ቦታ የራሳቸው መተዳደሪያ ሕግ ሠርተው በአንድነት ይኖሩ እንደነበርም የሚጠቁም መረጃዎች በልዩ ልዩ ሊቃውንት ለኅትመት በቅተዋል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ቀጥሎ ይህንን ቦታ ጎብኝተዋል፣ በቫቲካን ከተማ ቅጽር ግቢ ውስጥ ከቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በቅርበት የሚገኘው ቦታ ውስጥ በግእዝ ቋንቋ በድንጋይ ላይ የተጻፉ የጥንት ኢትዮጵያውያን ማስታወሻዎችንም ለማየት ተችሏል፡፡
ቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ጒብኝት፤
ቅዳሜ የካቲት 19 ቀን 2008 ዓ/ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያውያን ስም የተሠየመውን የቅዱስ እስጢፋኖስ ኮሌጅ ጎብኝተዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ “Santo Stefano degli Abissini” “Saint Estefanos Pontifical Ethiopian Col-lege Vatican City” “ቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ” በመባል ይታወቃል፡፡ ቅዱስነታቸው በኮሌጁ ሲደርሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን የኮሌጁ ተማሪዎች ከካርዲናል ሊዎናርዶ ሳንድሪ እና የኮሌጁ ዳይሬክተር ዶ/ር አባ ዳዊት ወርቁ፣ የኮሌጁ ፕሮፌሰሮችና የአስተዳደር ሠራተኞች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ደቀመዛሙርቱ ባዘጋጁት ልዩ መንፈሳዊ መርሐ ግብር መሠረትም ዶ/ር አባ ዳዊት የኮሌጁ ዳይሬክተር አስቀድመው በእንግሊዝኛ ከዚያም በጣሊያንኛና በአማርኛ ቋንቋ የእንኳን ደኅና መጡ ንግግር አድርገዋል፡፡ በመቀጠልም ስለ ኮሌጁ አመሠራረትና ታሪክ አሁን ስላለው አገልግሎት ሰፊ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል የነበሩት ኢትዮጵያውያን ከሁሉ አስቀድመው በየዓመቱ በልደትና በትንሣኤ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሳለም የሚጓዙ መሆኑን በርካታ የታሪክ መረጃዎች እንዳሉ በመጠቆም፣ ተጓዦቹም አብዛኛዎች መነኮሳት እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ኢትዮጵያውን የኢየሩሳሌም ጒዟቸውንም በግብጽ በኩል እንደሚያደርጉ በዚያም የግብጽ ገዳማትን እንደሚጎበኙ፣ ከኢየሩሳሌም በኋላ ደግሞ በሶርያና በኢየሩሳሌም አካባቢ ያሉ ቅዱሳት መካናትን እንደሚጐበኙ ከዚህም የተነሣ በርካታ ገዳማት በኢየሩሳሌም እንዳሉን አስረድተዋል፡፡ በኢየሩሳሌም ከጥንት ጀምሮ ስለነበረን ይዞታም በሰፊው አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ ጒብኝት ፍጻሜ ቅዱስነታቸው በኮሌጁ ያለውን ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ለሮም በስጦታ ያበረከቱት አንድ አነስተኛ ፒያኖ/ኦርጋን ያለበትን አነስተኛ ሙዚየምና ቤተ መጻሕፍት የጎበኙ ሲሆን፤ የኮሌጁ ፕሮፌሰሮች ስለ ኢትዮጵያ በተለይም ነገሥታቱ ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አስመልክተው ያሳተሟቸውን የጥናት ጽሑፎች ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አበርክተውላቸዋል፡፡ በመጨረሻም የኮሌጁ አስተዳደርና ሊቃውንት የማስታወሻ ስጦታ በኮሌጁ ስም ለቅዱስነታቸው ሰጥተዋቸው የጒብኝቱ መርሐ ግብር ተከናውኖአል፡፡
ምንጭ፡- ’ዜና መዋዕል ፤ ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ’ (ገጽ 334-338)
