የኢትዮጵያ ወጣቶቾ:- ወጣት፣ ሰላም እና ደህንነት

Date:

በታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) የተዘጋጀ ፅሁፍ

ግዮን መጽሔት :- ወጣቱን ሰላም ፈላጊ አድርጎ ከማሰብ ይልቅ ችግር ፈጣሪ አድርጎ የመቁጠር ዕሳቤ መኖሩ በዕድሜ ከፍ ያሉት የሕብረተሰብ ክፍሎች (elders) የሰላም ግንባታ ሂደቱን  እንዲንዲመሩ ምክንያት ኾኗል።

ሆኖም የሰላሙ ባለቤትና ዋና ተዋናይ የኾነው ወጣቱ ትርጉም ባለው መንገድ ተሳታፊ እስካልኾነ ድረስ በአዛውንቶች ጥረት ብቻ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሰላም መፍጠር አይቻልም። ለዚህ ደግሞ በተለምዶ ሸኔ ተብሎ ከሚጠራው የኦሮሚያ ነፃ አውጪ ጦር (OLA) ጋር በአባገዳዎችና የሀገር ሽማግሌዎች የተደረጉት በርካታ ያልተሳኩ ድርድሮች በምሳሌነት ሊነሱ ይችላሉ።

በትግራይ ባለው ሁኔታም ያለ ወጣቶች ንቁ ተሳትፎ ክልሉን ማረጋጋት በጣም ከባድ ነው። በኢትዮጵያ ለወጣቶች ያለውን አሉታዊ አመለካከት በመለወጥ እና በሁሉም የሰላም ግንባታ እና የዜጎች ደህንነት ማረጋገጫ ሂደቶች በንቃት የማሳተፊያው ጊዜ አሁን መኾን ያለበትም ለዚህ ነው።

ወጣትን ለሰላምና ደህንነት የማሳተፍ ዕሳቤ ለአካዳሚው ዓለም፣ ለተባበሩት መንግሥታት እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አዲስ አይደለም። የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በታህሳስ 2015 ውሳኔ ቁጥር 2250 ግጭትን በመከላከል እና ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ የወጣቱ አቅም ትልቅ እንደኾነ በማያሻማ ሁኔታ ገልጹዋል።

ይኽ የተመድ ውሳኔ እንደተለመደው ወጣት ወንዶችን “በጠመንጃ ነካሽነት” ሴቶችን ደግሞ “በሰለባነት” ጠቅሰው የተቹትን ባያጣም ወጣቶች ግጭቶችን በመፍታት እና በመከላከል ረገድ ያላቸውን አቅም ግን በሚገባ አስተዋውቋል። የውሳኔ ሃሳቡ አባል አገራት እና ሲቪክ አደረጃጀቶች ወጣቶች በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና እውቅና ሰጥተው እንዲደግፉም አሳስቧል።

መደረግ ያለበት

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 2250፣ የወጣቶችን የሰላምና ደህንነት ተሳትፎ ለማሳደግ ምን መደረግ እንዳለበት መመሪያ ሆኖ ሊያገለግል የሚችል ሃሳብ አስቀምጧል። በዚህ መሠረትም የፌዴራል፣ የክልል መንግሥታት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚከተሉትን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ፡-

ግጭቶችን እና ጽንፈኝነቶችን ለመከላከል እና የሰላም ግንባታን ለማሳለጥ ወጣቶች በአካባቢያዊ አስተዳደሮች፣ በክልል እና በፌዴራል የሥልጣን እርከኖች የውሳኔ ሰጪነት ተሳትፏቸውን ማሳደግ፣

ግጭት ባለባቸው እና ግጭት በተፈጸመባቸው ቦታዎች የወጣቶችን እና የንጹሐንን ሕይወት ጥበቃ ማረጋገጥ ፤ በተጨማሪም በዘውግ፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት፣ በቆዳ ቀለም፣ በጾታ፣ በጤና ወይም በአካል ጉዳት ላይ የተመሠረቱ ማናቸውንም የመድልዎ ዓይነቶች
ማስወገድ ፤

ወጣቶች በራሳቸው ሁከትና ነውጥን ለመከላከል እንዲሁም የሰላም ግንባታ እንቅስቃሴዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር መደገፍ ፤

ጽንፈኝነትን በመከላከል እና በማኅበራዊ ትስስሮች ውስጥ በቅንጅት በማሳተፍ ከሚመለከታቸው ሌሎች ተዋናዮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር ፣ እንዲሁም

የሥራ ዕድሎችንና ትምህርትን በመፍጠር፣ የአቅም ግንባታን ሥልጠናን በመሥጠት የወጣቶችን ሕልምና ርዕይ ለመደገፍ የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ከአመጻ ተግባራት እንዲርቁ ማድረግ ናቸው።

ሰላምን እና ደህንነትን በሚመለከት በወጣቶች ላይ የአመለካከት እና የአሠራር ለውጥ ማምጣት፣ የኢትዮጵያን የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ዘላቂነት በማድረግ ረገድ ሰፊ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ለዚህ ደግሞ ወጣቱ በሁሉም የሰላም ግንባታ ሂደቶች እና የዜጎችን ደህንነት በሚያረጋግጡ እንቅስቃሴዎች በንቃት መሳተፍ አለበት ፤ ከግጭቶች እና ከጽንፈኝነት ተግባራት መጠበቅ አለበት። የኢትዮጵያን ወጣቶች በሰላምና ደህንነት ውስጥ ያላቸውን ሚና በማጠናከር ረገድ ደግሞ ሁሉም የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል።

ለዚህ እንዲረዳም ወጣቶችን ከአመፅ ተግባራት ለማራቅ ሥልጠናዎች ከመሥጠት ጀምሮ የሲቪክ ተሳትፎ መርሃ ግብሮችን መተግበር አስፈላጊ ነው።

የዚህ ፅሁፍ ስፖንሰሮች:- This project implemented by Youth and Cultural Development Foundation (YCDF) is supported by The Fund for Local Cooperation (FLC) Embassy of Finland

ይህ በ ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን የሚተገበረው ፕሮጀክት በፊንላንድ ኤምባሲ የአካባቢ ትብብር ፈንድ (ኤፍኤልሲ)ነው።


ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በ ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን የሰላምና የግጭት ጥናቶች ባለሙያ ናቸው። ሀሳብና አስተያየቶን በ ycdfoundationethiopia@gmail.com ወይም tkersmo@yahoo.com ሊያደርሷቸው ይችላሉ፡፡

ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን ሀገር በቀል የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን ከተመዘገበ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በ አቅም ማጎልበት፤ ትምህርት፤ ጤና፤ አካባቢ እንክብካቤ፤ ማህበራዊ ሃላፊነት መወጣት፤ ድህነት ቅነሳና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፤ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት፤ ዘርፎች ላይ በማተኮር  አሳታፊ የሆኑና የተቀናጁ ፕሮጄክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር  230 መጋቢት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን ምስክርነት መጠቀም ተከለከለ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ...

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...