
የ40 ያህል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን የሚመራው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከጃፓናዊው የኤሌክትሪክ ሞተር ሳይክል አምራች ኩባንያው ከሆነዉ ዶዳይ ግሩፕ ኢንክ ጋር የነበረውን የመግባቢያ ሰነድ ማቋረጡን አስታውቋል።
ስምምነቱ ጥቅምት 11 ቀን 2017 የተፈረመ ሲሆን በአዲስ አበባ በ12 ወራት ውስጥ 100 የባትሪ መለዋወጫ ጣቢያዎችን ለመክፈት እና በሸገር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ 300 ጣቢያዎችን ለማስፋፋት ያለመ ነበር።
ይሁን እንጂ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኢትዮጵያ ዘላቂ የትራንስፖርት ዘርፍ ውስጥ ሰፋ ያለ የኢንቨስትመንት አካሄድን ለመከተል ስምምነቱን ማቋረጡን አስታውቋል ።
ይህ ውሳኔ አዳዲስ የቢዝነስ ሃሳቦቸን ለመደገፍ እንዲረዳ የታቀደውን ልዩ የቬንቸር ካፒታል (VC) ፈንድ ለማቋቋም የተወሰደው ስትራቴጂካል ለውጥ ነዉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ባወጣው መግለጫ “አጠቃላይ ግምገማ ካደረግን በኋላ ተመሳሳይ ኢንቨስትመንቶች በተዋቀሩ የቬንቸር ካፒታል ፈንዶች በተሻለ ሁኔታ ሊተዳደሩ እንደሚችሉ ወስነናል።” ብሏል።
የዶዳይ መስራች እና ዋና ስራ አስፈፃሚ ዩማ ሳሳኪ ለካፒታል እንደተናገሩት “ሁለቱንም ኩባንያዎች በሚጠቅም መልኩ በጋራ ስምምነቱን አቋርጠናል፣ ነገር ግን በየመግለጫዎቻችን ከተገለጸው በላይ ዝርዝር መረጃዎችን ላለመስጠት ተስማምተናል” ብለዋል።
በዓለም ገበያ ላይ እየተደረጉ ያሉትን ለውጦች ከግምት ውስጥ በማስገባት ዶዳይ ቴክኖሎጂያችንን እና ሀብታችንን የበለጠ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድንጠቀም የሚያስችሉን አማራጭ ስትራቴጂካዊ እድሎችን ለመከታተል መወሰኑን ጠቁሟል።