የዓለማችን የእግር ኳስ ንጉሥ የኾነው ፔሌ በሰማንያ ሁለት ዓመቱ በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በብራዚል ትንሿ መንደር ቴሪስ ኮራኮስ (ሦስቱ ልቦች) ፔሌ ጥቅምት 04 ቀን 1940 እኤአ የተወለደው ፔሌ፣ በሞቀው ከተማ ሳኦፖሎ ባሁሩ በተባለ ስፍራ አድጓል። ምድራችን ካፈራቻቸው ድንቅ ጥበበኛ እግር ኳስ ተጨዋቾች አንዱ ነው ይሉታል ኤዲሰን አራንተስ ዶናስሜንቶ (ፔሌን)። ብራዚላዊ ኮከብ ፔሌ ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምንም እንኳን በኦሎምፒክ ባይሳተፍም በ1999 የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ስፖርተኛ ብሎ ሰይሞታል።
ፔሌን ፊፋም የሀያኛው ክፍለ ዘመን ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋች ሲል የአክብሮት ሽልማት አበርክቶለታል። በ1956 ጥቅምት ወር ፔሌ ለሳንቶስ ክለብ ገና በ15 ዓመቱ የዋናው ቡድን ተጨዋች ለመሆን ፈረመ። በ1958 ፔሌ 56 የሊግ ጎል አስቆጥሮ ክለቡ ዋንጫ አገኘ በታሪክ ይህን ያደረገ ማንም ተጨዋች የለም በዚሁ ዓመት በ17 ዓመቱ ብራዚል የስዊድኑ የዓለም ዋንጫን እንድታሸንፍ አድርጓል። የብራዚል ሳንቶስ ክለብ በፔሌ ዘመን 10 የሊግ ዋንጫ እና ሁለት የኮፖ ሊቤርታዶስ ዋንጫ ሲያገኝ ሳንቶስ ክለብ እንደሚያምነው ፔሌ ከአንድ ሺ በላይ ጎል ማስቆጠር እና ጨዋታ እስከ 1974 አድርጓል ይላል ክለቡ።
ፔሌ ለብራዚል ሶስት የአለም ዋንጫ ያስገኘ ሲሆን በሁሉም ውድድሮች በተጫወተበት ጊዜ በ1364 ጨዋታ 1282 ጎል እንዳስቆጠረ ቢነገርም ፊፋ በይፋዊ መንገድ የመዘገባቸው 767 ጎሎችን በ831 ጨዋታ ብቻ ነው። ለአንድ ወር በሆስፒታል በህክምና እርዳታ ጤንነቱ ለመመለስ ቢሞከርም በካንሰር ሲሰቃይ የቆየው ፔሌ በጨረሻውም ሕይወቱ አልፏል።
መላው ዓለም በእግር ኳስ ንጉሥነቱ የሚስማማበት ኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶስ በአጭሩ ፔሌ፣ ሦስት የዓለም ዋንጫዎች በማንሳት በታሪክ ብቸኛው ከመሆኑ በተጨማሪ በርካታ ግቦችንም በማስቆጠር የክብረ ወሰን ባለቤት ነው። ባለፈው ሳምንት በ82 ዓመቱ ያረፈው ፔሌ የእግር ኳስ ነገር ሲነሳ ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ እና ታሪኩ ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በመላው ዓለም ሲነገር ቆይቷል። በዚህም የፔሌ አብዛኛው ታሪክ እና ገጠመኙ በስፋት ተነግሯል ቢባልም ስለኳሱ ንጉሥ ብዙም ያለተባለለቸውን የተወሰኑ ጉዳዮችን እነሆ።
ለፔሌ ሲባል ዳኛ ከሜዳ መባረሩን ያውቃሉ?
በ1968 (እአአ) የብራዚል ቡድን ለኦሊምፒክ ውድድር ዝግጅት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ከኮሎምቢያ አቻው ጋር ቦጎታ ውስጥ ገጥሞ ነበር። በወቅቱ ቀይ ካርድ ሥራ ላይ ውሎ ስላልነበረ የጨዋታው ዳኛ ጉሌርሞ ቬላስጌዝ ፔሌ በኮሎምቢያ ተጫዋች ላይ ጥፋት በመፈጸሙ ከሜዳ እንዲወጣ አዘዙ በዚህ ጊዜ በስታዲየሙ ውስጥ ቀውጢ ተፈጠረ። ብራዚላውያኑ ተጫዋቾች የቡድናቸው ወሳኝ ተጫዋች ከሜዳ እንዲወጣ መታዘዙ አስቆጣቸው፣ የእግር ኳሱን ኮከብ ለመመልከት ስታዲየም የታደሙት ኮሎምቢያውያንም የፔሌን ከሜዳ መባረር በመቃወማቸው ግርግር ተፈጠረ። ዳኛውም በተፈጠረው ውዝግብ መሃል ጉሸማ ደርሶባቸው ፊሽካቸውን ለአንደኛው የመስመር ዳኛ አስረክበው ከሜዳ ሲወጡ፣ ፔሌ ወደ ጨዋታው እንዲመለስ ተደርጎ ግጥሚያው ቀጥሏል።
የፔሌን ጨዋታ ለማየት ተኩስ አቁም ተደርጎ ነበር?
በአውሮፓውያኑ 1960ዎቹ ፔሌ የሚጫወትበት የሳንቶስ ቡድን በዓለም ላይ ካሉ ዝነኛ ክለቦች መካከል አንዱ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስገኙ የወዳጅነት ጨዋታዎችን በዓለም ዙሪያ እየተጓዘ ያደርግ ነበር። ከእነዚህ ጨዋታዎች መካከል ሳንቶስ በ1969 በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ወደ ነበረችው አፍሪካዊት አገር ናይጄሪያ በመሄድ በቤኒን ከተማ ካለ ቡድን ጋር ተጋጥመው 2 ለ 1 አሸንፏል። በወቅቱ ቢያፍራ የተባለችውን ግዛት ከናይጄሪያ ለመገንጠል የተጀመረ ጦርነት ይካሄድ ነበር። ፔሌ የሚገኝበት የሳንቶስ ቡድን የደኅንነት ስጋት ስለነበረው ለጨዋታ ከማምራቱ በፊት ተዋጊዎቹ ወገኖች ተኩስ ለማቆም ተስማምተው ነበር። በእርስ በርስ ጦርነቱ የሚሳተፉት ወገኖች ጨዋታው በሚካሄድበት ወቅት ጦርነቱን እንደሚያቆሙ እና አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ጥቃት እንደማይሰነዝሩ አረጋግጠዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ዝነኛው ፔሌ በቡድኑ ውስጥ መካተቱ ነው ተብሎ ይታመናል።
ታዋቂዎቹ ‘ዘ ቢትልስ’ ፔሌን እንዳያዩ ተከልክለዋል?
ፔሌ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ በ1975 (እአአ) በመሄድ ኒው ዮርክ ኮስሞስ የተባለን ቡድን ተቀላቅሎ ነበር። ከቡድኑ አባላት ጋር ለመግባባት እንዲያግዘው ኒው ዮርክ ከደረሰ በኋላ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መማር በጀመረበት ጊዜ፣ በዘመኑ በሙዚቃው ዘርፍ በመላው ዓለም ተወዳጅ የነበሩት የ‘ዘ ቢትልስ’ የሙዚቃ ቡድን አባል ከሆነው ከጆን ሌነን ጋር ተገናኝተዋል። በ1966 (እአአ) እንግሊዝ ውስጥ የዓለም ዋንጫ በተካሄደበት ጊዜ ታዋቂዎቹ ሙዚቀኞች ፔሌን እና የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ተጫወቾችን ለማየት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ሌነን ለፔሌ እንደነገረው የዘ ቢትልስ ሙዚቀኞች ሙከራ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ይህም የሆነው በወግ አጥባቂ የብራዚል እግር ኳስ ማኅበር ባለሥልጣናት እምቢተኝነት መሆኑን ፔሌ ጽፏል።
ፔሌ ለምን ለአውሮፓ ቡድን መጫወት አልቻለም?
የፔሌ ተቺዎች ፔሌ እግር ኳስን በአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ተጫውቶ አለማወቁ ያለተቀናቃኝ የእግር ኳስ ንጉሥ እየተባለ ለመዝለቅ ሕይወቱን ቀላል አድርጎለታል ይላሉ። ለዚህ ግን ችግሩ የፔሌ አልነበረም። እንደሚነገረው ከሌሎች ብራዚላውያን ተጫዋቾች በተለየ ፔሌ ዝነኛ በነበረባቸው ዓመታት ወደ ውጪ አገር ሄዶ እንዳይጫወት ታግዶ ነበር። በወቅቱ በተጫዋቾች ዕጣ ፈንታ ላይ ክለቦች ወሳኝ ስለነበሩ፣ ክለቡ ሳንቶስ ከሪያል ማድሪድ እና ከኤሲ ሚላን ፔሌን ለመውሰድ የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል። ፔሌ ብራዚል ውስጥ ብቻ እንዲጫወት ግፊቱ ከመንግሥት በኩልም መጥቶ ነበር። በ1961 (እአአ) የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጃኒዮ ኳድሮስ፣ ፔሌ “ወደ ውጪ ሊላክ የማይችል ብሔራዊ ሀብት ነው” ብለው አወጀው ነበር። ነገር ግን ከዓመታት በኋላ ፔሌ የአሜሪካውን ኒው ዮርክ ኮስሞስ ቡድንን በመቀላቀል በውጪ አገር ቡድን ውስጥ ተሰልፎ የመጫወት ዕድል አገኘ።
ፔሌ ለምን አምበል ሳይሆን የእግር ኳስ ዘመኑ አበቃ?
ምንም ያህል የእግር ኳስ ጥበበኛ ቢሆን፣ ዝናው በዓለም ቢናኝ ፔሌ በእግር ኳስ ዘመኑ በአምበልነት በጨዋታ ላይ የተሳተፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ለአገሩ ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ለቡድኑ አምበል እንዲሆን ሲጠየቅ እምቢኝ በማለቱ ነበር። ፔሌ ለአንድ ጊዜም ቢሆን የአምበልነቱን መለያ ክንዱ ላይ ያሰረው የእግር ኳስ ዘመኑ ካበቃ በኋላ በ50ኛ ዓመት ዕድሜው ለብሔራዊ ቡድኑ በተሰለፈበት ጊዜ ነው። ይህ የሆነው ከብሔራዊ ቡድኑ ተሳትፎ ጫማውን ከሰቀለ ከ19 ዓመታት በኋላ በ1990 (እአአ) ለፔሌ 50ኛ ዓመት በተዘጋጀው ጨዋታ ላይ ነው። ጨዋታው ጣሊያን ሚላን ውስጥ የተካሄደ ሲሆን በብራዚል ብሔራዊ ቡድን እና ከመላው ዓለም የተወጣጡ ታዋቂ ተጫዋቾች መካከል ሲሆን፣ ፔሌ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ፔሌ ለምን ከሜዳ “ተጠልፎ” ተወሰደ?
የሳንቶስ ቡድን ተጫዋቾች በ1972 (እአአ) ለግጥሚያ ወደ ካሪቢያኗ አገር ትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ ለግጥሚያ በሄዱበት ጊዜ በአገሪቱ ሰላም ስላልነበረ በቶሎ ግጥሚያቸውን አደርገው ወደ አገራቸው ለመመለስ ጓጉተው ነበር። ነገር ግን በጨዋታው ላይ በ43ኛው ደቂቃ ፔሌ ግብ ሲያስቆጥር ያልጠበቁት ነገር ተከሰተ። በስታዲየሙ የነበሩት ተመልካቾች በደስታ ሜዳውን ጥሰው ገቡ። ከዚያም ግብ ያስቆጠረውን ፔሌን በትከሻቸው ላይ ተሸክመው ከስታዲየም ውጪ ይዘውት በመውጣት በጎዳናዎች ላይ እየጨፈሩ ደስታቸውን ይገልጹ ነበር። በወቅቱ ከቡድኑ አባላት ተለይቶ በደጋፊዎቹ ወደ ጎዳና የተወሰደውን ፔሌን ከትከሻቸው ላይ አውርዶ ከቡድኑ ጋር ለመቀላቀል ከፍ ያለ ጥረትን ፈልጎ ነበር።ምንጭ፡- ቢቢሲ አማርኛ እና ሌሎችም
