የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ወደ አገሪቱ ለመግባት የB-1 የቢዝነስ እና የB-2 የቱሪስት ቪዛ ለሚጠይቁ አመልካቾች እስከ 15 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በማስያዣነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ አስታውቋል። ይህ በሁለት ሳምንት ውስጥ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል የተባለው የሙከራ ፕሮግራም ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ የሚቆዩ ጎብኚዎችን ለመከላከል ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ያወጣው ይህ ማስታወቂያ በርካታ ሰዎች ወደ አገሪቱ ለመግባት የሚያደርጉትን ሂደት አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል ተብሏል። እንደ የፌደራል መንግሥቱ የምዝገባ ማስታወቂያ ከሆነ ይህ አሠራር በቀጣዮቹ 12 ወራት ውስጥ በሙከራነት በተወሰኑ አገራት ላይ ተግባራዊ ይሆናል።
የሙከራ መርሃ ግብሩ አሜሪካ ውስጥ ከቪዛ ጊዜያቸው በላይ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ ዜጎች ባሏቸው አገራት እና የአገር ውስጥ ሰነዶች ላይ የላላ ቁጥጥር በሚያደርጉ አገራት ላይ ተግባራዊ መደረግ ይጀምራል ተብሏል። የእነዚህ አገራት ዜጎች ለቪዛ ሲያመለክቱ 5,000፣ 10,000 ወይም 15,000 ዶላር በማስያዣነት እንዲያቀርቡ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ይህ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አሠራር ይፋ የሆነው የትራምፕ አስተዳደር ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚጠየቁ የቪዛ አመልካቾች መስፈርቶችን እያጠናከረ በመጣበት ወቅት ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገር ማስወጣት እንዲሁም የድንበር ቁጥጥሩን ለማጠናከር በጀት ከፍ የማድረግ እና ወደ አገሪቱ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር የማዋል እርምጃዎችን ሲወስዱ ቆይተዋል። በሰኔ ወር ከ19 አገራት ወደ አሜሪካ ለመግባት የሚያመለክቱ ግለሰቦች ላይ ከብሔራዊ ደኅንነት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች የጉዞ እገዳ ጥለዋል።
በትራምፕ የስደተኞች ፖሊሲ ምክንያት የተወሰኑ ጎብኚዎች ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት እየሰረዙ መሆኑ ይሰማል። ከነሐሴ 20 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው ይህ አዲሱ የቪዛ ማስያዣ ገንዘብ ፕሮግራም ለአንድ ዓመት ያህል ይቆያል ተብሎ ተገምቷል።
