የኳታር ዓለም ዋንጫ እና ከሜዳ ውጪ የነበረው ጦርነት!

Date:

ኳታር የኢኳዶር ተጨዋቾችን ለመደለል ሞክራለች በሚል በሬ ወለደ ወሬ ተጀምሮ ሊዮኔል ሜሲ እና አርጀንቲናን የክብር ካባ በማልበስ የተጠናቀቀው የ2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከበስተጀርባው ግን ብዙ ፖለቲካዊ ሰበዞች እና የሴራ ትንተናን የያዘ ነበር። በእርግጥ ለኳታራውያኑ እና ለመላው የመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝብ የዓለም ዋንጫው ከውድቀት ይልቅ ስኬትን ያላበሳቸው እንደሆነ ሊያስቡ ቢችሉም ምዕራባውያኑ ግን ከነጭ ጋቢ ጥቁር ነጥብን ከመፈለግ አልቦዘኑም።

ኳታር አስቀድማ ውድድሩን ከተረከበችበት ጊዜ ጀምሮ ስሟን የሚያጎድፍ ባታጣም የውድድሩ ጅማሮ ሰሞን ላይ የነበረው ከበድ ያለ የትችት ናዳ ግን ሊቋቋሙት የሚከብድ ናላን የሚያዞር ይመስል ነበር። ኳታር እና የዓለም አቀፉ እግርኳስ ማህበራት የበላይ አስተዳዳሪ (ፊፋ) ግን ያንን ሁሉ ቅጥ ያጣ የትችት ናዳ በተረጋጋ መንፈስ የሚያስተናግዱበት የደነደነ ልብ ነበራቸው። 

ፊፋ በፕሬዝዳንቱ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በኩል አርፋቹ እግርኳሱ ላይ አተኩሩ እያለ ለተወዳዳሪ ሀገራት ማስጠንቀቂያ ሲልክ ኳታር በበኩሏ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የሚሰነዘርብኝ ክስ ሁሉ በሬ ወለደ ነው። የውድድሩ ጅማሮ እውነታውን ይገልጥላቹሃል በማለት ጫናውን በጋራ ለማረጋጋት ሲጥሩ ተስተውለዋል።

የሁሉ መጀመሪያ የነበረው ግን አምጃድ ጠሃ የተባለው ግለሰብ በይፋዊ የቲውተር ገፁ ላይ ኳታር የመክፈቻ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንዲረዳት ስምንት ለሚደርሱ የኢኳዶር ተጨዋቾች 7.4 ሚሊየን ዶላር በጉቦ መልክ ሰጥታለች ማለቱ ነበር። ግለሰቡ አራት መቶ ሺ የሚደርሱ ተከታዮች ያሉት ሲሆን ዜናውን ተዓማኒ የተባሉ የመገናኛ ብዙኃን በየቋንቋቸው ለሕዝባቸው ሲያደርሱ መታዘብ ችሏል። የሆላንዱ ደ ቴሌግራፍ የሕንዶቹ ኢንዲያ ኢኮኖሚክ ታይምስ እና ሂንዱስታን ታይምስ ተጠቃሾች ነበሩ።

በቲክቶክ የዩኤስ የዘገባ ምንጭ የሆነው ባርስቱል ስፖርት ይህኑን ዘገባ ሲያገባ 1.3 ሚሊየን ጊዜ መታየት ችሏል። ጉዳዩን በቲውተር እና በቲክቶክ ለማስተጋባት የሞከሩት ሁለት ግለሰቦች ስለማንነታቸው ዘ አትሌቲክ በተባለው ግዙፍ ሚዲያ በተጠየቁ ጊዜ ስለ መካከለኛ ምስራቅ ትኩረቱን አድርጎ በሚሰራ የብሪታኒያ ጥናት እና ምርምር ተቋም ውስጥ እንደሚሰሩ ነበር ይፋ ያደረጉት። ነገር ግን በተደረገው ማጣራት እንዲህ ያለ ተቋም በመላው ብሪታኒያ ሊገኝ አልቻለም። ይህ አስቀድሞም ቢሆን የዚህ ውድድር ለኳታር መሰጠትን ላለመቀበል የትችት ተኩሳቸውን የከፈቱ አካላት የውድድሩን መክፈቻ እና የሀገሪቱን ላቅ ያለ ዝግጅት ለማጣጣል የተጓዙበት ርቀት ማሳያ ሆኖ አልፏል።

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች እውነታ ላይ የተከፈቱ ጦርነቶች ከመሆን አልፈው የተቺዎቹ ማንነት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ማድረጋቸው አይቀርም። ለምሳሌ እንኳን አምጃድ ጠሃን ብንወስድ እንኳን “The Deception Arab Spring” በሚለው ጽሑፉ በዐረቡ አለም ተነስተው የነበሩ ሕዝባዊ አመፆችን አላስፈላጊነት የጠቀሰ ነው ይሄም የግለሰቡን ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ለራሱ ጥቅም እና ፍላጎት መቆምን አመላካች ነው በሚል ከፍተኛ ትችት ደርሶበታል። በማህበራዊ ሚዲያ ገፆቻቸው ብዙ ተከታይ ስለያዙ አሊያም ከገፃቸው ጎን ሰማያዊ ጭረትን ስላገኙ ብቻ ተዓማኒ አርጎ መቀበልም የተከታዩ ስህተት እንደሆነ ጠቋሚ ነው።

አምጃድ ጠሃ ዘ አትሌቲክ የተሰኘው ግዙፍ የሚዲያ ተቋም በሱ የተሳሳተ መረጃ ላይ ሰፊ ሀተታ በተነገረው ጊዜ በይፋዊ የቲውተር ገፁ ላይ ያጋራውን መረጃ ወዲያው አጥፍቶታል። የተሳሳቱ መረጃዎች አንዴ ካፈተለኩ የተደራሽነታቸውን መጠን መገመት ከባድ አይሆንም። ለዛም ነው በዓለም ዋንጫው ኳታርን በአሠልጣኝነት የመሩት ፌሊክስ ሳንቼዝ በይነ-መረብ ጥቅሙ ላይ ያለ እንደሆነ ሁሉ ጉዳቱም በዛው ልክ ነው ብለው የገለፁት።

ከሕዝብ ግንኙነት ስራ ጋር በተያያዘ ኳታር አስቀድሞም ቢሆን በእግርኳሱ እዚህ ግባ የማይባል ስምን መያዟ እና በሰበአዊ መብት አያያዟ ላይ ጥያቄ ሲነሳባት በመክረሙ ምክንያት ትኩረት ሰጥታ እንድትሰራ አስገድዷታል። ፈረንጆቹ “Sports Washing” ብለው ያስቀምጡታል የጎደፈን ስም በስፖርታዊ ክንውኖች ለማጥራት የሚደረግ ጥረት ነው። የውድድሩ ጅማሮ ሲቃረብ ዳቪድ ቤካምን አስቀድማ ደሞ እንደ ዚነዲን ዚዳን ፣ ፔፕ ጓርዲዮላ ፣ ጋብሬል ባቲስቱታ ፣ ሮጀር ሚላ እና ቲም ካሂልን ለማስታወቂያ ስራ መጠቀሟ ከምዕራባዊያኑ የመገናኛ አውታሮች የተሰነዘረባትን የበዛ ፍላፃ ለመቋቋም እንዳስቸግራት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

ለምሳሌ የቀድሞ የባርሴሎና አማካይ ዣቪ ሄርናንዴዝ በኳታር አል-ሳድን በሚያሰለጥነበት ወቅት ስለ ዓለም ዋንጫው በጎ በጎ ነገሮችን ብቻ እንዲያወራ ለሶስት አመት የሚቆይ ስምምነት ነበራቸው። በስምምነቱ መሰረት ዣቪ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ቀርቦ ስለ ውድድሩ ካላወራ ከክፍያው የሚቆረጥበትን አንቀፅ የያዘ ነበር። የቀድሞውን የኤቨርተን የፊት መስመር ተሠላፊ ቲም ካሂልንም ብንወስድ በአውስትራሊያ እግርኳስ ፌደሬሽን በኩል በኳታር ውክልና ቢሰጠውም ጎን ለጎን ግን የውድድሩ አምባሳደር ነበር። ታዲያ የአውስትራሊያ ብሄራዊ ቡድን እና የኳታር ዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ኮሚቴ ውዝግብ ውስጥ በገቡ ጊዜ ካሂል ዝምታን ለመምረጥ ተገዷል። ኳታር በሕዝብ ግንኙነት ስራዋ ላይ ስኬታማ ነበረች እንድንል የሚያደርገንም ስመጥር የሆኑ የእግርኳሱ ዓለም ሰዎችን ወደራሷ የሳበችበት መንገድ አስደናቂ በመሆኑም ጭምር ነው።

እንደዛም ቢሆን ኳታር ቀጥተኛም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ እንደ ዴኒማርክ እና ጀርመን ካሉ ሀገራት ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብታ ነበር። በእርግጥ ጀርመን ‹‹ዓይኔን ግንባር ያድርገው›› በሚመስል መልኩ ሰብዓዊ መብት ጥሳለች ብላ ስትከሳት ከከረመችው ኳታር ጋር የሊኪውድ ጋዝ አቅርቦት ለማግኘት ለ15 ዓመታት የሚዘልቅ ውል ማሰሯ በርካቶችን ያስገረመ ክስተት ሆኗል፡፡ ዴኒማርክ እና ጀርመን ግን በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ያላቸውን ጥያቄ ባሰሙበት ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል አቋም ሳያሳዩ ከምድባቸው በጊዜ በመውደቅ ነበር ዶሃን የተሰናበቱት። ከዚህም ባለፈ ኢራናዊያን መንግስት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ሲያሳዩ ሞሮኮ በበኩሏ ለፍልስጤማዊያን የድጋፍ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

የኳታሩ ውድድር ክብረ-ወሰን የሆነ ወጪ የወጣበት ብቻ ሳይሆን ፊፋም ሪከርድ የሆነ ገቢ ያጋበሰበት ሆኖ አልፏል። ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላም ቢሆን ስደተኛ ሰራተኞች በቂ የካሳ ክፍያ አላገኙም በሚል ንትርኩ ማቆሚያ ባይገኝለትም በመካከለኛዋ ምስራቅ ሀገር የተካሄደው የዓለም ዋንጫ ግን እግርኳሳዊ በሆኑ መመዘኛዎች እንከን የማይወጣለት፣ ብዙዎችን ባስማማ መልኩ ሊዮኔል ሜሲ እና አርጀንቲናን ያነገሰ፣ የተመልካች ድርቅ ያልመታው፣ ትልልቆቹ ቡድኖች ካልጠበቁት ቅዠት ጋር የተላተሙበት አስደናቂ ውድድር መሆን ችሏል።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

“ሎዛ ዘፀአት”እና “የሎዛ ድርሳናት”ተከታታይ ረጅም ልቦለድ መጻሕፍት ተመረቁ

በጋዜጠኛና ደራሲ መርዕድ እስጢፋኖስ የተጻፉት ሎዛ ዘፀአት(2014 ዓ.ም) እና...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል አደረሳችሁ፣ አደረሰን!! በክርስቲያኖች ዘንድ ጥምቀት...

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...