የአፍሪካ ሕብረት የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ታፍነው መወሰዳቸውንና በተቋማት ላይ እየደረሱ ያሉ ወታደራዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በሀገሪቱ ያሉት ሁኔታዎች በጥልቅ እያሳሰቡት መሆኑን ገለጸ። ጉዳዩን በቅርብ እየተከታተለው መሆኑንም ሕብረቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሕብረቱ ለዓለም አቀፍ ሕጎች በተለይም፤ ለሃገራት ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት መጠበቅና ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት መረጋጋጥ ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
ይህም የሀገራት የሉዓላዊነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር በግልጽ የተጠበቀ መሆኑን ያመላከተው ሕብረቱ፤ በሀገራት መካከል የሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች መፈታት ያለባቸው በንግግርና በሰላማዊ መንገድ መሆን እንዳለበት አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።
በአባል ሀገራት መካከል እንዲሕ ዓይነት አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በመልካም ጉርብትና መንፈስና በጋራ ትብብር መርሆች ላይ ተስርቶ፤ ሕገ መንግሥታዊና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ተከትሎ በንግግርና በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም አሳስቧል።
ቬንዙዌላ የገጠሟት ውስብስብ የውስጥ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ነሀገሪቱ ዜጎች መካከል ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ንግገሮችን በማካሄድ በራሳቸው በቬንዙውላውያን ነው የሚል ጽኑ እምነት ያለው መሆኑንም ሕብረቱ ገልጿል።
ሕብረቱ ለቬንዙዌላ ሕዝብ ያለውን አጋርነት እንዲሁም በሀገራትና በቀጠናዎች መካከል ሰላም እንዲሰፍንና የጋራ መከባበር እንዲኖር ያለውን ቁርጠኝነት ገልጾ፤ “ችግሩ ከዚህ የበለጠ እንዳይባባስና ቀጠናዊ ሰላምን እንዳያደፈርስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጉዳዩን ኃላፊነት በተሞለባትና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መንገድ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት ጥሪ አቀርባለሁ” ብሏል የአፍሪካ ሕብረት በመግለጫው።
