ውጪ አገር የሚገኙ ሁለት ወንድማማቾች ለእናታቸው ቤት ባለ 32 ኢንች ቴሌቪዥን ሰደዱ አሉ፡፡ ከወራት በኋላ የእረፍት ጊዜያቸውን ከእናታቸው ጋር ለማሳለፍ ወደ ትውልድ አገራቸው መጥተው እቤታቸው ሲገቡ፣ የላኩት ባለ 32 ኢንች ቴሌቪዥን፣ ባለ 14 ኢንች ሆኖ አገኙት አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ግራ የተጋቡት ወንድማማቾች እናታቸውን ጠየቁ፤
‹‹እማ !››
‹‹ኧይ !››
‹‹የላክንልሽ ቴሌቪዥን ባለ 32 ኢንች ነው፡፡ ይኼ ግን ባለ 14 ኢንች ሆኗል፡፡ …ምንድን ነው ነገሩ?››
‹‹አይ ልጆቼ!›› አሉ እናት ፈገግ ብለው፤ ‹‹አይ ልጆቼ፤ ራሱ ነው እንዲህ የኾነው!››
‹‹እንዴት?››
‹‹ውሸት ሲነገር ሲሸማቀቅ፤ ውሸት ሲነገር ሲሸማቀቅ 32 የነበረው 14 ሆኖ አረፈው፡፡ …ኧረ እንኳን ሞባይል ሳያክል መጣችሁ ልጆቼ!››
ይኽ ፍተላ፣ በ1997 ዓ.ም ከተካሄደው ብሔራዊ የፖለቲካ ምርጫ ዘገባ ጋር ተያይዞ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ከተፈተሉ ታዋቂ ፍተላዎች አንዱ ነው፡፡ ፍተላው ሁለት ነገርን ይዘክራል፡፡ አንድም በወቅቱ ለሕዝቡ ሌላ አማራጭ ሚዲያ የሌለው መሆኑን፤ አንድም ደግሞ ራሱ ቴሌቪዥኑ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ከእውነታው የራቁ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳዎች ማቀበያ ብቻ መሆናቸውን፡፡
(በወቅቱ ሌላ አማራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያ አልነበረም፡፡ …እነ የአሜሪካን ድምፅ እና የጀርመን ድምፅን መስማት ደግሞ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡)
…ይኽን ጨዋታ እንደ መግቢያ አድርገን ወደ ዛሬው ጉዳያችን እንለፍ፤ ወደ ኢሳት (የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን)፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የኢሳት የቴሌቪዥን ጣቢያ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮ መክፈቱን ተከትሎ፣ ‹‹እዚህ ጋ አንድ ኖርማል ኢሳት!›› የምትል ጽሑፍ ጽፈን ነበር፡፡
ጽሑፏ የኢሳት የዝግጅት ክፍል ቁልፍ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፣ በሚሌኒየም አዳራሽ ከአድናቂዎቻቸው ጋር መገናኘታቸውን ምክንያት አድርጋ የተጻፈች ነበረች፡፡ …ይዘቷም፣ ኢሳት ከለውጡ በፊት በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት፣ በነባሩ ኢሕአዴግ ጊዜ ለሕዝቡ ዋና የመረጃ ምንጭ እና ድምፅ መሆኑን የምታትት፤ እንዲሁም ጸሐፊው ቢሻሻል የሚላቸውን አንዳንድ የጣቢያውን ነባር ሰሃዎች የጠቆመባት ነበረች፡፡
አዎ! የዛሬ ሁለት ዓመት፣ ለለውጡ ትልቅ ሚና ከተጫወቱ አካላት አንዱ ኢሳት መሆኑ በጠቅላይ ሚንስትሩ አንደበት ሳይቀር ተገልፆ ነበር፡፡ (በጠቅላይ ሚንስትሩ ዙሪያ፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው›› የሚሉ ሹማምንት የነበሩ ሰሞን)
ይኼን ተከትሎም አንዳንድ የአዲስ አበባ ምግብ ቤቶች፣ ‹‹ኢሳት ‹ኖርማል› እና ኢሳት ‹እስፔሻል› ›› የሚል የምግብ ዓይነት ፈጥረው ‹ሜኑአቸው› ውስጥ እንዳካተቱ በመገረም ጠቁመን ነበር፡፡ በወቅቱ መገረማችንን ለመግለፅ፣ ‹‹አይ ጊዜ! …ኢሳትን በስም መጥራት እንደ እሳት የሚፈራበት ወቅት አልፎ፣ ምግብ በኢሳት መጠራት ተጀመረ!›› ብለንም ነበር፡፡ (አሁን አሁን ቀረ እንጂ ያኔ፣ ‹‹አርሰናል፤ ቼልሲ እና ማንችስተር›› በሚሉ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ቡድኖችም ሳይቀር ለምግብ ዓይነቶች ስም መስጠት የተለመደ ነበር፡፡)
‹‹ኢሳት ምን ዓይነት ምግብ ነው?››
‹‹እስፔሻሉ ነው ኖርማሉ?››
‹‹እስፔሻሉ!››
‹‹በነጭ ሽንኩርት፣ በሎሚ እና በዝንጅብል ያበደ ቲማቲም ለብለብ፤ በዳጣ!››
‹‹ወይ ጉድ! …ኖርማሉስ?››
‹‹ነጭ ሽንኩርት እና ዝንጅብል ያልገባበት ቲማቲም ቁርጥ በአረንጓዴ ዳጣ!››
‹‹ማን ነሽ!?››
‹‹አቤት!››
‹‹እዚህ ጋ አንድ ‹ኢሳት ስፔሻል› አምጪልኝ!››
ኢሳት አማራጭ የመረጃ ምንጭ በሌለን ጊዜ በነጭ ሽንኩርት፣ በዝንጅብል እና በዳጣ ባበደ የቲማቲም ቁርጥ የተመሰለ መድኃኒት ነበር፡፡
(‹‹ሆዴን ተጣላኝ፤ ጉንፋን ብጤ ያዘኝ፤ ጉሮሮዬን ሕመም ብጤ ተሰማኝ›› ስትሉ፣ ‹‹ዝንጅብል አፍልታችሁ ጠጡበት፤ ነጭ ሽንኩርት ብሉበት! እንጀራውን ዳጣ ቀብታችሁ ተመገቡበት ንቅል ያደርግላችኋል!›› እንዲል የመንደር መካሪ፡፡ የኢሳትም አንዳንድ መረጃዎች እያቃጠሉ፤ እየለበለቡ፤ እየመረሩን የምንቀበላቸው መረጃዎች ነበሩ፡፡ ‹‹ዝንጅብሉ እና ዳጣው እንዲሁም ነጭ ሽንኩርቱ አንዳንዴ የጨጓራ ፀር እንደመሆኑ፣ ኢሳትም አልፎ አልፎ መረጃዎቹ መስመር የሚስቱበት፤ ጥቂት የሚጋነኑበት ጊዜም ነበር፡፡›› ብሎ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ያምናል፡፡)
…ሰሞኑን ግን ኢሳት በበጀት ምክንያት ከሜዳው ገለል ማለቱን ሰማን፡፡ …ያሳዝናል፡፡ (ለነገሩ ገለል ብሎ ከርሞ ተመልሶ መምጣቱ ለኢሳት አዲስ አይደለም፡፡)
ዛሬ፣ ከሁለት ዓመት በፊት እንደነበረው ያህል፣ ‹‹ምን አለ ኢሳት? …እከሌ ኢሳት ላይ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ …የምንትሴው ጉዳይ ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ቀረበ፤ …የእንትንን ዜና ኢሳት ዘግቦታል!›› ተብሎ ብዙ የሚነገርለት መረጃዎች ባይቀርብበትም፣ አሁን በያዘው የራሱ መንገድና አቀራረብ አማራጭ ሚዲያ ሆኖ ቢቀጥል የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ፅኑ ፍላጎት ነበር፡፡ (የነባር ጋዜጠኞቹ ከተቋሙ መውጣት ቅር ቢያሰኝም፡፡ ለነገሩ ተገንጣዮቹም በዛው ሳይጠፉ ሌላ አማራጭ ሚዲያ ይዘው መምጣታቸው የሚደገፍ ነው፡፡)
ለጉዳዩ አፅንኦት ለመስጠት ያህል፣ ያኔ፤ የሕትመቱም ሆነ ሌላው የብዙኃን መገናኛው ዘርፍ በመንግሥት መዳፍ ተጨብጦ እልህ አስጨራሽ ግብግብ ውስጥ በነበረበት በዚያን ጊዜ፣ ኢሳት ከአማራጭነቱም በላይ ዋነኛ የመረጃ ምንጭና የሕዝብ ድምፅ ሆኖ በማገልገሉ ለዚያ ውለታው ይኼ አይገባውም ብሎ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ያምናል፡፡
ከአንድ ቀን በፊት ይህን ጉዳይ አንስተን ከአንድ ጓደኛዬ ጋር እያወራን ሳለ፣ ወዳጄ ተበሳጭቶ እንዲህ አለ፤ ‹‹የጠቅላይ ሚንስትራችን ምላስ ጥቁር ነው!››
በወዳጄ ንግግር በእጅጉ ደንግጬ፣ ‹‹እንዴት?›› ስል ጠየቅኩ፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚንስትራችን ወደ ሥልጣን ሲመጡ ባደረጓቸው ሁለት ሦስት ንግግሮች ኢሳትን እያነሱ አሞግሰው ነበር፡፡››
‹‹እና …ቢያሞግሱስ!?››
‹‹የእሳቸው ሙገሳ ብዙ ሳይቆይ፣ ጋዜጠኞቹ ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አሁን ደግሞ ከዚያ በፊት በነበረው ኢሕአዴግ ሲረገም፣ ሲወገዝና የክስ ፋይል ሲከፈትበት የኖረው የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ብዙ መሥራት በሚጠበቅበት በዚህ ጊዜ ተዘግቶ አረፈዋ!››
በ ለ ው!
እውነት ኢሳት በጠቅላይ ሚንስትሩ አንደበት መሞካሸቱ ምን አተረፈለት? ወደ አገር ቤት ገብቶም ሥራ እንዲሠራ መፈቀዱ፣ ለስቱዲዮና ለቢሮ ወደል የኪራይ ገንዘብ ከማውጣት በላይ ምን አስገኘለት? …ይኽን ጥያቄ የምናነሳ ከሆነ፣ እውነትም፣ ‹‹የጠቅላይ ሚንስትራችን ምላስ ጥቁር ነው!›› ያሰኛል፡፡ (‹‹ጥቁር ምላስ›› በዚህ ዐውዱ፣ ‹‹ውዳሴው መርገም ሆኖ ቀን ቆጥሮ የሚመጣ፤ እርግማኑም ቢሆን የሚሰምር ማለት ብቻ ነው፡፡)
