የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች አየር ማረፊያዎች የሚያደርጋቸው በረራዎች መሰረዛቸው ተነገረ።
ቢቢሲ ትግርኛ ሐሙስ ጥር 21/2018 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ በረራዎች መቋረጣቸውን ከተጓዦች እና ከክልሉ አንድ ኃላፊ ማረጋገጥ ችሏል።
ለዛሬ ተይዘው በነበሩ በረራዎች ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ትኬት ቆርጠው የነበሩ መንገደኞች የሐሙስ ጥር 21/2018 ዓ.ም. መሰረዛቸውን የሚያስታውቅ አጭር የጽሁፍ መልዕክት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
በመልዕክቱ ላይ “ከዕቅድ ውጪ በመሆነ ምክንያት” በረራው መሰረዙን እና መንገደኞች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወይም የጉዞ ወኪላቸውን እንዲያገኙ መክሯል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራዎቹን መቋረጥን በተለመከተ እስካሁን የሰጠው ይፋዊ ምክንያትም ሆነ መግለጫ የለም።
ስለ በረራዎች መሰረዝ የተጠየቁት የክልሉ ትራንስፖርት ኃላፊ አቶ ታደለ መንግሥቱ በረራዎች መቋረጣቸውን አረጋግጠው፤ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከአየር መንገዱ ይፋዊ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አስካሁን ምላሽ አላገኘም፤ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአየር መንገዱ ኃላፊ ግን ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች መቋረጣቸውን አረጋግጠዋል።
እኚሁ የአየር መንገዱ ባልደረባ እንደገለጹት “በረራዎች ለዛሬ [ሐሙስ] ብቻ ነው የተሰረዙት፤ ነገር ግን የቀጣይ ቀናት በረራዎች በሚኖረው ሁኔታ የሚወሰን ይሆናል” በማለት ለውሳኔው ምክንያቱ ምን እንደሆነ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
