በኢትዮጵያ የሚከበረው ዒድ አል-ፈጥር እንደ መካና መዲና በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በጋራ የሚታደምበት ታላቅ በዓል መሆኑን የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አደም ካሚል ገለጹ።
ፕሮፌሰር አደም ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት፤ የረመዳን ጾም ሕዝበ ሙስሊሙ ለ30 ቀናት በመጾም ከፈጣሪው ምሕረት የሚጠይቅበት ታላቅ ወቅት ነው።
ጾሙን ያጠናቀቀው ምእመን የዒድ አል-ፈጥርን በዓል ከትንሽ እስከ ትልቅ፣ ሴት ወንድ ሳይል በአደባባይ በአንድነት የሚያከብረው ልዩ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ከበዓሉ አንድ ቀን አስቀድሞም አቅም ለሌላቸው ወገኖች ዘካ በመስጠት የተግባራዊ መረዳዳት ሥርዓት የሚከናወንበት መሆኑንም አውስተዋል።
ዓለም አሁን እያስተናገደች ያለውን የሰላም እጦትና የኢኮኖሚ ቀውስ ተከትሎ፣ ወቅቱ ከምንጊዜውም በላይ ጸሎት የሚደረግበት መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ፍጹም ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላቸውን ከፍተኛ ምኞት አክለዋል።
የዒድ አል-ፈጥር በዓል ብሔር፣ ቋንቋና ቀለም ሳይለይ ሕዝበ ሙስሊሙ በአንድነት ፈጣሪን የሚያመሰግንበት በመሆኑ፤ ማኅበረሰቡ በዓሉን እርስ በርስ በመረዳዳት፣ በመጠያየቅና በመተሳሰብ እንዲያከብር ፕሮፌሰር አደም ጥሪ አቅርበዋል።
ከጋዜጣ ፕላስ
