በአሜሪካ የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር በርሃኑ ገረሱ ክፍሌ፣ የዋስትና ጥያቄያቸው በፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።
ዶ/ር በርሃኑ “የዓመቱ የላቀ መምህር” (Teacher of the Year) ሽልማታቸውን የተቀበሉበትን የሙያ ኮንፈረንስ አጠናቀው በመመለስ ላይ ሳሉ ባለፈው ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም በዳላስ ፎርት ዎርዝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።
የሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ህጋዊ የሥራ ፈቃድ እንዳላቸው በመግለጽ በፍጥነት ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ ማድረጉን ቢገልጽም፣ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት (DHS) ግን ዶ/ር በርሃኑ የቪዛ ጊዜያቸው በሜይ 2024 ያበቃ በመሆኑ በሀገሪቱ ውስጥ በሕገ-ወጥ መንገድ ቆይተዋል ሲል ከሷቸዋል።
መምህሩ በኦክላሆማ በሚገኘው የዳይመንድባክ ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ሲሆን፣ የሕግ ጠበቃቸው ሳሮን በርሄ የቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉ ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል። የኢሚግሬሽን ሂደታቸው እስኪጠናቀቅ ድረስ ዶ/ር በርሃኑ በማቆያ ማዕከሉ እንደሚቆዩ ተገልጿል።
Source : CBS News
