የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት መደበኛ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ እንደሚጀምር ያስታውቃል፡፡ ጨረታዎቹ ለሚቀጥሉት በርካታ ወራት የሚካሄዱ ሲሆን፣ ዓላማውም የማዕከላዊ ባንኩን የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ግብን ለማሳካት ነው፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ከተጀመረበት ከሐምሌ ወር 2016 ወዲህ የወጪ ንግድ በመስፋፋቱ፣ የውጭ ሐዋላ በመጨመሩና የካፒታል ፍሰት በማደጉ ምክንያት የኢትዮጵያ የውጭክፍያ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ የመሻሻል አዝማሚያ አሳይቷል፡፡ የማዕከላዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በታሪኩ ከፍተኛው ሆኗል፡፡ በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ፣ በሀገሪቱ ውስጥ ብቸኛው የወርቅ ገዥ ለሆነው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ከፍተኛ መሆን የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከተገመተው በላይ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
ከዚህ ከተጠበቀው በላይ ከሆነው የውጭ ምንዛሪ ግኝት አንጻር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይወራት በመደበኛነት በየሁለት ሳምንቱ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታዎችን ለማካሄድ ወስኗል፡፡ ይህ አካሄድ በማዕካላዊ ባንክ እየተከማቸ ካለው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን መጠን ለግሉ ዘርፍ ለማቅረብና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማ ለማሳካት የሚረዳ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት የሚያወጣው የውጭ ምንዛሪ ጨረታ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማረጋጋትና ሪፎርሙ ከተጀመረ ወዲህ መሻሻል እያሳየ የመጣውን የውጭ ክፍያ ሚዛን በይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳ ታምኖበታል፡፡
በመሆኑም፣ ፍላጎቱ ያላቸው ባንኮች በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳና በተቀመጠው አኳኌን የጨረታ ሰነዶቻቸውን እንዲያስገቡ ባንኩ ጥሪ ያደርጋል፡፡
ለጨረታ የቀረበው የውጭ ምንዛሪ መጠን፡- 50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር
ጨረታው የሚካሄድበት ቀን፡- ማክሰኞ መጋቢት 231 2017
የጨረታ ሰነድ የሚላክበት ኢ-ሜይል አድራሻ :- fxauction @nbe.gov.et
የጨረታ ሰነድ የሚቀርብበት ጊዜ፡- ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ 6 ሰዓት
የጨረታው ውጤት የሚገለጽበት ሰዓት፡- 9 ሰዓት
ሂሳቡ የሚወራረድበት ቀን፡- ማክሰኞ 23፣ 2017
