አይናለም እሸቴ
ግዮን መጽሔት :-በመጀመሪያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ስንጀምር ምንጊዜም የክብር አቶ ይድነቃቸውን ታሪክ አብሮ ማጣመር ያስፈልጋል፡፡
1. የኢትዮጵያ እግር ኳስ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን እግር ኳስን ስንመለከት በቅድሚያ መሠረት የሆነውን የትምህርት ቤቶች ውድድር ማየት እጅግ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ በዚያን ዘመን ትምህርት ቤቶች የእግር ኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ ነበሩ ብንል ስህተት አይሆንም፤ ምክንያቱም ትምህርት ቤቶች ዓመቱን በሙሉ በትምህርት ሚኒስቴር የበላይ ተቆጣጣሪነት ውድድር ያለማቋረጥ ሲያካሂዱ ስለነበር ነው፡፡
አንዱ ግዴታ ትምህርት ቤቶች ለውድድር ብቁ ሆነዉ የሚመዘገቡት ‹‹A፣ B C›› ቡድኖች በሥራቸው ሲታቀፍ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች እንደየምዝገባቸው ዓመቱን በሙሉ ይወዳደራሉ፡፡ ይህም በመሆኑ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች ከA ወደ B እንዲሁም ወደ C በአዲስ አበባ በጊዜው የማደግ ዕድል ስለሚገጥማቸው በግዜው በሸዋ ጠቅላይ ግዛት ፉትቦል ፌደሬሽን ተመዝግበው የሚጫወቱ ትልልቅ ክለቦች በቀላሉ ተጫዋቾች እየመረጡ ቡድናቸውን ያጠናከሩ ነበር።
ከዚያም እንደየ ችሎታቸው እየታየ ለወጣትና (ተስፋ ቡድን) እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድን ይመረጡ ነበር። በጊዜው የነበሩት ተጫዋቾች በሰዉነት አቋምም ሆነ በኳስ ችሎታቸው እጅግ ተመጣጣኝ ስለነበሩ ዋናውን ብሔራዊ ቡድን ለመለየት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እራሳቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ – አዳዲስ ተጫዋቾችን ዘወትር የማመለምሉት ትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ነው፡፡
ለምሳሌ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድንን ከተቀላቀሉት ውስጥ እነ ዶክተር ተቀዳ ዓለሙ(የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩ)፣ ያረጋል፣ ፍስሐ ወ/አማኑኤል፣ ሰለሞን ተርፋ፣ ሸዋንግዛው አጎናፍር፣ ጌታቸው ዱላ፣ ጥበበ መንክር የመሳሰሉት ተጫዋቾች የተገኙት ከየት/ቤቶች ነው፤ ስዩም አባተን ጨምሮ በጊዮርጊስ በቋሚነት ውጤታማ ተጫዋቾች ከዚያም ለብሔራዊ ቡድን የተጫወቱት ተጫዋቾች የመጡት ፍል ውሃ አካባቢ ከበደ ሜዳ ከተባለው ቦታ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች የተገኙት ከትምህርት ቤት ነው፡፡
ከት/ቤት ተገኝተው ለብሔራዊ ቡድን ረዘም ላለ ጊዜም ተጫውተዋል፡፡ ጊዮርጊስ ብቻ ሳይሆን ኤሌክትሪክ፣ አየር መንገድ፣ አንድነት፣ በራሪ ኮከብ የተባሉ ጠንካራ ቡድኖችም መነሻቸውን ስንፈትሽ የትምህርት ቤት ውድድር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ሌላኛው የኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ
ትምህርት ቤቶች ውድድር ሌላ የኳስ ተጫዋቾች መፍለቂያ የነበረው የወታደራዊ ክፍል የዓመታዊ ውድድር ነበር፡፡
ለምሳሌ፡-
✓ መሃንዲስ
✓ ሙዚቀኛ
✓ ሲግናል
✓ ወዘተ››
በሚል የእግር ኳስ ቡድኖች አቋቁመው ዓመቱን በሙሉ ውድድር ያደርጉ ነበር፡፡ በዚህ ውድድር የተሻለ ኳስ ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች በመምረጥ በፌደሬሽን ተመዝግበዉ በሚጫወቱ ቡድኖች ይጠሩ ነበረ፡፡ ለምሳሌ ቀፀላ ከበደ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የሄደው ከወታደራዊ ቡድኖች ነበር፡፡ እንደየ ችሎታቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ይመረጡ ነበር።
የክቡር ዘበኛ ፖሊስ፣ ኦሜድላም የየራሳቸው ጠንካራ ቡድን ነበራቸው፤ ለምሳሌ የሦስተኛ አፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ቡድን ከነበሩት ውስጥ አምስት ቁጥር ቦታ ይጫወት የነበረው አዋድ መሐመድ ከዚሁ ቡድን የተገኘ ነበር፡፡ እንግዲህ በጊዜው በነበረው ሥርዓት ከየዉድድሩ በችሎታቸው ተመዝነው በሚመረጡ ተጫዋቾች ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለመፍጠር እንደተቻለ ታሪክ ይመሰክራል፡፡
2. ከለውጡ በኋላ በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ይመስላል?
የኃይለሥላሴ ሥርዓት ተቀይሮ ደርግ በመንግሥትነት ከተሠየመ በኋላ ብዙ ለውጦች ሲደረግ ለውጡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንንም ነክቶታል፡፡ በመጀመሪያ የተወሰደው እርምጃ ሥርዓቱ ሲፈርስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥም ተመዝግበው የሚገኙትን ክለቦች ፌዴሬሽኑ በማፍረስ በአዲስ ሥርዓት እንዲቋቋሙ አድርጎ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ቀደም ብሎ በነበረው የፌዴሬሽን ሥርዓት ወታደራዊ ቡድኖች ከሲቪል ጋር እንዳይጫወቱ ተደርጎ ስለነበረ በአዲሱ ለውጥ እንደገና እንዲመለሱ ተወሰነ፡፡
በተጨማሪ በአዲስ አበባ አስተዳደር 25 ከፍተኞች ሥር የሚገኙ 285 ቀበሌዎች የራሳቸዉን የእግር ኳስ ቡድን እንዲያቋቁሙና በየከፍተኛቸው ሥር ውድድር እንዲያደርጉ እንዲሁም እነዚህ 25 ከፍተኞችን በዞን በመክፈል አምስት ዞን ተከፋፍለው ውድድር እንዲያደርጉ እቅድ ወጥቶ በእውነቱ ከፍተኛ ፉክክር የታየበት ስለነበር ተጫዋቾንም ለማውጣት ብዙም አላስቸገረም ነበር፡፡ ታዲያ በአዲሱ መዋቅር አዳዲስ ክለቦች በየመሥሪያ ቤቱ በመቋቋማቸው ከነበሩት ወደ ሃምሣ የሚጠጉ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን በመመልመል ሥራም በመስጠት በዋናው የፌዴሬሽኑ ፕሪሚየር ሊግ የሚጫወቱ ቡድኖች ተከስተው ነበር፡፡
ለምሳሌ፡-
– ቡና- መድን- ጥቁር አንበሳ- አብዮት ፍሬ- ትግል ፍሬ- መቻል – ቅዱስ ጊዮርጊስ- መብራት ኃይል – አየር ኃይልና ሌሎችም
ከዚያ በኋላ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለመምረጥ እጅግ ቀላል ቢያደርገውም በየመሀሉ በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ፍጹም ምርጥ የነበሩ ተጫዋቾች በየጊዜው በመመልመል ለብሔራዊ ቡድኑ በማሰለፍ ለዉድድር ከአገር ሲወጡ በዚያዉ እየጠፉ የፖለቲካ ጥገኝነት እየጠየቁ ስለሚቀሩ አሰልጣኞችም ሀገሪቱም በዚህ በኩል ችግር ገጥሟት ቆይቷል፡፡
በጊዜው በተገኙ ተጫዋቾች የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ በማሸነፍ የዋንጫ አሸናፊ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ ይህም ከሦስተኛ አፍሪካ ዋንጫ ወዲህ በብቸኛነት የተገኘ ድል ነው፡፡ በደርግ ዘመን ሌላው መነሳት ያለበትና አርአያነት ያለው ዕርምጃ እያንዳንዱ ቀበሌ የራሱ የእግር ኳስ ሜዳ እንዲኖረው ያስገድድ ነበር ፤ ከየቀበሌው የሚወጡ ተጫዋቾችን በቀላሉ እያወዳደሩ መምረጥም አስችሎ ነበር፡፡
ስለ መንግሥት ወይም ሥርዓት ለውጥ ሲነሳ በተለይ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የመንግሥት ለውጥ በመፈንቅለ መንግሥት ወይም በሌላ አካሔድ ሲደረግ አዲስ የሚቋቋመው መንግሥት የመጀመሪያ እርምጃው ሥር ነቀል ለውጥ በሚል ፈሊጥ የነበረውን የመንግሥት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በአዲስ መልክ እንዲቋቋም ማድረግ ነው፡፡
ይህ ደግሞ እግር ኳሱንም በጣም ጎድቶታል፡፡ በጣም የሚገርመው ማንኛውም ለውጥ አምጥቻለው የሚል መንግሥት ከተቀየረው መንግሥት ምንም ዓይነት የአስተዳደር ሕጎችንና ደንቦችን አይዎስድም፤ ሁሉንም ከዜሮ ስለሚጀምር በሂደቱ ላይ ይህ ነው የማይባል ችግሮችን ሲፈጥር ቆይቷል፡፡
እንደ እኔ አመለካከት ማንኛውም መንግሥት በየትኛውም አገር ቢሆን 0/100 የሚያገኝ የለም፡፡ አንዳንዱ ጥፋቱ ያመዝንና በጎ ልማቱ ያነሰ ሲሆን አንዳንዱ ደሞ ልማቱ ይበልጥና ጥፋቱ ያነሰ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ እኩል በኩል ይሆናል፡፡ ይሻል የነበረው ግን ከነበረው ላይ የጥፋቱን መንገድ ትቶ በጎውን በመውሰድ በማሻሻልና በማዳበር እጅግ ላገር ጠቃሚ የሚሆኑ ሥራዎችን መፍጠር ያስችላል የሚል አስተሳ
ሰብ አለኝ፡፡
3. ከደርግ መውደቅ በኋላ በኢሕአዲግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ እግር ኳስ
( ቀጣዩን ክፍል በቅርብ ቀን ይጠብቁን)
