የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማክበር እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት በይፋ አስታውቀዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ እና የኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሻክቦት ቢን ናህያን አል ናህያን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ባደረጉት ምክክር፣ የሁለቱን ወገኖች ስትራቴጂካዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ለአሐዱ በላኩት ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጸዋል።
ውይይቱ በዋናነት ያተኮረው በሶማሊያ መረጋጋት፣ በሱዳን ወቅታዊ ቀውስ እና በአህጉሪቱ በሚታዩ የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ዙሪያ ሲሆን፣ ሁለቱም ወገኖች ለአፍሪካ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ እድገት በጋራ ለመቆም ቃል ገብተዋል።
በተለይም በሶማሊያ ጉዳይ ላይ ያተኮረው ንግግር የአገሪቱን ደህንነትና የግዛት አንድነት በጽኑ እንደሚደግፉ ያረጋገጠ ሲሆን፣ ይህ አቋም በቀጠናው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል።
ይህ የፖለቲካ ምክክር በ2019 የተፈረመውን የመግባቢያ ስምምነት ተከትሎ በ2025 በአቡዳቢ የተጀመረውን የውይይት መድረክ መሠረት ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህ ጎን ለጎንም በሱዳን ዕየታየ ያለው ቀውስ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና ለዜጎች ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲቀርብ ጥሪ አቅርበዋል።
