የገራልታ ተራራዎች የሞት ፍቅር

Date:

አቦነህ አሻግሬ ዘኢየሱስ
በመጽሀፍ ቅዱስ ዉስጥ የሰፈሩትን ክስተቶች ለመመርመር ከአገር አገር ለአመታት ሲንከራተት የነበረዉ አሜሪካዊ ተመራማሪዉ ጂም ራንኪን፣ አገራችንንም ከዳር እስከዳር ካሰሰ በሁዋላ የጥናት ግኝቱን እየሱስ በኢትዮጵያ (Jesuse in Ethiopia ) በተሰኘ መጽሀፉ-አሳተመ፡፡ መጽሀፉ፣ የእግዚአብሄር ልጅና እናቱ ቅድስት ማርያም ኢትዮጵያ ዉስጥ ከአብ ጋር ስለመገናኘታቸዉን ያተተልን ብቻ ሳይሆን የምጽአት ቀን የሚከናወነዉ በዚህች ቅድስት ምድር እንደሆነም በመረጃዉ ላይ በመንተራስ ተንብዮዋል፡፡ በሀይቆችና በጅረቶች ባበለጸጋት፣ በተራራና በሸንተረረር ባገዘፋት፣ በአርታሌ እሳተገሞራ ባደመቃት ልዩ አገር ላይ አምላክ የመጨረሻዉ የፍርድ ቀን ስርአት እንደሚያካሄድ አብራራቶዋል፡፡
በአገራችን የሰሜኑ ክፍል ያለዉን የመሬት አፈጣጠርና ግርማ ሞገስ እንደ እሱ ልብ ብሎ ለተመለከተ፣ በሰሞኑ በቆላ ተንቤን ተራራዎች፣ በተከዜ ሸለቆዎችና ከፍታዎች የተሰጠዉን የመጨረሻ ፍርድ ላጤነ ምእመን፣ኢትዮጵያ ለዚህ መንፈሳዊ የመዝጊያ ምእራፍ እንደተመረጠች አይጠራጠርም፡፡ እግዚአብሄር በአማልክት ኢምቢልታና መለከት ታጅቦ ከሰማይ ሰማያት ወርዶ፣ ከተራራ ዙፋኑ ተሰይሞ ለሁሉም እንደየእጁ ግራና ቀኝ ብይን ባይሰጥበት፣ እንደ የመጨረሻዉ የፍርድ ቀን ፍጻሜ ማመላከቻ ምልክት አድርጎም ይወስደዋል፡፡
በመከረኛዋ ሀዉዜን ወረዳ ዉስጥ ጠፈር ሊነኩ የሚዳዳቸዉ አስፈሪዎቹ የገራልታ ተራራዎች፣ እጩ የችሎት መናኸርያ እንደሆኑ ምስክር ሆንነ፡፡
ሌቱ አህያ ሆድ እንደመሰለ ድንገት የተሰማዉ ነጎድጉዋዳዊ ድምጽና እቶናዊ ብልጭታ፣ ገራልታ ምጽአት ላይ የጀመረ መስሎ ያስደነግጥ ነበር፡፡ ገራልታ ሎጅ ዉስጥ ሆነዉ የጦር ስልት ሲነድፉ የነበሩ የትህነግ ከፍተኛ አመራሮችና የጦር መኮንኖች፣ ፍንዳታዎችን እንደሰሙ፣ ድሮ በረሃ ሳሉ የለመዱት የጦር ጄት ሙዚቃዊ ድምጽ አይነት አልሆነባቸዉም፡፡ ደመነብሳዊ “ሀ እራስን ማዳን” እንጂ፡፡ የባለስልጣናት ሚስቶችና ልጆች የዋሻ ከለላ ለማግኘት እየተጩዋጩዋሁ ሲሮጡ ያሰሙ የነበረዉ የጭንቀት ድምጽ ልክ በመተከል፣በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአዲስ አበባ ፣ በቢሾፍቱ…. እንደሚሰማዉ ሰቆቃ የሚሰቀጥጥ ነበር፡፡ የሚያሳዝንም ነበር፡፡
በተለይ የሳባ ጭንቀት፡፡
ከወር በፊት የኒዉ ዮርክንና የካሊፎርኒያን አስፋልት ለመርገጥ ይጠየፉ የነበሩ የሳባ ሙልሙል እግሮች፣ በዚያ በገራልታ ቆንጥርና እሾህ እየተበሳሱ በደም ተበክለዋል፡፡ ከወር በፊት የፊል ኮሊንስ፣ ሊዮን ሪቼ፣ ኬኒ ሮጀርስ ሙዚቃዎችን ያጣጥሙ የነበሩ ጆሮዎች በፈንጂ ፍንዳታ ደንቁረዋል፡፡ ታየዉ የነበረዉ የጦርነት ፊልም፣ በእዉንነት ከፊትዋ በመከሰቱ ልብዋ በሽብር ተበትኖዋል፡፡ ዘመዶችዋን ተከትላ ቁልቁለቱን እየተንፉዋቀቀችና አቀበቱን እየቡዋጠጠች፣ ሶስት ሰአት ሙሉ እየተነሳች እየወደቀች፣ ሩጣ የገባችበት እጅግ ሰፊ ዋሻ ግን ከዚህ ጭንቀት ገላገላት፡፡
ዋሻዉ ወደ አፉ ጠበብ ያለ ቢሆንም ወደ ዉስጥ ስትዘልቅ እየሰፋ እየሰፋ ሄዶ በኤሌክትሪክ ጀነሬተር ቡዉ! ያለ ትንሽ መንደር መስሎዋል፡፡ እንደ አርከበ ሱቅ በመደዳ የተሰለፉ ትናንሽ የአለት ፍልፍል ክፍሎች በምታዉቃቸዉ የአባትዋና የእናትዋ ቤተሰቦች፣ በኮሎኔሎች ተጣበዋል፡፡ ክፍሎቹ እስከወገባቸዉ በብሎኬት የተገነቡ እንጂ መዝጊያ በር አልተበጀላቸዉም፡፡ እርስ በርስ ለመጠባበቂያ ሲባል፡፡ ክፍት ከሆነዉ ሰፊ ስፍራ፣ በካርቶን የተሞሉ ብስኩቶች፣ እሽግ ምግቦችና መጠጦች ተቆልለዋል፡፡ ከጎኑ ከሚታዩት ሰፋ ያሉ አምስት ቢሮ መሳይ ክፍሎች ዉስጥ ኮምፒዉተር፣ ሬዲዎ መገናኛ፣ የጦር መሳርያዎች፣ ከፍተኛ አመራሮች፣ አነስተኛ አልጋዎችና፣ የፊዚዮቴራፒ ረዳት ሴት ልዩ ሀይሎች ይታያሉ፡፡
ሳባ፣ ፊልም ትማርበት በነበረበት ወቅት፣ ስለ መከወኛ ቦታ ዲዛይን አሰራር የተማረችዉን በተግባር ማየቱዋ ፍርሀቱዋን ገፈፈላት፡፡ እንድትሰራዉ ኮንትራት የተፈራረመችዉ የመንግስት ምስረታና የትህነግ ድል ዶኩመንታሪ ፊልም ሀሳብ ቁልጭ ብሎ ታያት፡፡
የፍንዳታዉ ና የጠመንጃ ተኩስ ድምጽ እየቀረበ ቢመጣም እምብዛም ስጋት አላደረባትም፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ፣ያን ሁሉ በሶስት ዙር ምሽግ ቆፍሮ ያደፈጠዉን ዋሻ ጠባቂ አልፎ፣ በኮንክሪት ጭምር የተጠናከረዉን ዋሻ ደርምሶ የመግባት አቅም እንደሌለዉ እርግጠኛ ነች፡፡ በዚያ ላይ አባትዋ ስለመከላከያዉ ሰራዊት ፈሪነትና ደካማነት የነገርዋት አጽናንቶዋታል፡፡
ከአባትዋ ቢሮ ገብታ ከአልጋቸዉ ላይ አረፍ በማለት የዶክመንተሪዋን ትረካ ማሰብ እንደቃጣት፣ ቢኒዚኑ አጨበጨበ፡፡ ድምጹን ከፍ አድርጎ ጥብቅ ማሳሰብያ አወጀ – ቤንዚኑ፡፡
“ይህ ነጥብ የትግራይ ህዝባዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ኮማንድ ፖስት እንደመሆኑ መጠን፣ ወሳኝነት አለዉ፡፡ ሽምቅ ዉጊያ በመምራት ትግል ለማስቀጠል፣ ወይንም ነፍጠኛዉን እሰከ መጨረሻ መስዋእትነት ለመተናነቅ ከወሳኝ ምእራፍ ላይ ደርሰናል፡፡ እጃቸዉን ሰጥተዉ ጀግናዉን ህዝብ እንዳዋረዱት ከሀዲ ሽማግሌዎች ሳንሆን ለራሳችን የምትሆን ጥይት እስቀረች ድረስ እድሜና ጾታ ሳንለይ ለመዋደቅ መሳርያና ጥይት ተረከቡ ፡፡” ሲል መመርያ ሰጠ፡፡
ቤኒዚኑ እንደዚያ አጭርና ቀጫጫ ሆኖ ለምን ባለስልጣኑ ሁሉ እንደሚርበተበትለት በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ሰዉ ሁሉ በመደበኛ ስሙ እያወቀዉ ሳለ ለምን ቤንዚኑ በሉኝ እያለ በደህንነት ስሙ እንደሚያንተባትባቸዉ ለሳራ ግራ የገባ ነገር ነበር፣ ያዉም በመጨረሻዉ ቀን፡፡
እድሜ ጠገቡ ሥራ አስፈጻሚዉ ብድግ ብለዉ ሲነሱ ሁሉም ተከትሎዋቸዉ እየተጣደፈ ከመሳርያዉ ቁልል ሄዶ ነፍስ ወከፍ ጠመንጃና ረጃጅም ዝናር ጥይት እያነሳ ወደነበረበት ተመለሰ፡፡ ሁሉም አቀባበለ፡፡
የእጅ ቦምብ ፍንዳታዉና የክላሽንኮቭ ተኩስ ድምጽ እየቀረበ መጣ፡፡
ሥራ አስፈጻሚዉ ብድግ ብለዉ ጠመንጃዉን በተጠንቀቅ ከወደሩ በሁዋላ ድምጹን ከፍ አድርጎ ጉሮሮዉን አጸዳ፡፡
“ቤንዚኑ የሰጠኸዉ መመርያ ሳይንሳዊ ነዉ፡፡ ሆኖም መሪያችን እጅ ከሰጡ በሁዋላ፣ መስራች መሪዎቻችን ከተሰዉ በሁዋላ እኛም መሞት የለብንም፡፡ ነገሩ አልቆዋል፡፡ እጅ እንስጥ! ይሄ ደግሞ እዚህ ያለዉ ቡድን የጋራ አቁዋም ነዉ፡፡” ሲሉ ቆፍጠን ብለዉ ተናገሩ፡፡
“የሁላችሁ አቁዋም ነዉ”? ሁሉም ላይ በተራ አፈጠጠ፡፡ቤንዚኑ ብዉ አለ! በንዴት- ፣ ተቀጣጠለ፤ ሊነድ ትንሽ ቀርቶታል፡፡
የሚመልስ አልነበረም፡፡ ቤንዚኑ አንድ ሙከራ ማድረግ አለበት፡፡ አጭርና ጠንካራ ትምህርት መስጠጥ፡፡
“በደርግ የተሰዉ ታጋዮችን እናስታዉስ፣ አሲምባ ላይ በኢህአፓ የተሰዉ ጉዋዶችን እናስታዉስ፡፡ዛሬ እየመታን ያለዉ የአብይ ጦር እንደሆነ ብቻ አድርገን አናስብ፡፡ ህወሀትን በማፍረስ ላይ ያለዉ ዋናዉ ጠላታችን፣ አድፍጦ የቆየዉ የኢህአፓ አሀዳዊነት መንፈስ ነዉ፡፡ የኢህአፓ ርዝራዥ አዘናግቶን ኢህዴን ሆኖ ሲፈጠር ተታለልን፡፡ አዲስ አበባ ገብተን ኢህዴንን ወደ ብአዴንና ኦህዴድ ስንበትን፣ አህዳዊነታቸዉን በልባቸዉ ይዘዉ፣ ጥርሳቸዉን እያሳዩን 27 አመት በቂም በቀል ከዉስጥ ቦረቦሩን፡፡ ኢህዴን ኖቹ እነአባ ዱላና እነአዲሱ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ“ ብለዉ የሚጮሁ ልጆቻቸዉን በምስጢር ኮትኮተዉ፣ አብይና ደመቀን ከአመጽ መሪነት ረድፍ ላይ አሰለፉብን፡፡ እነዚህ ከሀዲዎች ደግሞ የድሮ እህዴን አባል የነበሩትን እነ ጀነራል ብርሀኑ ጁላን፣ እነጀነራል አበባዉ ታደሰን፣ እነ ጀነራል ባጫ ደበሌን በጦር መሪነት እየሾሙ በበቀል አስቀጠቀጡን፡፡ ከኛ ዉጭ የነበሩ የኢህአፓዎቹ ትምክህተኞች አንዳርጋቸዉ ጽጌና ብርሀኑ ነጋ ደግሞ ከጠላታችን ከኢሳያስ ጋር ተሞዳምደዉ፣ከአብይ ጋር አፋቅረዉ አስወረሩን፡፡ ይህ ነዉ አዲሱ የድርጅታችን ፖለቲካዊ ንድፈ ሀሳብ፡፡ እና ይህን እያወቃችሁ ለአህዳዊያን ተንበርክካችሁ እጅ ለመስጠት ታስባላችሁ? እጅ እንደሰጣችሁ ይረሽኑዋችሁዋል፡፡“ የወትሮዉ ተናዳጅነቱ ጣርያ ነክቶበት፣ እንደማስፈራራት አይኑን እያንዳንዱ ለይ አጉረጠረጠ፡፡
የሰጠዉ ንቃት ሀይለኛነት፣ ሌላዉ ቢቀር ቡድኑን ለሁለት እንደሚከፋፍልለት እርግጠኛ ነበር፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ቀጥሎ ምን እንደሚያደርግ ያዉቃል፡፡
“ብጻይ ቤንዚን፡፡“ አሉ የቡድን መሪዉ፡፡ “አብዮታዊ ዲሞክራሲያችን በቡድን መብት ላይ ብቻ ያተኮረ ስለመሆኑ ለወደፊቱ የምንገመግመዉ ይሆናል፡፡ የግል መብትን መጠበቅ ነበረብን፡፡ ስለዚህ እዚህ ያለዉን ሰዉ የግል መብት ማክበርን አብዮቱ ጠይቆዋል፡፡ እኔም አንተም በዚህን ጊዜ አስገዳጅ መመርያ ማስተላለፍ አንችልም፡፡ እንደምታየዉ እንደ እኔና እንደ አንተ ሁሉም በጁ ብረት ጨብጦዋል፡፡ እጄን ልስጥ ካለ ለጽናት ብለን ልንታኮስ ነዉ”? እርስ በርስ እንተላለቅ”?
የቤንዚኑ ሰዉነት በብስጭት ተንቀጠቀጠ፡፡ ሁሉንም ከገረመመ በሁዋላ ከጆንያ ዉስጥ የሪፓብሊካን ጋርድ ዩኒፎርም አዉጥቶ በችኮላ ለበሰ፡፡ የእጅ ቦምቦችን በጃኬቱና ሱሪ ኪሶች አጭቆ፤ የጥይት ዝናር በወገቡና በትከሻዉ አንዠርግጎ፣ ከበድ ያለ ጠመንጃ ይዞ ወደ ዋሻዉ መዉጫ ተንደረደረ፡፡
“እኔ ግን እጄን እንደሰጥ ድርጅቴ አላስተማረችኝም፡፡ እስከ መስዋእትነት እዋጋለሁ፡፡ የምትከተለኝ ተከተለኝ፡፡” ብሎ ወደ ዉጭ አፈተለከ፡፡
መትረየስ የተሸከመ አንድ ልዩ ጦር ብቻ ተከተለዉ፡፡
ትንሽ እንደቆየ፣ ጋብ ብሎ የነበረዉ ተኩስ ተጋግሎ ከዋሻዉ ደጅፍ ላይ ተንጣጣ፡፡ ተንካካ፡፡ በመሀሉ የድምጽ ማጉያ ጮኸ፤
“እጃችሁን ስጡ! ባለቀ ጦርነት ህይወታችሁን ከንቱ አታበላሹ፡፡ ወታደሮች! በእናንተ ሞት ለመኖር ለሚፈልጉ ጁንታዎች አትሙቱ፡፡ተዉዋቸዉና በሰላም እጅ ስጡ፡፡ የህወሀት አመራሮች ከመደምሰስ እጅ ብትሰጡ ይሻላል፡፡” አለ የስምሪቱ መሪ ወጣቱ ኮሎኔል፡፡
የተኩሱ መጠን እየቀነነሰ እየቀነሰ ሄዶ ረጭ አለ፡፡ ሸማቂዉ እጁን ወደ ሰማይ አንስቶ ከየምሽጉ እየወጣ ለምርኮ ወደ ፊት እየተራመደ በመደዳ ቁጢጥ አለ፡፡
ለጥቆ ህወሀትን የተቀላቀሉ ወፈር ወፈር ያሉ የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ መኮንኖች እጆቻቸዉ ከአናታቸዉ ላይ አድርገዉ ከዋሻ እየወጡ ቁጢጥ ቁጢጥ አሉ፡፡
ለጥቀዉ ደግሞ የቡድኑ መሪ የህወሀት ስራ አስፈጻሚ፣ ሴትና ወንድ ሲቪሎችን አስከትለዉ ከዋሻዉ አፍ በአግድም ተኮለኮሉ፡፡ ምዝገባዉ እንዳለቀ ግራና ቀኝ በሰራዊቱ እየታጀቡ መከረኛዉን የገራልታን ተራራ ሽቅብ ተያያዙት፡፡
ገራልታ፣ ሙሉ እምነት በልብ ዉስጥ ካልነገሰ እንዲህ በቀላሉ የሚያራምድ አይደለም፡፡ በዉስጡ ለተፈለፈሉት የ28 ዉቅር ቤተክርስቲያናት ጽኑ መነኮሳት ነዉ ገራም የሚሆነዉ፡፡ የትላንትናዉ የኤሮፕላን ከባድ ድብደባ ተራራዉን እየናደ ቁዋጥኙን በማፈረካከሱ፣ ጠባብዋ የእግር መንገድ በሹልና ስል አለቶች ተዘግታ ጉዞዉን ለምርኮኛዉ የመከራ አድርጎታል፡፡ የበለጠ አስቸጋሪ የሆነዉ ሬሳን ለመሻገር መዝለሉ ነዉ፡፡ የመከላከያ ሰራዊቱ እየተዋጋ ቁልቁል የወረደበት በመሆኑ እንግዳ አልሆነለትም፡፡ ድሉም ሞተር ሆኖለት ይፈተለካል፡፡
“ትንሽ ልረፍ፡፡” አሉ ስራ አስፈጻሚዉ ቀጥ ብለዉ፡፡
“ይበርቱ እንጂ ደግፌዎት የለ እንዴ!” አለ ኮሎኔሉ ክንዳቸዉ የቆለፈበትን ክንዱን ጠበቅ አድርጎ እንደመሸከም ከፍ እያደረጋቸዉ፡፡
“መነቃነቅ አልችልም፡፡ ብትፈልግ ግደለኝ፡፡” ይባስ ብለዉ ከመሬት ተቀጡ፡፡
የተከተለዉ ምርኮ ሁሉ ባለበት ቆመ፡፡
“ፍጠን ምርኩዝ ቁረጥላቸዉ፡፡” ለመከላከያ፡፡
“እግር ሲቃነቅ አይደል ምርኩዝ! አልችልም!”
“የህክምና ቡድኑን ጥራልኝ፡፡” ሲል ከጎኑ ላለዉ መከላከያ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ወዲያዉ የህክምና ቡድኑ አቀበቱን በሩጫ ወጥቶ ደረሰ፡፡
“ቃሬዛዉን አምጡና እንርዳቸዉ፡፡ እስከዚያ አንዳችሁ ማሳጅ አድርጉላቸዉ፡፡”
መከላከያ ተንበረከከና ከእግር ጣታቸዉ እስከጉልበታቸዉ አፍተለተለ፡፡
“እንዴ ! በቂም በቀል ልታወላልቀኝ ነዉ እንዴ?” ተቆጡ ፡፡
ከቃሬዛ አስተኝተዉ እንዳይንሸራተቱ በጎንና ነጎን ጥፍር አድርገዉ ተሸክመዉ ጉዞ ጀመሩ፡፡
“አባቴ ሞተ! አባቴ ሞተ!” የሚል ጩኸት ከሁዋላዉ እንደሰማ ዞር ሲል የሚያለቅሰዉ ጎረምሳዉ ምርኮ ነዉ፡፡ ወጣትዋ ሳባ፤ አቅፋዉ እየተራመደች ታባብለዋለች፡፡
“ምን ነክቶህ ነዉ አንተ” አለ ኮሎኔሉ በወታደራዊ ቆፍጣናነት
“ ያማዋል፡፡” አለች ሳባ፡፡
“ምኑን ነዉ የሚያመዉ?”
“ችንክላት ያማል፡፡ ወንድሜ የኔ” አንባዋ ዱብ ዱብ አለ፡፡
ኮሎኔሎም አተኩሮ ካየዉ በሁዋላ አይኑ ረጠበ፡፡ እራሱን በሀዘኔታ ነቀነቀ፡፡
“ከዋሻዉ ነዉ የታመመዉ?”
አሜሪካ፣ የአሜሪካን ሽግር!”
ልቡ ተነካ፡፡ ” አይ ትህነግ! በሉ የሁለቱን እጅ ልቀቁ፡፡ ይዘሽዉ ከፊት ፊቴ ሂጂ፡፡ እንዲያዉም አስቀድሚዉ ከአባቱ ጋር ይራመድ፡፡ ወደፊት!”
“አዉርዱኝ! አዉርዱኝ! እንደሞተ ሰዉ ተገንዤ አልጉዋዝም! አዉርዱኝ!” አሉ በመንፈራገጥ ተሸካሚዎችን እያንገዳገዱ፡፡
“አንቱ ሰዉዬ ሲከበሩ ይከበሩ! ምርኮ መሆኑዎን ዘነጉት እንዴ! አቀበቱዋን እንደወጣን ኤሊኮብተር ይመጣል፡፡ እስከዚያ ትእግስት ያድርጉ፡፡” ኮሎኔሉ በቁጣ፡፡
የገራልታ ወበቅ የሲኦል ነዉ፡፡ የተራራም ኦክስጂን ብን ነዉ፡፡ የሳባ እናት ሸሚዛቸዉን ከወገባቸዉ ላይ ሸብ አድርገዉ ምርኩዛቸዉን እየተደገፉ፣ በመከላከያ እየተሳቡ ጥርሳቸዉን ነክሰዉ ሲራመዱ፣ ወጣትዋ ሳባ ተዝለፈለፈች፡፡ ኮሎኔሉ ደርሶ ክንዱን ከክንዱዋ ሶቶ አስገብቶ ከፍ ሲያደረጋት መፍጠን ጀመረች፡፡
“ኮሎኔል ካን አይ አስክ ዩ ኤ ኩዌስሽን ?”
“ትችያለሽ ጠይቂኝ፡፡”
“ፊዉ ይርስ ኤጎ.. ላንተ ዘ ዳንሲንግ ካፒቴን ይላል የነበረ ላንተ ስም ያስታዉሳል?”
“ፊትዋን አየ፡፡ አተኩሮ አያት፡፡ ሳባ ነኝ እንዳትይኝ ብቻ!”
“እወ ! አይ አም ሳባ፡፡” ፈገግ አለች፡፡ ጥርሱዋ እንደ ንግስት ማክዳ ጥርስ ያምራል፡፡
“የህዳሴ ግድብ …?”
“የስ ! ኦን ዘ አባይ ዳም፡፡”
ልቡ ክዉ አለ፡፡ ኦኦኦኦ! ሃላፊነት! ሃላፊነት! ሃላፊነት! ዝም አለ፡፡ ዝም አለች፡፡ ክንዱዋን ጥብቅ አድርጎ ይበልጥ ደገፋት፡፡ ጉዞ፡፡
ጉዞዉን በንቁ አመራር እያስተናገደ ሳለ ግን የህዳሴ ግድብ ትዝታዉ እየተሸነቆረበት አስቸገረዉ፡፡ ወይድ! ብሎ ሲያባርረዉ እንደገና ድግን ይልበታል፡፡
ለታላቁ የአባይ የህዳሴ ግድብ ምረቃ ስነስርአት ከመላ አገሪቱ የተጠራ በሺዎች የሚቆጠር እንግዳ በተስፋና በደስታ ተሞልቶ፣ እየተገነባ ካለዉ ግድብ የላይኛዉ ወለል ላይ ሆኖ በሙዚቃ ባንድ ይምነሸነሻል፡፡ ከየአቅጣጫዉ የሚፈነጥቀዉ ባዉዛ መብራት ከሙዚቃዉ ምት ጋር እየተወዛወዘ ግድቡን በአሸብራቂ የአፍሪካ ቀለማት ያስዉባል፡፡ የምሽቱን ጨለማ ድል ነስቶ ቀትርን አፍክቶዋል፡፡
ለስላሳ ሙዚቃ ከተደጋገመ በሁዋላ፣ ሞቅ ያለ የትግርኛ ምት ሲጀምር ሁሉም ወደ ኦርኬስትራዉ ሮጠ፡፡ “እመበር ተጋዳላይ!“ ሲል አበበ በጎርናናዉ ድምጹ፣ አካባቢዉ ጩኸት በጩኸት ሆነ፡፡ ትርጉሙን የማያዉቀዉም ሁሉ እየተሽቀዳደመ የኦርኬስትራዉን መድረክ ሞላዉ፡፡ ሴት የለ፣ወንድ የለ፣ሽማግሌ የለ፣ ወጣት የለ፣ ተራ ሰራተኛ የለ፣ ሚኒስትር የለ፣ አባል የለ፣ ስራ አስፈጻሚ የለ፣ወታደር የለ፣ሲቪል የለ፣ ሁሉም ከአበበ በላይ እየጮኸ ሙሉ ክብ አስፍቶ፣ ትንንሽ እርምጃ በቄንጥ እየረገጠ፣ በትከሻዉ ቁልቁል እየመታ፣ እሽም!እሽም!እሽም! ይላል፡፡ከዘፋኙ ብዛት ቦታዉ ጠቦ መፈናፈኛ በመጥፋቱና፣ ዘፋኙን ለመሸለም መገፋፋቱ በማጨናነቁ ከጥበብ አኩዋያ ሁሉን ያረካ አልነበረም፡፡ ብቻ ላብ በላብ እስኪኮን ተጨፈረ ተጨፈረና በሙቅ ዳሸን ቢራ ተሀድሶ ተደረገ፡፡…….
ብንን አለ ኮሎኔሉ ቃሬዛ ተሸካሚዉ ቡድን ቀጥ ሲል፡፡
ምንድነዉ?”
“አስቸገሩ፡፡ እስከ ታች ተደራጅተናል፡፡ በሳቦቴጅ ዉሀ-ኤሌክትሪክ- ቴሌ እንዲቁዋረጥ፣ የእልህና የገንዘብ እጥረት እንዲፈጠር፣ በየመስርያ ቤቱ ስራ እንዲሽመደመድ፣ እርስ በርስ እንድትተላለቅ አድርገን በቅርቡ እንመለሳለን፡፡ የምታንገላቺኝ ሁሉ ያኔ የእጅሺን ታገኝያለሽ፤ እያሉ ሊወድቁ ይንፈራገጣሉ፡፡” ልጅ እግሩ መቶ አለቃ፡፡
“ቅጀት ዉስጥ ሆነዉ ነዉ፡፡ ቀጥል!” የኮሎኔል አጭር ትእዛዝ፡፡ ቡድኑ ጉዞ ቀጠለ፡፡
ደግሞ በትዝታ አፈፍ!
ከኦርኬስተራዉ የአማርኛ ምት ተሰማ፡፡ “የሸበል ገዳዬ ”ሲል አንጎራጉዋሪዉ፣ መድረኩ ጨፋሪ አልጠራ አለ፡፡ ለደቂቃ ቀዝቀዝ ካለ በሁዋላ ሶስት ጀኔራሎች፣ አንድ ወጣት ኮሎኔል እንደተመካከረ ሰዉ እየተርገበገቡ የመሀሉን መድረክ ተቆጣጠሩት፡፡ ኪነት እንጂ ወታደር አይመስሉም፡፡
ትርኢት ዘሎ ደግሞ፣ ከሳባ በእለቱ የሰማዉም ድምጽ ፣ ያወሩት ወገግ ብሎ ተሰታዉ፡፡ (በአጭሩ ተሰማዉ -ታየዉ ለማለት ነዉ፡፡)
“ቱ ዘ ዳም የመታሁ ዳድ ሂስቶሪካል ኢቨንት ሚስ ማድረግ ትሩ አይደለም፡፡ የኤሮፕሌን ትኬት ሴንድ ያደርጋል ..እኔ መታሁ፡፡ ዜን በታም ደስ ይላል ነበረ፡፡
“የአማሪክ ዳንሰሮሽ ፕሮፌሽናል ነበሩ፡፡ ላዉክ..ለማወክ.ቅ … ሁ አር ዜይ? አልኩ ለዳድ፡፡
ሁለት አምሀራ ጄኔራልስ፣ አንድ ኦሮሞ ጀኔራል አለ፡፡ በት.. ሁሉ ቱረታ ላይ ተኙ..ወቱ አለ፡፡
“አይ ዎዝ ሾክድ፡፡ ሁዋይ? ተየቀ፡፡”
“ዴንጀረስ ነዉ ሁሉ አለ፡፡ ዱ ዩ ቲንክ ዘይ አር ዴንጀረስ?”
“ስለኔ አልጠየቅሽም?” አለ ፈገግ ብሎ ፤ የግድቡ የባዉዛ ህብር ዉብ ያደረጋቸዉን አይኖችዋን በልቡ እየዳሰሰ፡፡
“ፊርስት አይ አስክድ አባዉት ዛት ያንግ ከይ ኮሎኔል፡፡ ዳድ ለኔ የነገረ.. እሱ ቬሪ ክሌቨር ነዉ፡፡ በት.. ሙችልችል ይላል…ዲፊካልት ቱ ኖዉ ሂም አለ፡፡ እሱ ፕራይም ሚኒስትር ይሁናል ድሪም ያደርጋል አለ፡፡ በጣም ሳኩት፣ ሳክቼ ሞቱኩት፡፡ ዳድ ሳቁ ሞተ፡፡ ዉስኪ ፈስሶዋል በልብስ… ሳቀ ጊዜ፡፡”
“እሺ ስለኔ ደግሞ ንገሪኝ፡፡”
“ አባዉት ዩ ?” የካሊፎርኒያዋ የሆሊዉድ ሴቶች ጸጉር ሰሪ ያሳመረችዉን ጸጉርዋን ወደሁወላዋ ብትን አድርጋ እየሳቀች፡፡
አዎ፡፡”
“አስተዋቃቂ ናዎ ሙዚክ ፎር ዲፐሎማት አለ የማክ ጃክሰን እስሙዝ ክሪሚናል ዘፈን መታ፡፡ እስሙዝ ክሪሚናል በአምሀርኛ ሁዋት
“እ..እ..እ..እ — ልስልስ ወንጀለኛ፡፡”
ዜን ኖ ባዲ ኬም ቱ ሰቴጅ! አንተ ብቻ፡፡ ማይ ሎርድ! ዩ ዌር ጀሰት ኤ ማይክል ጃክሰን፡፡ ነች ባርኔታ፣ ነች ልብስ፣ ኤ ገላሰስ፣ ኤር ላይ ትሄዳለህ ይመስላል፣ ዋዉ!” ሳታስበዉ እራስዋን ደረቱ ላይ ጣለች፡፡
”እሽ!”
”አይ አስክድ ዳድ አንቴ ማነዉ እሱ፡፡”
”ዳድ ሰይድ እኔ አያዉክም፡፡ ጎ ቱ ሂም፤ ዳንስ አድርጊ፡፡ ተከታተሊዉ፡፡”
”እኔ ተናደደ ፡፡ አር ዩ ትራይነግ ቱ ሜክ ሚ ኤ ስፓይ!!!!”
”ኖ ሰላይ ! ፖለቲካ አልፈልግም ብሎዋል አንቴ፣ እኔ ተስማምቶዋል፡፡ …. እኔ አንቴን የወደደዉ ግና የጃክሰን ብለድ ኦን ዚ ዳንስ ፍሎር… አመሀርኛ ምንድነዉ ?”
“ደም በጭፈራ ወለል ላይ ነዉ … ማለት ነዉ የኔ ተብታባ!”
“አንተ አሜሪካ ይወስዳል፡፡ ያገባል፡፡”
በግድቡ ጥግ ጠቃቅፈዉ ለሊቱን ሙሉ….
አመታት ሲሮጡ ታየዉ፡፡
የእጅ ሬዲዮዉ ጮኸ፡፡“ ሰብልዬ ሰብልዬ ኦቨር!”
ብንን!
ከሁዋላዉ የምርኮኛዉን ሰልፍ አየት አደረገ፡፡ ላብ በላብ ሆነዋል፡፡ መሄድ እየተሳናቸዉ ነዉ፡፡
“ቶሎ ቶሎ ተራመጂ !”ተቻኮለ፡፡
“ኖ! እኔ ችሎ አይሔድም፡፡ ደክሞዋል፡፡” ቀጥ አለች፡፡
“በአንድ እጁ እንደ ህጻን ወደትከሻዉ ወረወራት፤ 40 ኪሎም የማትመዝን ነፋስ፡፡ እቅፍ አድርጋዉ ተጣበቀችበት፡፡
“እዚህ መገኘት አልነበረብሽም፡፡” ላፍ ላፍ አደረገዉ አቀበቱን፡፡
“ዳድ ደወለ፡፡ ለንጻነት ሂስቶሪካል ኢቭነት ና ዶክሜንታሪ ስራ አለ፡፡ አኔ መታ፡፡ ፖለቲክስ እኔ አልወድም፡፡ … አንተ ሚስት አገባ?”
“በቃ ሳባ፡፡ ግዳጅ ላይ ነኝ፡፡ ዝምበይ፡፡”
“አንድ ኩዌሽን ብቻ፡፡ ኢንቨስተር ብሎ ዋሸ አንቴ ከአባይ ዳም፡፡ ለምን?”
“በቃ ብዬሻለሁ፡፡ ትእዛዝ ነዉ፡፡”
“ኦኬ ኦኬ ዚ ዳንሲንግ ካፒቴን!”
በድንገት ከወደላይ መትረየስ አስካካና ቦምብ ፈነዳዳ! ኮሎኔልና ሳባ እንደተቃቀፉ ወደቁ፡፡
ምርኮኞች ሁሉ ባሉበት ወዳደቁ፡፡ ገራልታ ተራራ እንደለመደበት በደም ወንዝ ጥሙን አረካ፡፡
የአጸፋ ምላሽ ከመከላከያ ሰራዊት ተጋጋለ፡፡ ከዚያ እረጭ፡፡
ወዲያዉ ሁለት ኮማንዶዎች፣ ፈንጂ ወርዋሪዉን ለኮለኔል ለማስረከብ ካደፈጠበት ይዘዉ ደረሱ፡፡ ኮሎኔሉ ከወገብ በታች በደም ርሶዋል፡፡
“ቤንዚኑ! አትማረክም ስትባል እጅ ሰጠህ?” እንደምንም ብሎ ወደ ሳባ ዞሮ አያት፡፡ አይኑዋ ገርበብ አድርጋ“ ዚ ዳንሲንግ ካፒቴን!” ብላ በትንሹ ፈገግ አለች፡፡ ወዲያዉ ለዘለአለሙ አሸለበች፡፡ የእሱም አይን ተስለመለመ፡፡ ተከደነ፡፡
ኤሊኮብተር ብቅ አለች፡፡
ገራልታ በሞት ፍቅር የደም ምሱን እንደጠገበ ከጎኑ ሌላ ጉብታ አበቀለ፡፡
አወይ አገሬ ኢትዮጵያ! ልጆችሽ ለስንት ዘመን እርስ በርስ ይበላሉ?
በዳግም ምጻት ገራልታ ላይ የመጨረሻ ፍርድ የሚፈረድላቸዉና የሚፈረድባቸዉ እነማን ይሆኑ ይሆን?

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...