የኢትዮጵያ ትያትር ፻ ዓመት

Date:

ክብረ- ምዕታመት ያትርለዛሬ እና ለነገ ጥበባዊ ልማት!!!!!

አቦነህ አሻግሬ ዘኢየሱስ

የኢትዮጵያ ትያትር ጳጉሜ 2013 ዓም አንድ መቶ ዓመቱን እንደሚደፍን ታሪካችን ያስረዳል፡፡ እና በህዳር ወር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምህርት ቤት መምህራን፣ ስለ መቶኛዉ  የአገራችን  ትያትር እድሜ አዘካከር ለመመካከር ጉባኤ ተቀመጡ፡፡ ይህ በታሪክ አጋጣሚ የሚገኝ አንድ እድል እንደመሆኑ፣ ክብረ በአሉ ለጥበቡ እና ለጠቢቡ እንዲሁም ለሀገር የጎላ ውጤት በሚያስገኝ ዓላማ ሊከበር እንደሚገባ ከስምምነት ተደረሰ፡፡ በዚህ መሰረት፣ በምዕት አመቱ ውስጥ የተከወኑ ስኬታማ የሙያው ጉዞዎች የሚነቀሱበት፣ የጥበቡና የጠቢባኑ ውጣ ዉረዶች የሚጤኑበት፤ የትያትር ጉዞዉ ከሙያ፣ ከሃገር እና ከህዝብ ጠቀሜታ አንጻር የሚመረመርበት፤ በቀጣዩ ሁለተኛ ምዕት በሰመረ የእድገት ጎዳና እንዲጉዋዝ አቅጣጫ የሚተለምበት በዓል ሆኖ እንዲከበር ተወሰነ፡፡

በማስከተልም፣ የትያትር ጥበባት ትምህርት ቤት ተልእኮዉን ለማሳካት ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸዉን፣ በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የመንግስትና የግል የጥበብ ድርጅቶችን፣ የክልል ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት ትምህርት ቤቶችን፣ ባህል ማእከላትን፣ትያትር ቤቶችንና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን፣ እንዲሁም የሙያ ማህበራትን በማስተባበርና በማሳተፍ፣ ከየካቲት እስከ ጳጉሜ መጨረሻ የሚካሄዱ የተለያዩ ጥበባዊና አካዳሚያዊ ተግባራትን በደማቅ ሁኔታ ለማከናወን ታቀደ፡፡

ክብረ- መዕታመት ያትርለዛሬ እና ለነገ ጥበባዊ ልማት! የሚል መሪ ቃል የትግበራ አቅጣጫዉን እንዲወስን ተመረጠ፡፡ ክብረ-በዓሉ ለሀገር እና ለህዝብ የሚጠቅም፣ ለትያትር ታሪክ ምርምርና ዘገባ የሚውል፤ ለታሪክ የሚበቃ፤ በታሪክ የሚወሳ፤ ለቀጣይ ትውልድም የሚተርፍ አሻራ የሚጥል እንዲሆን ታለመ፡፡

የኢትዮጵያ ትያትር ምእት ዓመት  የማክበር ዝግጅትና አተገባበር፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ተገምቶዋል፡፡ ትያትር በኢትዮጵያ የተጀመረበትን መቶኛ ዓመት  በመዘከር ሂደት ጥበቡ ያለፈበትን የእድገት ጉዞ ቃኝቶ ለወደፊቱ ይበልጥ የሚበለጽግበትን አግባብ ያመቻቻል፡፡ ክብረ-በአሉ ፣ ያለፈዉን መቶ ዓመት  የትያትር ታሪክና እድገት ከመተረክ ባለፈ፣ ፖሊሲ አዉጭዎች እና የሚመለከታቸዉ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቁዋሞች ለመጪዉ  የተሻለ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ግንዛቤንና መነቃቃትን ያገዝፋል፡፡ የኢትዮጵያ ትያትር የሚገኝበት ደረጃ በአገር ዉስጥ፣ በአፍሪካና በመላዉ አለም የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኝ በማድረግ የአገሪቱን መልካም ገጽታ ያበለጽጋል፡፡ የበአል አከባበሩ፣ የፌዴራል ባህል ሚኒስቴርና የየክልሉ የባህል ቢሮዎች፣ የትያትር ትምህርትን የሚሰጡ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ባህል ማእከላት፣ እንዲሁም ትያትር ቤቶችና የሙያ ማህበራት ያለፉበትን ሂደት ገምግመዉ ጠንካራ ጎናቸዉን ይበልጥ የሚያሳድጉበትን፣ እጥረታቸዉን አስተካክለዉ የሚያሙዋሉበትን መድረክ ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ያመቻቻል፡፡ በተከታታይ ኮንፈረንስ ላይ የሚቀርቡ ጥናትና ምርምሮች በፕሮሲዲንግ ታትመዉ፣ የትያትር አቅርቦቶችና ክንዋኔዎች በቪዲዎ ተቀርጸዉ፣ በመማር ማስተምርና ምርምር ረገድ የሚስተዋሉትን የግብአት እጥረቶች ለመቅረፍ ያግዛሉ፡፡

ባለፉት ሁለት አሰርት አመታት የኢትዮጵያን ትያትር በልዩ ስልት ለማጥፋ የተደረገዉን ስዉር ዘመቻ በማሳየት፣ ለጥበቡ ትንሳኤ መሰረት እንዲጣል ያነቃቃል፡፡   

ዝግጅቱ ከየካቲት እስከ ዻጉሜ 2013 ዓ.ም ሳይቆራረጥ እንደሚከናወን ይታሰባል፡፡ ከመጋቢት የመጀመሪያው ሳምንት የመክፈቻው ስነስርአት አንስቶ፣ በጥናት ወረቀት አቅርቦት፣ ሲምፖዚየም፣ የትያትር አቅርቦት፣ አግዚቪሽንና ወርክሾፖ እንዲሁም የእዉቅና ሽልማት ተፈጻሚነትን ያገኛል፡፡  

ዝግጅቱ በዋናነት መቸቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትያትር ጥበባት ትምህርት ቤት ቢያደርግም፣ በየትያትር ቤቶች፣ በክልል የትያትር ጥበባት  ትምህርት ቤቶች፣ በተለያዩ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከናወን ይገመታል፡፡

ክብረ በአሉ በሚከበርበት ወቅት፣ ትያትር በአገራችን በማንና እንዴት እንደተጀመረ፣ መቶ ዓመት  ወደኋላ ተጉዘን ታሪካዊነቱን ማስተዋል ተገቢ ይሆናል፡፡ በጥናት እንደተረጋገጠዉ፣ ትያትር የሚባልን ነገር በአገራችን የጀመረዉ ለአገር ዝመና ተቆርቆዋሪ የነበረዉ ተክለ ሀዋርያት ተክለማርያም ዋየህ ነዉ፡፡ እጅግ የሚያስገርመዉ ደግሞ፣ የትያትር ጅማሮዉ ከዓድዋ ጦርነትና ድል ጋር የሚጣቀስ መሆኑ ነዉ፡፡ ይህ ቀጥሎ በሚሰፍረዉ የተክለ ሀዋርያት አጭር ታሪክ ዉስጥ ይንጸባረቃል፡፡

ተክለሀዋርያት ተክለማርያም ዋየህ ጥር 12 ቀን 1876 ዓ.ም በሸዋ አንኮበር ስድበር በምትባል አካባቢ ተወለደ ፡፡ አምስት ዓመት እስከሚሞላው ከአያቱ ከወ/ሮ ይጠይቁሽ እገዶ ጋር ከኖረ በኋላ አጎቱ ዘንድ ሆኖ የቤተ ክህነት ትምህርት እንዲማር ወደ ሞቲሎሚ ተወሰደ ፡፡ ከዚያም በ1884 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ከአቡነ ማቲዮስ ዘንድ በማረፍ ትምህርት እንዲጀምር ተደረገ ፡፡ ወዲያዉ ታላቅ ወንድሙ ገብረ ፃዲቅ ተረክቦት ትምህርቱን አስቀጠለዉ ፡፡

ገብረ ፃዲቅ የራስ መኮንን ልዩ ፀሐፊ ሆኖ ወደሀረር ሲሄድ ተክለ ሐዋርያትን ይዞ ሄደ፡፡ ለጥቂት አመታት ሀረር እንደኖሩ ጥልያን አገራችንን በመዉረርዋ፣ በአጤ ምኒልክ  ትእዛዝ ራስ መኮንን ሰራዊታቸዉን አሰልፈዉ ወደ ትግራይ ዘመቱ፡፡ ፀሐፊያቸዉ ገብረ ፃዲቅ አብሮ ዘመተ፡፡ ገብረ ፃዲቅም   ብላቴናዉን ተክለሀዋርያትን ከፈረሱ አፈናጥጦ ነበር ከምስራቅ እሰከ ሰሜን የተጉዋዘዉ፡፡

ጥልያን መቀሌ ላይ የጸና ምሽግ አድርጎ ክፉኛ በመዋጋቱ ወገንን ባስቸገረበት ወቅት፣ ገብረ ፃዲቅ ከጠላት ምሽግ ዘልሎ ገብቶ በጎራዴዉ ሲከታከት በህዳር ወር 1888 ዓ.ም ተሰዋ፡፡ ራስ መኮንንም በገብረ ፃዲቅ ህልፈት ክፉኛ አዝነዉ ተክለሀዋርያትን ከድንኩዋናቸዉ አስገቡት፡፡ ከአድዋ ድል በሁዋላ ከፈረሳቸዉ አፈናጥጠዉት ወደ ሁረር አደረሱት፡፡ የማሳደግ ሀላፊነትን በመረከብ ከልጃቸዉ ተፈሪ መኮንንና ከስጋቸዉ ከእምሩ ሀይለ ስላሴ እኩል በቤተመንግስታቸዉ አሳደጉት፡፡ ቆይቶ ዳግማዋ አጤ  ምኒልክን አስፈቅደው ለትምህርት ወደሩሲያ ላኩት፡፡ ተክለሀዋርያትም በሩሲያ በሴንት ፒትስበርግ የጦር ትምህርት ተምሮ የኮለኔልነት ማዕረግ ካገኘ በኋላ በ1900 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ብዙም ሳይቆይ የእርሻ ትምህርት ሊማር ወደ ፈረንሳይና እንግሊዝ ሀገር ሄዶ 1912 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ ሂርና ላይ እርሻ ጀመረ፡፡  

ዳግማዊ አጤ ምኒልክ አርፈዉ፣ ልጅ እያሱ አልጋ እንደወረሱና፣ ሞግዚታቸዉ ራስ ቢትወደድ ተሰማ ናደው እንደሞቱ፤ እያሱ ተክለሀዋርያትን ከሂርና ወደ አዲስ አበባ አስጠሩት፡፡ ያኔ በነበረዉ የቤተመንግስት ስርአት ሳቢያ ወዲያው ሊገናኙ ግን አልተቻላቸዉም፡፡ ተክለሀዋርያት ዛሬ ነገ ወደ ቤተ መንግስት እጠራለሁ እያለ በሥራ ፈትነት አዲስ አበባ ውስጥ በቆየበት ጊዜያት ቅሬታ ተሰምቶታል፡፡ የአውሮፓ  ቆይታው የባህልና የአስተሳሰብ ልዩነትን ፈጥሮበት እንደ ባዳ እንዲታይ እንዳደረገዉም ቆጥሮ ነበር፡፡   

እንደምንም ብሎ ወጣቱን የአገር መሪ ቀርቦ በአማካሪነት ሊያገለግለዉ ዘዴ ሲፈልግ፣ ያለው አማራጭ በስነ ፅሁፍ ሰበብ መቀራረብ ሆኖ አገኘው፡፡ ስለዚህም በአውሮፓ  ያነበባቸውንና በሀገር ውስጥ የሚያውቃቸውን ተረቶች አሰባስቦ ስምንት ተረቶችን በሐምሌ 1904 ዓ.ም በግጥም ፅፎ ፋቡላ ተረትን አጠናቀቀ፡፡ የተረቶቹም  ርእስ  ፌንጣን ጉንዳን ዝንጀሮና መስታዎት ሉልና አውራ ዶሮ ዋርካና ሰንበሌጥ ርግብና ጉንዳን ቀናተኛ እንቁራሪት ሞኝ ዛፍ ሆድ ዕቃ ናቸው፡፡ የፃፈውንም ተረት የልጅ እያሱ ባለ ል ለነበሩት ለነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አነበበ ፡፡ ተሰማ እሸቴም ወዲያው ከልጅ እያሱ ጋር አገናኙት ፡፡ ተረቶቹንም ለልጅ እያሱ  አነበበላቸውና ከዚያ ወዲያው ባለ ል ሆነ፡፡

ልጅ አያሱን በሚፈልግበት መንገድ ሊመራ ግን አልተቻለውም፡፡ አለመስማማቱ ጎላና ከባለ ልነት ተወገደ፡፡ በዚሀም ልጅ እያሱን ከምኒልክ ዙፋን አውርዶ የባለውለታውን ልጅ ፣ ተፈሪ መኮንንን ከሥልጣን ለማውጣት በተደረገው ፖለቲካዊ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና ተጫዉቶዋል፡፡ ለዚህም ልኡል ተፈሪ መኮንን አልጋወራሽና ባለሙሉ ስልጣን እንደራሴ ሆነዉ፣ ንግስት ነገስታት ዘዉዲቱ ከዙፋን እንደወጡ ከፍተኛ ሹመት አግ ቶዋል፡፡

አንድ ቀን፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዴሬክተር የነበሩት ከንቲባ ህሩይ ወልደ ስላሴ፣ ተክለሀዋርያት ትያትር እንዲመለከት በደብዳቤ ጋበዙት፡፡ ቀድሞ ትያትር በኢትዮጵያ ስላልተጀመረ አጀማመሩን ለማየት በጉጉት ወደቴራስ ሆቴል ሄደ  

መኳንንቱና መሳፍንቱ ከአዳራሽ ግጥም ብሎ ያወጋል፡፡ ወዲያው ከንቲባ ሂሩይ መድረክ ላይ ወጥተው የዛሬው ትያትር የሚቀርበው በወጣት ኢትዮጵያን የትያትር ማህበር መሆኑንና ይህም አቅርቦት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መሆኑን ገልፀው ከመድረክ ይወርዳሉ፡፡ ከዚያም አዝማሪዎች ከመድረክ ተደርድረው መዲናና ዘለሰኛ አንቆረቆሩ፡፡ በመቀጠል ባለመስንቆ አዝማሪ ቅኔ አዘል በሆነ የዜማ ግጥም ተደራሲውን አሳቀ፡፡ በኋላም በፈጣን የመሳንቆና ከበሮ ምት በታጀበ ዜማ አንዲት ተወዛዋዥ በደመቀ እስክስታ ታዳሚውን አስደነቀች፡፡ ሕዝቡ በዚህ በአዲስ የተደራጀ አቅርቦት ተገር ፡፡ ቅር የተሰኘው ተክለሃዋሪያትን ብቻ ነበር፡፡ በተለይም ሙዚቃና ዳንኪራ ትያትር መባሉ በአገራችን አንድ የጐደለ ነገር እንዳለ አስገነዘበው፡፡

ተክለሃዋርያት አዘነነና በፔትስበርግ፣ በሎንደን፣ በፓሪስ ያየውን የትያትር አይነት በአገራችን በቶሎ ለመጀመር አቋራጭ መንገድ አሰበ፡፡ አዲስ የተውኔት ታሪክ ፈጥሮ ለማዋቀር ጊዜ ስለሚወስድበት፣ አልጋወራሹን አቤቶ እያሱን ለመቅረቢያና ለመምከሪያ ቀደም ሲል በ1904 ዓ.ም የደረሳትን ፋቡላ የተሰኘች የተረት ስብስብ ሊገለገልባት ወሰነ፡፡ በተረቱ ውስጥ የፈጠራቸውን የአውሬና እንሰሳት ታሪክ በድራማ መልክ ጽፎ የወጣት ኢትዮጵያ ትያትር ማህበር አባላትን አሰልጥ ፣ የአውሬዎች ኰሜዲያን  ጳጉሜ 1913 ዓ.ም አዘጋጀ፡፡ ልዑል አልጋወራሽ ተፈሪ መኰንን፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ባሉበት በቴራስ ሆቴል  ቴዎድሮስ አደባባይ በሚገኘው በዛሬው የሜጋ አዳራሽ  አቀረበ፡፡

ድራማው እየተተወነ ተደራሲው ድምፁን ከፍ አድርግ አስተያየት ይለዋወጥ፣ ይተችና ስሜቱን ይገልፅ ነበር፡፡ አዳራሹ የመድረክ ብርሃን ስላልነበረው በመስኰት የሚገባው ብርሃን ለድራማው እይታ በቂ አልነበረም፡፡ እንዲያም ሆ  መሳፍንቱና መኳንንቱ በአዲሱ የጥበብ ጅማሮ ተደነቁ፡፡

ተክለሃዋርያት በ3ሺህ ቅጂ ካስጠረዘው ተውኔት ውስጥ ሶስት መቶው በድራማው መክፈቻ ዕለት ተሸጠ፡፡ ይሁንና ተውኔቱ አስተዳደራዊ ስረዓቱን እንደሚጐነትል ተደርጐ በመወራቱ ንግስት ዘውዲቱን ክፉኛ ቅር አሰኘ፡፡ ዳግመኛ በመድረክ እንዳይታይ፣ የተሸጠውም ሆነ ያልተሸጠውን ተውኔት ለልጅ መኮንን እንዳልካቸው በአስቸኳይ እንዲያስረክብ በአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን በኩል ተነገረው፡፡ እንዲህ በፖለቲከኛነት ተጠርጥሮ፣ የመጀመርያዉ የአገራችን ትያትር ልደቱንም ስርአተ ቀብሩንም በአንድ ቀን አስተናገደ፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ ግን ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ እስተንፋስ ሰጥተዉት በብዙ ድጋፍ የትያትርን ጥበብ ከላቀ ደረጃ ላይ አደረሱት፡፡ ደርግም እንዲሁ ልዩ ትኩረት ሰጥቶት በአንጻራዊነት አበለጸገዉ፡፡ ብልሀተኛዉ ትህነግ ግን የሚቆረቆርለት እየመሰለ፣ በከንቲባዎቹ ረቂቅ ስልት በአዲስ አበባ መስተዳድር ስር ያሉትን ሶስት ነባር ትያትር ቤቶችን በቢፒአር መመርያና በማኦ ሴቱንግ ኦሪታዊ አስተምሮ አሽመደመደዉ፡፡ የራስ ትያትርን ህንጻ ከነአካቴዉ አፈረሰ — አዲስ እገነባለሁ ብሎ፡፡

በቅርቡም የአዲስ አበባ መስተዳድር ታሪካዊዉን የሀገር ፍቅር ትያትርንና የማዘጋጃ ባህልና ትያትርን በማደስ ሰበብ ዘግቶዋቸዉ የጥበቡን ሞት አፋጠነ፡፡ ብሄራዊ ትያትር ብቻ ከጽኑ ህሙማን ክፍል ዉስጥ ሆና ለመተንፈስ ያጣጥራል፡፡

እንግዲህ የኢትዮጵያን ትያትር መቶኛ ዓመት የምናከብረዉ በሀዘን ጭምርም ነዉ፡፡ክብረ- ምዕታመት ትያትር፣ ለዛሬ እና ለነገ ጥበባዊ ልማት ብለን የፈከርነዉ ከዚህ ሀዘን ለመዉጣትም ጭምር ነዉ፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት የተሰማዉና የተረጋገጠዉ የምስራች ለትያትር  ትንሳኤ ብስራት ሆኖዋል፡፡ ትያትር በሰለጠኑት አገራት በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደ ትምህርት አይነት እንዲካተትና እንደማስተማርያ ዘዴ ከአገልግሎት እንዲዉል በጠቢባን ይቀርብ ለነበረዉን አቤቱታ በወደቀዉ መንግስት መሪ ይሰነዘር የነበረዉ እንቢታ በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተሰብሮዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የማስተማርያ መጻህፍት ዝግጅት እየተጣደፈ ይገኛል፡፡ ይህ ለአንድ አገር መማር-ማስተማር ሂደትና የትያትር እድገት ስርነቀል እርምጃ ሆኖ፣ ለትያትር ትንሳኤ አይቀሬነት ተስፋ ይጭራል፡፡ ታሪካ የሚመዘግበዉ ተአምራዊ እርምጃ !!

ትንሳኤ እዉን የሚሆነዉ ታድያ እንደነ ሶርያ፣ ሊቢያ፣ የመን ያሉትን ነባር ባለታሪክ ህዝቦች ባጠፉዋቸዉ ስልት ኢትጵያን ለማጥፋት የሀሰት ሰበብ የሚደረድሩትን ሀያላን ለመመከት አንድነታችን አጎልብተን፣ ሰንቀን፣ ታትቀን፣ ሰልጥነን፣ተደራጅተን ስንጠነክር ነዉና ከወዲሁ እንዘጋጅ፡፡ ዓድዋ እናስታዉሳቸዉ፡፡ አለበለዚያ የፈጠራ ትራጀዲ ሳይሆን በየቄያችን የእዉን ትራጀዲ ተዋንያን ሆነን እንቀራለን፡፡   የዓድዋ ድል 125ኛ ዓመት እና የኢትዮጵያ ትያትር 100ኛ ዓመት እንደ ሰኔና ሰኞ መግጠሙም ይደንቃል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...