የንግዱ ማኅበረሰብ
‹‹ለዘርፉ ተገቢው ድጋፍ አለመደረጉን እናምናለን››
መንግሥት
በኢትዮጵያ ከፖሊሲ ማዕቀፍ ጀምሮ በየደረጃው ባለው የአሠራር ሒደት ዙሪያ አሉ የተባሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ዓላም ያደረገ የመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ የንግድ ባለድርሻ አካላት ሐምሌ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ምክክር አድርገዋል፡፡ የምክክሩ አጠቃላይ ሒደት ምን መልክ ነበረው? የተነሱ ጥያቄዎች እና የተሰጡ ምላሾችስ ምን ይመሥሉ ነበር? የሚለው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የምክክር መድረኩ የተጀመረው ኢንጅነር መላኩ እዘዘው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር እያከናወነ ያለውን ተግባር፣ ለንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ንግድና ኢንቨስትመንት አካባቢን በመፍጠር ረገድ አመቺ መድረኮችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር እንደሚያዘጋጅ ይህ መድረክም የዚሁ አንድ አካል መሆኑን ፣በአግሮ ፕሮሰሲንግ በቱሪዝም በኢኮሜርስ ወይም ዲጂታል ማርኬቲንግ ዘርፎች ላይ ላዘጋጀው የሁለት ቀናት መድረክ የጥናት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል፡፡
መድረኩ በዘርፉ መሠማራት ለሚፈልጉ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ያለውን የሥራ አማራጭ አስመልክቶ ግልጽ ማብራሪያ እንደሚያስቀምጥና በመንግሥት በኩል የተዘጋጁ ማበረታቻዎችን በተመለከተ ግንዛቤ የሚፈጠርበትና በጋራ መሥራት የሚቻልበትን መንገድ ለማመቻቸት እድል የሚፈጥር መድረክ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸው አቶ ተሻለ በልሁ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዲኤታ በንግግር እንዲከፍቱ ጋብዘዋል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዲኤታ ክቡር አቶ ተሻለ በልሁ መድረኩን በንግግር እንዲከፍቱ በመጋበዛቸው አመስግነው ለንግድና ኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱና በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን የልማት ግንኙነትና አጋርነት በይበልጥ ለማጎልበት እንዲቻል በማሰብ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውና በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት መካከል በተደረገ ስምምነት በሐምሌ 2002 ዓ.ም የጋራ መድረክ መመሥረቱን፣ በዚሁ መሠረት በርካታ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢውን ለማሻሻል የሚያግዙ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጎ በአብዛኛዎቹ ላይ የጋራ መፍትሄ መደረሱን፣ ለማስፈጸምም ጥረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አበርክቶ ባላቸው በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ጥናት በቀረበባቸው ዘርፎች ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄዎችን ለማመላከት ከግሉ ዘርፍ ጋር በመመካከር እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ፍትሃዊና የተሳለጠ የንግድ እንቅስቃሴ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር አበክሮ እንደሚሠራ በትግበራ ሂደት የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች በተሻለ አሠራር እንዲስተካከሉ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ በጋራ መምከርና ውጤታማ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች ሃላፊዎች የተገኙበት በርካታ መድረኮች ቀደም ብለው የተዘጋጁ ፣ቀድሞ የነበረውን የንግድ ህግ በማሻሻል እንዲሁም የንግድ ፖሊሲ ዝግጅት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡በማጠቃለያም መድረኩን ያዘጋጁትን አካላት አመስግነው መድረኩ መከፈቱን በይፋ አብሥረዋል፡፡
በመርሐግብሩ መሠረት በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ዘርፍ እንቅፋቶች ዙሪያ በወይዘሮ ሃይማኖት ጥበቡ አማካይነት ቅኝት ቀርቧል፡፡ ጥናት አቅራቢዋ በቅኝታቸው ግብርና ለኢትዮጵያ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 80 በመቶው በግብርና ላይ የተመሠረተ ኑሮ እንዳለው፣ በአገሪቱ ጥቅል አገራዊ ምርት 39 በመቶ ድርሻ ያለው የግብርናው ዘርፍ አገሪቱ ከወጪ ንግድ ገቢ ከምታገኘው የውጪ ምንዛሪም 90 በመቶ ድርሻ እንደሚይዝ፣ ለወጪ ንግድ ሀገሪቱ የምታቀርበው የግብርና ምርት በአብዛኛው ያልተቀነባበረ ወይም ያልተዘጋጀ እንደሆነ፣የአግሮ ኢንደስትሪው ዘርፍ ለኢትዮጵያ ጥቅል አገራዊ ምርት ያለው ድርሻ አምስት በመቶ ያህል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሃይማኖት ለጥናታቸው አራት የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎችና ሁለት የንግድ ማህበራትን እንደመረጡና የናሙና ጥናቶችን በመሰብሰብና መረጃዎችን መሠረት በማድረግ በዚህ ጥናት የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች
- ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣
- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዕገዛ በማድረግ፣
- የተመጣጠነ ምግብ እትረትን ለመቆጣጠር የሥነ ምግብ ይዘትን በማሻሻል
ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡
በግብርና ምርቶች ማቀነባባሪያ ዘርፍ ውስጥ በላይኛው እርከን በጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት እንቅፋቶች በአራቱ የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች
- በሥጋ ማቀነባበር – አነስተኛ ምርታማነት፣
- በምግብ ዘይት – ፓልም ኦይል ድፍድፍ ከውጪ ሀገራት ገዝቶ ለማስገባት የውጪ ምንዛሪ አለማግኘት
በላይኛው እርከን በጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንቅፋቶች በሥጋ ማቀነባበር፣ በምግብ ዘይት፣ በፍራፍሬ ጭማቂዎችና በተቆላ ቡና ኢንዱስትሪዎች የጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ዋነኛ ችግር መሆኑ ተመልክቷል፡፡
በመካከለኛው እርከን በማቀነባበርና በአስተሻሸግ ላይ ያሉ ዕንቅፋቶች እንዲሁም በታችኛው እርከን በማርኬቲንግ ያሉ እንቅፋቶች ተዳሰዋል፡፡በድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶች በተለይ በመሠረተ ልማትና በፋይናንስ አቅርቦት ያሉ እንቅፋቶችም ተመልክተዋል፡፡ጥናት አቅራቢዋ ድምዳሜያቸውን ምክረ ሐሳቦችና ቀጣይ አቅጣጫ አቅርበዋል፡፡
በመቀጠል ክቡር አቶ ታረቀኝ ቡልቡላ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዲኤታ፣ የተከበሩ ዶክተር ሶፊያ ካሳ የግብርና ሚኒስትር ዲኤታ እና ኢንጅነር መላኩ እዘዘው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የጉባኤውን ተሳታፊዎች በኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ አወያይተዋል፡፡
ክቡር አቶ ታረቀኝ ቡልቡላ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዲኤታ በምክር ቤቱና በፓን አፍሪካን በተዘጋጀው በዚህ የምክክር መድረክ ደስተኞች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከንግድ በተጨማሪ የአምራች ዘርፉን በተመለከተ ምክክሩ መዘጋጀቴ ጠቃሚ መሆኑን፣ለኢትዮጵያ ትልቁ የወደፊት ዕድል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ መሆኑን ግብርናው ላይ እሴት መጨመር ተገቢ ሃሳብ መሆኑን አስረድተው በጥናቱ የተለዩት ችግሮች ትክክለኛ መሆናቸውን በመንግሥት በኩል ከማበረታቻ አኳያ የተወሰኑ የግብርና መሣሪያዎች ከግብር ነጻ መሆናቸውንና ግብር መቀነሱን ሆኖም ዘላቂ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ማበረታቻ ለአምራች ኢንዱስትሪው እንዳልተደረገ በቀጣይ ተለይተው ድጋፍ እንደሚደረግላቸውና ለዚህም ዕድል እንዳለና አብሮ መስራት እንደሚስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ክብርት ሶፊያ ካሳ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ እንደ ሀገር ማምረት ያለብንን ያህል እንዳላማረትን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንዱ ተግባር አርሶአደሩንና የንግድ ኢንዱስትሪ ዘርፉን ማገናኘት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም ተሳታፊዎች በዘርፉ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች አቅርበዋል፡፡
ከኤክስፖርት አንጻር
- ከሀገር ውስጥ የሚገዛው ግብዓት በጎረቤት ሀገራት ካሉት አንጻር ውድ መሆኑ ለማሳያ በሀገር ውስጥ አንድ ኪሎ ሥጋ በ400 ብር በ3.7 የአሜሪካ ዶላር እየገዛን ሲሆን ኬንያ ያሉ ነጋዴዎች በ3.6 የአሜሪካ ዶላር እየገዙ በአንድ ገበያ መወዳደር አስቸጋሪ እየሆነ ከዱባይ ገበያ እየወጣን ነውና ትኩረት ቢሰጠው (ትርፍ የሚያስገኝ አለመሆኑ)
ከውጭ ምንዛሪ
- የውጪ ምንዛሪን ችግር መንግሥት በአስቸኳይ ሊፈታው እንደሚገባ፣
- ባንኮች የሚሠጡት ብድርና የወለድ መጠን ቢታይ
ከአገልግሎት አንጻር
- በግብርናው ዘርፍ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ያላቸው መሬት ለማግኘት ፈታኝ ቢሆንም በሚፈለገው መጠን መሬት እየቀረበ አይደለምና ትኩረት ቢሰጠው፣
- የውጪ ምንዛሪ በቀጥታ ለሚያስገቡ ነጋዴዎች ማበረታቻ ቢኖር፣
- የመንግሥት አገልግሎት በአንድ መስኮት ቢሆን፣
- የመሠረተ ልማት በተቻለ መጠን ቢሟላ
- አሁንም ከፍተኛ ብድር እያገኘ ያለው የንግድና አገልግሎት ሴክተር እንጂ አምራቹ ዘርፍ ስላልሆነ ባንኮች ትኩረት ቢሰጡት
ሌሎች ነጥቦች
- በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላይ የቅባት እህል እጥረት እንዳለ፣የመንግሥት አገልግሎት ፈጣን አለመሆኑ፣በተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ድጋፍ ያለማግኘት ችግር እንዳለ
- ከመንግሥት ተቋማት የሚወጡ መመሪያዎች አለመናበብ ቢስተካከል፣
- ባር ኮድ ስታንዳርድ ላይ ድምዳሜ ቢደረስ፣
- የተሻለ ገቢ ከሚያገኙ አርሶ አደሮች ገቢ መሰብሰብ ቢቻል፣
- ባንኮች የሚጠይቁት ከፍተኛ የብድር ወለድ የአምራች ኢንዱስትሪውን የሚያበረታታ አይደለምና ቢታይ፣
- ከማኑፋክቸሪንግ ጋር ያሉ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ቢፈተሹ፣
- የመንግሥት አገልግሎት ሠጪ ተቋማት በቅልጥፍናና በብቃት ዘርፉን የሚያገለግሉበት ሁኔታ ቢጠናከር ፣
- ለአግሮ ፕሮሰሲንግ መሬት ሲጠየቅ በወቅቱና በአግባቡ የማያስተናግዱ የመንግሥት አካላት ስላሉ ክትትል ቢደረግ፣
- በአግሮ ፕሮሰሲንግ ለሚሠማሩ ከጸጥታ አንጻር በቂ የጸጥታ ጥበቃ ቢደረግ፣
- የግልና የመንግሥት አጋርነት ተጠናክሮ ቢቀጥል፣
- የምርት ጥራት ከአርሦ አደሩ ቢጀምር፣
- ላኪዎችን ወደ ኪሳራ ከሚከታቸው አንዱ በህጋዊ መንገድ ኤክስፖርት አድርገው ሲመጣ የውጪ ምንዛሪው በጥቁር ገበያ በከፍተኛ ዋጋ እየተሸጠ መሆኑ
በሦስቱም ክቡራን ሚኒስትር ዲኤታዎች በኩል
- በጥናቱ የተለዩት ችግሮች ትክክለኛ መሆናቸውን፣
- ዘላቂና ተወዳዳሪ የሚያደርግ ማበረታቻ ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዳልተደረገ እንደሚታመንና በዚሁ ላይ በቀጣይ እንደሚሠራ፣
- አግሮ ፕሮሰሲንግ ለመደገፍ አምስት ክላስተሮች መዘጋጀታቸውን ግብርና ላይ ቀረጥ የሚጣልባቸው መሣሪያዎች የግንባታ መሣሪያዎች ከታክስ ነጻ እንደሆኑ ሆኖም መንግሥት ከግሉ ዘርፍ ጋር በበለጠ ተቀራርቦ አብሮ ለመሥራት ፍላጎት ቁርጠኝነትና ዝግጅት እንዳለ፣
- መሬት ለማቅረብ አቅም በፈቀደ መጠን ጥረት እንደሚደረግ ሆኖም መሬት ከወሰዱ በኋላ ወደ ሥራ አለመግባት ስላለ ሊታረም እንደሚገባ፣
- በቦታ አቅርቦት በኩል ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ እንዲሠጡ ከስምምነት መደረሱን፣
- በመንግሥት በቅርቡ ከግሉ ሴክተር ጋር የሚካሄዱ የውይይት መድረኮች እንዳሉ፣
- የቀጣይ ውይይቶች ዓላማ በዚህ መድረክ የተወያየንባቸው ችግሮች እንዴት እንደተፈቱ ለመገምገም መሆኑን
በንግድ ዘርፍ የተሠማሩም በቅንነትና በታማኝነት ሊሠሩ እንደሚገባ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት መመዘኛውን አሟልቶ መገኘት እንደሚገባም አስገንዝበው በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የተካሄደው ውይይት ተጠናቋል፡፡
